ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዘለንስኪ ጋር ለመገናኘት ፈቃደኛ መሆናቸውን በቤጂንግ በነበራቸው ቆይታ ገለጹ፡፡ ፑቲን ዘለንስኪ ወደ ሞስኮ ለመምጣት ከፈቀደ ለመገናኘት ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ፑቲን ትራምፕ ሁለታችን እንደንገናኝ ጠይቀውኛል፤በርግጥ ዘለንስኪም ከእኔ ጋር ለመገናኘት መቃደኛ መሆኑን አውቃለሁ፤ወደ ሞስኮ መምጣት ከቻለም ይህ የተጠየቀው ንግግር መካሄድ ይችላል ብለዋል፡፡ የደህንነት ሰዎች ግን የዘለንስኪ ወደ ሞስኮ መጓዝ መዘዝ እንዳለው በመግለጽ እያስጠነቀቁ ነው፡፡
ዘለንስኪም ወደ ሞስኮ ይሄዳሉ ተብሎ አጠበቅም፡፡ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ይህንን የፑቲንን ጥሪ ውድቅ እንዳደረገው ይፋ አድርጓል፡፡ ክሪሚሊን በበኩሉ ፑቲን ዘለንስኪን ወደ ሞስኮ የጋበዙት ለውይይት እንጂ እጁን እንዲሰጥ አይደለም ብሏል፡፡ የፑቲን ሃሳብ ይህ ነው ያሉት ፔስኮቭ ሞስኮ ዘለንስኪ ሃሳቡን ውድቅ እንዳደረገ ተመልክታለችም ብለዋል፡፡
ፑቲን ረቡዕ እለት በሰጡት መግለጫቸው ለዩክሬን ጦርነቱን ለመቋጨት ሁለት ምርጫ አሉሽ ብለዋል፡፡ የመጀመሪያው ንግግር ሲሆን ይህ ካሆነ ደግሞ ፑቲን በሃይል ጦርነቱን እንደሚያጠናቅቁት በግልጽ ተናግረዋል፡፡
የኔ ምርጫ ግን ከሃይል ይልቅ ንግግር ነው ብለዋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የመሪዎቹ ንግግር እንዲደረግ የሚፈልጉት ገለልተኛ ናቸው ባሏቸው እንደ ቱርክ እና ኦስትሪያ ባሉ አገራት ነው፡፡ ክሪሚሊን ግን ይህንን የፕሬዝዳንቱን እቅድ በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደርገው ቆይቷል፡፡
በዚህ ሳምንት ፑቲን በቻይና ነው ያሳለፉት፡፡ መጀመሪያ የሻንጋይ የትብብር ድርጅት ጉባኤን ለመሳተፍ በቲያንጂን የወደብ ከተማ የነበሩ ሲሆን ቀጥለውም የቻይናን ወታደራዊ ትዕይንት ለመታደም ወደ ቤጂንግ ተጉዘው ነበር፡፡
ባለፈው ወር ትራምፕ ፑቲንን በአላስካ ማግኘታቸው እና ከዚያ በኋላ ደግሞ ዘለንስኪ ከአውሮፓ አገራት መሪዎች ጋር ወደ ዋይት ሐውስ ማቅናታቸው ይታወሳል፡፡
በዚያን ወቅትም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዘለንስኪን እና ፑቲን ለማገናኘት የሁለት ሳምንት ቀነ ገደብ አስቀምጠው ነበር፡፡ ያ የጊዜ ቀነ ገደብ ግን አሁን አልቋል፡፡
በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሚመራው የ30 አገራት ጥምረት የደህንነት ዋስትና ለዩክሬንና ለዩክሬናዊያን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 30 የሚሆኑት የአውሮፓ አገራት ጥምረት የሰላም ስምምነት እስከሚፈረም ድረስ ለዩክሬን ድጋፋችንን እንደምቀጥል በዋሽንግተን በነበረን ቆይታ የተስማማንበት ነው ሲሉ ኢማኑኤል ማክሮን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ የአውሮፓ አገራት የደህንነት ዋስትና ለዩክሬን የሚሰጡት የዩክሬን የምድር ጦር እንዲጠናከር በማድረግ፡የዩክሬንን አየር ክልል ከስጋት የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ እና የዩክሬን ወደብና ባህር የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግን ያካተተ ነው፡፡
ኔቶም ጠንካራ የደህንነት ዋስትና ለኬቭ መስጠት ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነ ገልጻል፡፡//

