የትምህርት ቤት ሁኔታዎችን እና የመኖሪያ ውድነትን በመቃወም የተጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ከፍተኛ ብጥብጥ እና ዘረፋ አድጓል።
ከፍተኛ ሁከቱ የተጀመረው ከወራት በፊት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበር። ተማሪዎቹ የፈራረሰ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የተጨናነቁ የክፍል አዳራሾች፣ የመምህራን እጥረት እና የበጀት እጥረት አቤቱታዎችን በማሰማት ነበር።
የኑሮ ውድነት እና የነዳጅ ዋጋ ንረት ህዝቡን ክፉኛ በመፈታተኑ የሀገር ውስጥ የሰራተኛ ማህበራት፣ አርሶ አደሮች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተማሪዎችን እንቅስቃሴ መቀላቀላቸው ቀውሱን አባብሶታል።
ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በመላው ፈረንሳይ በተደረጉ ወደ 110 የሚጠጉ ሰልፎች ላይ ሲገኙ፣ የሰራተኛ ማህበራት በበኩላቸው የተሳታፊዎችን ቁጥር እስከ 800,000 አድርሰውታል።
ህገ-ወጥ ዘራፊዎች እና ሁከቱን እንደ ሽፋን በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱቆችን አውድመዋል። በሊሞዥ ከተማ የሚገኝ የከተማ አስተዳደር ህንፃ በእሳት ወድሟል። ማርሴይ በተባለችው ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ደግሞ የመንግስት ህንፃዎች ተሰብረዋል።
በመላው ሀገሪቱ 1,500 ገደማ ሱቆች መውደማቸው ተገልጿል፤ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች በፖሊስ ተይዘዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲታሰሩ፣ ከ1,000 በላይ የጸጥታ አስከባሪዎች፣ ተማሪዎች እና የትምህርት ቤት ሰራተኞች ቆስለዋል። በተለይም በፖሊስ አስለቃሽ ቦምቦች ምክንያት የሁለት ታዳጊዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ከፍተኛ ምርመራ አስከትሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲያን ሌኮርኑ ሁከቱን አጥብቀው አውግዘዋል፤ ጽንፈኛ የግራ አክራሪ ፓርቲዎች በወጣቶች ላይ የተሳሳተ አመለካከት በመዝራት ለሁከቱ መባባስ ምክንያት ናቸው ሲሉ ከሰዋል።
የግራ ዘመሞ ፓርቲ መሪ በበኩላቸው፣ የመንግስት ብቃት ማነስ ለዚህ ቀውስ ዋና ምክንያት ነው በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተችተዋል።
ይህ በፈረንሳይ የተከሰተው ታላቅ ህዝባዊ ተቃውሞ የአገሪቱን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መሠረት ያናወጠው ሲሆን፣ በቀጣይ በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።//
ፈረንሳይ ከዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ትልቅ ህዝባዊ ተቃውሞ እና ሁከት እየተናጠች ነው

