ከኢራን ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት ገና አልተጠናቀቀም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔትንያሁ ገለጹ፡፡ ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርክ ሩቢዮ በኢራን ላይ የተጀመረው የኦፕሬሽን ኤፒክ ፉሪ መጠናቀቁን ገልጸው ነበር፡፡
ሚኒስትሩ የተያዙት ግቦች በመጠናቀቃቸው ዘመቻው እያበቃ ነው ካሉ በኋላ፤የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ትላንት እሁድ በሰጡት ኢንተርቪው ከኢራን ጋር የሚደረገው ጦርነት ገና አልተጠናቀቅም ብለዋል፡፡ የኢራኑን ጦርነት በተመለከተ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል በኩል እርስ በርስ የሚጣረሱ ንግግሮች እየተደመጡ ነው፡፡
በወዲያ በኩል ኢራን ጦርነቱን ስለማሸነፏ ስትናገር፤ወዲህ ደግሞ አሜሪካም ሆነች እስራኤል ተመሳሳዩን በማለት ዘልቀዋል፡፡ ነገር ግን መሬት ላይ ያለው ሀቅ የተጠናቀቀ ጦርነት እንደሌለ ማመላከቱን የፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትንያሁ በኢራን ውስጥ የምድር ዘመቻ ሊደረግ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሄዝቦላህ፡ሁቲ እና ሃማስ መጨረሻቸው ስለሚሆንበትም ሁኔታ ከሲቢኤስ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል፡፡
አሁንም ድረስ በኢራን እጅ ውስጥ የኒውክሌር ቁሶች አሉ፤ከዚህ በተጨማሪም በቀጠናው የኢራን እጅ በመሆን የሚያገለግሉት ሃይሎች አሁንም አሉ እናም ጦርነቱ ገና ነው ብለዋል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ የበለጸገ ዩራኒየም አሁም ቢሆን በኢራን ውስጥ አለ ይህ ሙሉ በሙሉ መወገድ ይኖርበታል፤ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይም ለእሱ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም አሜሪካ እና እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር አቅም ያዳከሙት ቢሆንም፤ሙሉ በሙሉ ግን ጠፍቷል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ በነበረው ጦርነት ናታንዝ፡ኤስፍሃን እና ፎርዶ የተሰኙት የኒውክሌር ጣቢያዎች መውደማቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕም በተደጋጋሚ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንደማትሆን ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡
ይህንን ዩራኒየም እንዴት አድርጋችሁ ለማስወገድ አስባችኋል በሚል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረበላቸው ጥያቄም ገብትን እናስወግደዋለን በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህም ንግግራቸው የእግረኛ ዘመቻ በቴህራን ውስጥ ሊደረግ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
ከኢራን ጋር ያለው ጦርነት በዚህ ወቅት ቢጠናቀቅ ከሄዝባላህ ጋር ያለው ጦርነት ይቀጥላል ወይ የሚል ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢቢ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኢራን የሚደርጉ ስምምነቶች በሙሉ ሊባኖስን እንዲያጠቃልሉ ትፈልጋለች፤እኛ ግን ሄዝቦላህ ጥቃቱን እስካላቆመ ድረስ ይህንን አንቀበለውም ብለዋል፡፡
ነገር ግን የአሁኑ የኢራን አገዛዝ ተዳከመ ማለት የሄዝቦላህ፡የሁቲ እና የሃማስም መጨረሻ ሆነ ማለት ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትንያሁ የአሁኑ የኢራኑ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ቀርበው ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ኔትንያሁ ይህንን ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ትራምፕን ወደዚህ ጦርነት ጎትተው ያስገቧቸው እርሳቸው ናቸው በሚል ለሚነሳው አሉባልታ ግልጽ ያለውን ለመናገር ነው ሲሉ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ በቆይታቸው ኢራን ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ሞት የምትመኘው ለአሜሪካም ጭምር ነው፤ትራምፕም ይህንን በሚገባ ይረዱታል ብለዋል፡፡//

