ፀሐይ ባንክ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ዘመናዊ የክፍያ አጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 70 ቅርጫፎች ካሉት ፀሐይ ባንክ ጋር በንግድ ግብይቱ የሚፈጸሙ ክፍያዎችን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት መፈጸሙን ተናግረዋል።
የምርት ገበያው 22 ምርቶችን በማገበያየት ላይ ሲሆን ዘንድሮ ተጨማሪ ምርቶችን ወደ ገበያ ስርዓቱ ማስገባቱን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ወንድማገኝ ነገራ ገልጸዋል።
ስምምነቱን የፀሐይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ መስፍን እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ በምርት ገበያው ዋና መስሪያ ቤት ሚያዝያ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ተፈራርመዋል፡፡
ከፀሐይ ባንክ ጋር የተደረገው ስምምነት ተገበያዮች ግብይቱን በፈጸሙ ማግስት ለአቅራቢዎች የሸጡበትን ገንዘብ በቀጥታ ከገዢው የባንክ ሂሳብ ወደ ሂሳባቸው ለማዞር የሚከናወነውን ሥራ ከማሳደጉም በላይ የክፍያ ስርዓቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍና ለማዘመን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
አቶ ያሬድ መስፍን በስምምነቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ፀሐይ ባንክ ወደ ሥራ ከገባ የአስር ወራት እድሜ ያለውና በአሁኑ ወቅት 70 ቅርንጫፎችን በተለያዬ የአገሪቱ ክፍሎች መክፈቱን ገልጸው፤ በእነዚህ ጊዜያት ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ደንበኞችን ማፍራት የቻለ ባንክ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ባንኩ በአጭር ጊዜያት በደንበኞች ዘንድ ያገኘውን ተቀባይነት በማሳደግ በምርት ገበያው ውስጥ ለሚሳተፉ ገዢና ሻጭ ደንበኞች አመቺ የመክፈያ ስርዓቱን በመዘርጋት ለግብይቱ መሳለጥ ፀሐይ ባንክ ከፍ ያለ ድርሻ እንደሚወጣ አቶ ያሬድ አስታውቀዋል፡፡
ፀሐይ ባንክ ለንግዱ ማህበረሰብና እንደ አጠቃላይ ለባንኩ ደንበኞች ዘመኑ የሚፈልገውን ዘመናዊ ግብይት በተሻለ መንገድ ለማስተናገድ የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ጨምሮ ቀልጣፋና ደንበኛ-ተኮር አገልግሎቶችን በመስጠት ተመራጭ ባንክ ሆኖ የማገልገል ራዕይን ሰንቆ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ በበኩላቸው፤ ፀሐይ ባንክ 22ኛው የክፍያ አጋር ባንክ መሆኑን ገልጸው፤ ምርት ገበያው ከባንኮች ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሰረት የሚሰጠው የክፍያ አገልግሎት አስተማማኝ የግብይት የክፍያ ስርዓት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ ላለፉት 15 ዓመታት አንድም ቀን ተስተጓጉሎ አያውቅም ብለዋል፡፡
የምርት ገበያው ተጨማሪ ምርቶችን ወደ ግብይት ስርዓቱ በማስገባት፤ የወደፊቱን ግብይት ሥራ ላይ በማዋልና የመጋዘንና የጥራት ተጨማሪ አገልግሎቶች በማካሄድ ተጨማሪ ኦፕሬሽናል ሥራዎችን እያካሄደ መሆኑን አቶ ወንድማገኝ አስታውቀዋል፡፡
ግብይቶቹና አገልግሎቶቹ ህጋዊ የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ስለሚያልፉ ፀሐይ ባንክን ጨምሮ ከምርት ገበያው ጋር የሚሰሩ ባንኮችን የደንበኞቻቸውን ቁጥር እንዲያሳድጉና የአገልግሎት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ እንደሚረዳቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያገበያያቸው ምርቶች ብዛት 22 የደረሰ ሲሆን ባለፉት 15 ዓመታት በምርት ገበያው አማካይነት ለግብይት የተከፈለው የገንዘብ መጠን ከ350 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑን ከምርት ገበያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
ፀሐይ ባንክ እና ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ያደረገውን የዘመናዊ ክፍያ አጋርነት ስምምነት ተከትሎ ባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች የምርት ገበያውን እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡
የፀሐይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ መስፍን እና ሌሎች የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

