የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአሜሪካው የጦርነት ሚኒስትር ፒት ሄግሴዝ ጋር በመሆን በወሰዱት ወታደራዊ እርምጃ 159 የኢራን የጦር መርከቦች በባህር ውስጥ መስጠማቸውንና ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቸውን አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ የኢራን የባህር ኃይል አቅም በከፍተኛ ደረጃ መዳከሙን በመጥቀስ ቀደሞቹ መሪዎች ለቴህራን ነፃነት ሰጥተው የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በአሜሪካ ኃይሎች አማካኝነት መርከቦቻቸው በባህር ስር እንዲቀሩ መደረጉን ገልጸዋል።
ይህ የፕሬዚዳንት ትራምፕ መግለጫ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የመገናኛ ብዙሃንና በፖለቲካው መድረክ ትልቅ ትኩረት ያገኘ ሲሆን «ከፍተኛ ጫና የማሳደር ስልት» ውጤት ማስገኘቱን የሚያሳይ እንደሆነ እየተገለፀ ይገኛል።
በሌላ በኩል ገለልተኛ የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኞችና ታዛቢዎች የተደምሰሱት መርከቦች ቁጥር በዋናነት የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባህር ኃይል የሚጠቀምባቸውን ትናንሽ ፈጣን ተዋጊ ጀልባዎችና የጥበቃ መርከቦች እንዲሁም ጥቂት ዋና የጦር መርከቦችን የሚያጠቃልል መሆኑን ያስረዳሉ።
የኢራን የባህር ኃይል አቅም አሁንም ሙሉ በሙሉ አልተደመሰሰም የሚሉ አስተያየቶች ቢኖሩም የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (CENTCOM) በመካከለኛው ምስራቅ የቀይ ባህርና የሆርሙዝ ወደብን የንግድ መስመሮች ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ በኢራን ወታደራዊ መሰረተ ልማቶች ላይ ያካሄደው ጥቃት በክልሉ ያለውን ወታደራዊ ሚዛን በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀየረው ይነገራል።

