ዳሽን ባንክ እ.ኤ.አ በ2022 ” ዘ ባንከር ” በተሰኘውና በፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ ስር በሚታተመው መፅሄት በኢትየጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቀዳሚ ሆኖ በመመረጥ ሽልማት ተቀብሏል።
ባንኩ ይህንን ሽልማት ሲቀበል ለ12ኛ ጊዜ ሲሆን ሽልማቱን የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በእንግሊዝ ተገኝተው ተቀብለዋል፡፡
በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ዘርፍ በተለይ ባለፈው ዓመት ያሳየው እመርታ ለሽልማት እንዳበቃው ተነግሯል።
ከኢትዮ ቴሌኮምና በፋይንንስ አገልግሎት ዙሪያ ከሚሰሩ ሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር የመስራት አቅም ከመፈጠሩ በላይ አነስተኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ለማስፋት አስችሎታል፡፡
በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋለው ዕድገት፣ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱና የካፒታል ገበያ መቋቋም እንዲሁም የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭዎች በባንክ አገልግሎት ዘርፍ መሰማራት የሚፈጥሯቻን እድሎች በማጤን ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማምጣት እየሰራ መሆኑን የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ባደረጉት ንግግር አመልክተዋል፡፡
ዳሸን ባንክ ባለፈው ዓመት ፍላተርዌቭ ፣ ቱንስና ኤምኤፍኤስ ከተሰኙ በአፍሪካ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራርሟል። በግል የባንክ ኢንዱስትሪ ዘርፍም የመጀመሪያው የሆነውን ደረጃ 3 ግዙፍ የዳታ ማዕከል ያስገነባው ባለፈው በጀት ዓመት ነበር፡፡
ከ700 ባለይ ቅርንጫፎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመክፈት መደበኛና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለደንበኞቹ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

