የግል ባንኮች በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ ጠቅላላ የባለአክሲዮኖች ስብሰባ በማድረግ ተጠምደዋል፤ ይህ ወቅት ባንኮቹ ትርፍና ኪሳራቸውን በማስላት ለባለአክሲዮኖቻቸው የሚያሳውቁበት ወቅት ነው፤ ለመሆኑ የግል ባንኮች ዓመታዊ የትርፍ መጠናቸው ምን ይመስላል፤ ዝርዝር አለን፤
– ከግል ባንኮች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አዋሽ ባንክ ነው፤ አዋሽ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ በግል ባንኮች ታሪክ የመጀመርያው የሚያደርገውን ትርፍ ማግኘቱ ተነግሯል፤ ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 5.58 ቢሊዮን ብር አትርፏል፤ይህም ትርፉ ከዓምናው ጋር ሲመሳከር የ34 በመቶ ወይም የ1.2 ቢሊዮን ብር ዕድገት አለው፡፡
– የዳሸን ባንክ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 2.4 ቢሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን ባንኩ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ይህ የትርፍ ምጣኔ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከግል ባንኮች ሁለተኛውና ከፍተኛ የትርፍ መጠን ነው ፡፡
- አቢሲኒያ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን ከ103 ቢሊዮን ብር በላይ ያደረሰ ሲሆን የ2013 የሒሳብ ዓመት ከቀዳሚው ዓመት የ90 በመቶ ዕድገት ያሳየ ትርፍ አስመዝግቧል፣ ከታክስ በፊት2. 05 ቢሊዮን ብር ማትረፉ ተገልጿል፡፡
- ኅብረት ባንክ በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት የባንክ ኢንዱስትሪው የተለያዩ ተግዳሮቶችን ያስተናገደ ቢሆንም፣ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት1. 44 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል፡፡
- የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት1. 68 ቢሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን የባለአክሲዮኖች የተከፈለ ካፒታል ወደ አሥር ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወስኗል
- ቡና ባንክ በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ትርፉን በ61 በመቶ በማሳደግ ከታክስ በፊት 937 ሚሊዮን ብር ሲያተርፍ፣ የተበላሸ የብድር መጠኑንም በግማሽ መቀነሱን አስታወቀ፡፡
- አዲስ ኢንትርናሽናል ባንክ ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔው ከታክስ በፊት368 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ የትርፍ መጠን ከቀደመው ዓመት በ44 ብልጫ አሳይቷል፡፡ ከ13,064 በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ 876 ሠራተኞችን ይዟል፣ የቅርንጫፎቹም ብዛት 91 ደርሷል፡፡
- ዘመን ባንክ በ2013 በጀት ዓመት 1. 35 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ34.86 በመቶ ወይም 350 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው
- ዓባይ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት1.15 ቢሊዮን ብር ሲያተርፍ ፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የትርፍ ምጣኔ በ80 በመቶ ማደጉን ታውቋል፡፡
- ትርፍ የቀነሰባቸው ባንኮች መሀከል
- አንበሳ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያመላክተው በ2013 የሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ 414 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ካለፈው ዓመት ትርፍ ጋር ሲነፃፀር ከ366 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ780 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡
- የኢትዮጵያን የባንክ ገበያ የተቀላቀለበትን 25ኛ ዓመት እየዘከረ ያለው ወጋገን ባንክ፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 193 ሚሊዮን ብር ብቻ ሆኗል፡፡ ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉ የሚታወስ ሲሆን፣ የ2013 የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠን ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ከ880 ሚሊዮን ብር መቀነሱን የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት አመላክቷል፡፡

