ዩክሬን 400 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም የበቀል እርምጃ በሞስኮ ወስዳለች ተባለ፡፡
በሰሞንኛው ወታደራዊ ሹም ሽር ህዝባዊ አመጽ የተነሳበት የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አስተዳደር ሞስኮን እንቅልፍ አልባ ሌሊት እንድታሳልፍ አድርጓታል ተብሏል፡፡
ዩክሬን የጥቃት ኢላማዋን በሞስኮ ላይ ያነጣጠረችው ከሩሲያ ከፍተኛ የባላስቲክ ሚሳኤል ድብደባ በኋላ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ዩክሬን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን ወደ ሞስኮ የተኮሰችው፤እስካሁን ጦርነቱ ከተመጀረ ወዲህ እጅግ አደገኛ የተባለው ጥቃት ከደረሰባትና ካገገመች በኋላ ነው፡፡
ሰሞኑን ሩሲያ የዩክሬኗን ኪቭን እና ሌሎች ከተሞችን በባላስቲክ ሚሳኤል መምታቷ ይታወቃል፡፡
በዚህ የዩክሬን የድሮን ጥቃት 10 ሰዎች መቁሰላቸው ይፋ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም በርካታ የመኖሪያ ህንጻዎችና የሲቪል ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
ኪቭ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በሩሲያ ግዛት ላይ የምታደርሰው የአየር ጥቃት እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ እነዚህ የቅርብ ጊዜ ጥቃቶች በሞስኮ የነዳጅ ተቋማት ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ሩሲያም በበኩሏ ለዩክሬን አቅም ከባድ የሚባሉትን ባላስቲክ ሚሳኤሎች በመጠቀም በዩክሬን ላይ ጥቃት ማድረሷን ገፍታበታለች፡፡ በሰሞንኛው ጥቃትም ስድስት ሰዎችን የገደለ እና በደርዘን የሚቆጠሩትን ደግሞ ያቆሰለ ጥቃት አድርሳለች፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በጦር ሰዎቻቸው መካከል ከሰሞኑ ያከናወኑት ሽግሽግ በህዝባቸው ዘንድ አመጽን አስነስቶባቸዋል፡፡ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በግንቦት ወር 1ሺ 54 የዩክሬን ድሮኖችን በአንድ ቀን ውስጥ ማክሸፍ መቻሉን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የምዕራባዊያን አጋሮቻቸው ከሩሲያ ባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት የሚታደግ የአየር መከላከያ ስርዓት እንዲያቀርቡላቸው እየተማጸኑ ነው፡፡
የሩሲያ ሃይሎች ዛሬ አዳሩን ሁለት ሚሳኤል እና 94 የረጅም ርቀት ድሮኖችን ወደ ዩክሬን ተኩሰዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 81 ድሮኖች ከሽፈዋል የተባለ ሲሆን፤9 ድሮኖች እና ሚሳኤሎች ግን በዘጠኝ ስፍራዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዩክሬን ገልጻለች፡፡//

