ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትንያሁ ኳታርን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት የሃማስ ከፍተኛ ሰዎችን ለመግደል በሚል በኳታሯዋ መዲና ዶሃ የአየር ጥቃት ፈጽማ ኳታርን አስቆጥታ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኳታሩን አቻቸውን አል ታኒን ነው በይፋ ይቅርታ የጠየቁት፡፡ ከዚያ ጥቃት በኋላም እስራኤልንና ሃማስን ስታደራድር የቆየችው ኳታር የማሸማገል ስራዋን እንደምታቆመው ስትገልጽ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦቫል ኦፊስ ሆነው በስልክ ነው ይቅርታ ያቀረቡት፡፡ ኳታር የአሜሪካ ብርቱ ወዳጅ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በአየር ጥቃቱ የኳታሩ የደህንነት ሰው ሆን ተብሎ እንዳልተገደለም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ እስራኤል ያን መሰል ድርጊት እንደማታደርግም ቃል ገብተውላቸዋል፡፡ የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲህ አይነቱን ማረጋገጫ ማግኘታቸው መልካም እንደሆነ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
ከዚህ ባለፈ በዚያ ጥቃትም እስራኤል ኢላማ ያደረገችው የሃማስን ሰዎች እንጂ ኳታርን እንዳልነበረም ገልጸውላቸዋል ሲል ታይምስ ኦፍ እስራኤል አስነብቧል፡፡
የእስራኤል የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ግን በኳታር ላይ የተፈጸመው ጥቃት አስፈላጊ ነበር በማለት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ኳታርን ጠላት አገር ሲሉ ጠርተዋታል፡፡ አሁን እውቱን ለዓለም የምንናገርበት ጊዜ ነው፤ኳታር ሽብርተኞችን የምትደግፍና የምታበረታታ ናት ማለታቸው ተሰምቷል፡፡//

