2ኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይራዘም ተገለጸ

የሕዳሴው ግድብ አጠቃላይ ግንባታ 78.8 በመቶ እንደደረሰ ተገልጿል!

የሕዳሴ ግድቡን ማጠናቀቅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ጭምር መሆኑን አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል

የሕዳሴ ግድብ 10ኛ ዓመትን በማስመልከት በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ አስተባባሪነት በግድቡ ድርድር ላይ የተሳተፉ እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተገኙበት ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው፡፡

ሲምፖዚየሙን በንግግር የከፈቱት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን “ዓባይን ማልማትና የሕዳሴ ግድቡን ማጠናቀቅ ለነገው ትውልድ ከመስራት በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማረጋገጥም ጭምር ነው” ብለዋል፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፣ በቀጣዩ ክረምት ቀጠሮ የተያዘለት 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይራዘምና ለዚያ የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የሕዳሴው ግድብ አጠቃላይ ግንባታ 78.8 በመቶ እንደደረሰ የግድቡ ፕሮጄክት ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ክፍሌ ሆሮ መግለጻቸውም ተጠቁሟል፡፡

በሲምፖዚየሙ የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም የሶስትዮሽ ድርድሩ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ገለጻ እና ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

ግብፅ እና ሱዳን አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ የግድቡ ሁለተኛ የውሃ ሙሌት መከናወን እንደሌለበት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ በቅርቡ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ያደረጉት ሀገራቱ ፣ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ተመድም በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ በመጋበዝ የግድቡን ድርድር ጉዳይ ዓለማቀፋዊ ገጽታ ለማላበስ አቅደዋል፡፡ ሱዳን ለተጠቀሱት ዓለማቀፍ አካላት በይፋ የአደራድሩን ጥያቄም አቅርባለች፡፡

ይሁን እንጂ ስለዚህ ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ለአዲስ አበባ የደረሰ ጥያቄ አለመኖሩን የገለጸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ የድርድሩ ጉዳይ ከአፍሪካ ሕብረት አቅም በላይ እንዳልሆነ ጠቅሷል፡፡ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ አደራዳሪ እንደማትሻም በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ በድርድሩ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት ላይ የመድረስ ፍላጎትም የላትም፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe