ዳሸን ባንክ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለክቡር ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን የዕውቅና እና የማስታወሻ ሽልማት አበረከተ፡፡ ዳሸን ባንክ የ30 ሚሊዮን ብር የማህበራዊ ኃላፊነት ድጋፍ በማድረግና ለዳሸን ዕድል ጨዋታ አሸናፊ የቢዋይዲ መኪና በመሸለም 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አጠቃለለ፡፡
የዳሸን ባንክን 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ላለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ መርኃ-ግብሮች ሲከበር የቆየው የአከባበር ሥነ ስርዓት በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀ ደማቅ የመዝጊያ ሥነ ስርዓት የ30 ሚሊዮን ብር የማህበራዊ ኃላፊነት ድጋፍ በማድረግና ለዳሸን ዕድል ጨዋታ አሸናፊ የቢዋይዲ መኪና በመሸለም ተጠቃለለ፡፡
በመርኃግበሩ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ክቡር እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የፋይናንስ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች፣ አጋር ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን የስራ ኃላፊዎችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ታድመዋል፡፡
ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ያደረገውን አበርክቶ በሚገልፅ መንገድ የ30ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ከጥር 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ኹነቶች ሲዘክር የቆየ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ የዳሸን ባንክ 30ኛ ዓመት ኤክስፖ፣ የኢኖቬሽን ወር፣ የሴቶች አቅም የማጎልበቻ መርሐግብር እንዲሁም ለደንበኞች የእንኳን አደረሳችሁ የአጭር መልዕከት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡
በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው ደማቅ መርሐግብር ላይ ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ላይ ገናና የሆነ ተቋም እንዲሆን ስያሜ ከማውጣት ጀምሮ የባንኩ ምስረታ ዕውን እንዲሆን ከፍተኛ ዕገዛ ላደረጉት ክቡር ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን የዕውቅና እና የማስታወሻ ሽልማት ተበርክቷል፡፡ከዚህ በተጨማሪም ለዳሸን ባንክ 11 ባለራዕይ መስራቾች፣ ለቀድሞ የስራ አመራር ቦርድ ኃላፊዎችና ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች፣ አጋር ተቋማት፣ የረዥም ዓመት ደንበኞች እንዲሁም ከዳሸን ባንክ ምስረታ አንስቶ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ላገለገሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡
ዳሸን ባንክ የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራትን በመወጣት ረገድ ከምስረታው አንስቶ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በመመደብ የማህበረሰብ ተኮር ስራዎች፣ የተፈጥሮ አደጋ ምላሽ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሞችን የሚሰራ ሲሆን፣ የ30ኛ ዓመት ምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ልዩ ልዩ የአዕምሮ እድገት ውሱኑነት ያለባቸው ወገኖች ላይ ለሚሰራው የዲቦራ ፋውንዴሽን የ30 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የዲቦራ ፋውንዴሽን ለትርፍ ያልተቋቋመ የአዕምሮ እድገት ውሱኑነት ያለባቸው ልጆች ትምህርትና የሙያ ሥልጠና ላይ የሚሰረ የግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን፣ ዳሸን ባንክም በተለምዶ በአገራችን አነስተኛ ትኩረት የተሰጠውን የአእምሮ እድገት ውስንነት ችግር በአርአያነት ለመደገፍ በማሰብ የ30 ሚሊዮን ብር የማህበራዊ ኃላፊነት ድጋፉን አበርክቷል።
በሌላ በኩል በዳሸን ሱፐር አፕ በቀረበውና እስከ 30 ሚሊዮን ብር የሚደርሱ ሽልማቶች በቀረቡበት የዳሸን ዕድል ጨዋታ የዘመናዊ ቢዋይዲ ሴጉል የኤሌክትሪክ መኪና አሸናፊ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
ዳሸን ባንክ ለሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን የዕውቅና እና የማስታወሻ ሽልማት አበረከተ

