ትግራይ ፡ ጥቅምት 30 ሰኞ ዕለት በማይካድራ ከተማ የተከሰተው ምን ነበር?

በአካባቢው ለአንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ ስለነበረ ቢቢሲ በከተማዋ የሚኖሩ ሰዎችን ለማናገር ሳይችል ቆይቷል። አሁን ግን በአካባቢው የስልክ አገልግሎት በከፊል በመጀመሩ የከተማዋን ነዋሪዎችን ስለክስተቱ ለማናገር ችለናል።

ጥቃቱ ጥቅምት 30/ 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ 9፡ 00 ሰዓት ላይ የነበረ ሲሆን አስከሚቀጥለው ቀን ጠዋት ድረስ መቀጠሉን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።ወ/ሮ ትርፋይ ግርማይ የትግራይ ተወላጅ ሲሆኑ ከአማራው ባላቸው ጋር ትዳር መስርተው በማይካድራ ከተማ ውስጥ መኖር ከጀመሩ 12 ዓመታትን እንዳስቆጠሩ ይናገራሉ። አንዲትም ልጅ አለቻቸው። ባለቤታቸው በተለያዩ የግብርና ሥራዎችን በማከናወን የወይዘሮ ትርፋይን እናት ጨምሮ የመላው ቤተሰቡን ሕይወት ለመምራት የሚስችለው ዋነኛ የቤተሰቡ የገቢ ምንጭ ነበር።

በትዳር ውስጥ በቆዩባቸው 12 ዓመታት ውስጥ እንደአሁኑ ጥቃት ታይቶ እንደማያውቅ ያስታውሳሉ።ባለቤታቸውና የቤተሰባቸው አስተዳዳሪ አይናቸው እያየ ከቤታቸው ደጃፍ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ይናገራሉ። “ባለቤቴ ምንም የሚያስገድል ወንጀል አልሰራም፤ የተገደለው አማራ በመሆኑ ነው” ይላሉ ወይዘሮ ትርፋይ።

የጤና ችግር እንዳለባቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ትርፋይ፣ ባለቤታቸውን በዚያ አሰቃቂ ሁኔታ በማጣታቸው ቀጣይ ህይወታቸው መመሰቃቀሉን ይናገራሉ። እናታቸውን እና ልጃቸውን ለማስተዳደር ምን መስራት እንዳለባቸውም ግራ መጋባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የማይካድራ ነዋሪ የሺ ላቀም ባለቤቷን በተመሳሳይ ሁኔታ ማጣቷን ታስረዳለች። የነበረውን ሁኔታ ስታስታውስ “መጀመሪያ ቤታችሁን ዝጉ አሉን፤ ከዚያ ሁለተኛ መጥተው ቤታችንን እየከፈቱ ወንዶቹን መርጠው እየወሰዱ ገደሏቸው” በማለት በምሬት ትናገራለች።

የጥቃቱ ዕለት ባለቤቷ የትም እንዳልሄደ የምታስታውሰው ወ/ሮ የሺ፣ “ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ በቡድን የተሰባሰቡ ወጣቶች መጥተው ባለቤቴንና የባሌን ወንድም ከቤት በማስወጣት ገደሏቸው” ብላለች።

“ባለቤቴን ተውልኝ ብላቸውም አንቺን ነገ አይቀርልሽም፤ ዛሬ የምፈልገው ወንዶችን ነው በማለት እኔ እና ልጆቼ እያየን ገደሏቸው” በማለት የባሏን ሞት ያየችበትን አጋጣሚ ገልጻለች።

“በወቅቱ እኔንም አንዳንዶቹ ‘በላት’ እያሉ ሌሎቹ ደግሞ ገላግለው አተረፉኝ” ያለችው የሺ ከዚያ በኋላ ወደ ቤት ገብተው አንዳንድ ነገሮችን ዘርፈው እንደወሰዱ ትናገራለች።

ወ/ሮ የሺ ከባለቤቷ አየነው ሙላት ጋር ከ10 ዓመታት በላይ በትዳር ኑረዋል። ሁለት ልጆችንም አፍርተዋል። ልጆቻቸውም አባታቸው ሲገደል በቦታው ስለነበሩ አሁን “ሕጻኗ ልጄ ታስቸግረኛለች፤ ሌሊት እየተነሳች ‘አባቴ የት አለ’ እያለች ትፈልጋለች፤ ይህም ሌላ ችግር ፈጥሮብኛል” በማለት አሁን ያለችበትን ሁኔታ ታብራራለች።

የባሌን አሟሟት እያሰብኩ “ኑሮን እንዴት መምራት እንዳለብኝም ለማሰብ ሞራሉ የለኝም፤ ልቤ ተሰብሯል። የነበረው ሁኔታ በጣም ከባድ ተብሎ የሚገለጽበት አይደለም” ትላለች።አቶ ጥላሁን አታላይ ነዋሪነቱ በማይካድራ ግምብ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። “በዕለቱ [ጥቅምት 30] ማሽላ ለማስቆረጥ ስንሰናዳ 7፡00 ሰዓት አካባቢ በቡድን ወደቤታችን በመምጣት መታወቂያ ጠየቁን” በማለት የክስተቱን አጀማመር ያስረዳል። “ይህም ብሔራችንን ለመለየት ነበር።”

“ከቀኑ 8፡00 ላይ ወጣቶቹ በከተማዋ ውስጥ እንደሰልፍ ነገር አደረጉ፣ ከዚያ ግን ሰልፉን ሰበብ አድርገው ጥቃቱን ጀመሩ።”

ወዲያውም ወደ እነሱ ቤት ሲመጡ “እኛም ሴትና ህጻናትን አያጠቁም የሚል መረጃ ስለሰማን እኔና ወንድሜ ኮርኒስ ላይ ወጣን። ሲያጡን ተመልሰው ሄዱ። ተመልሰው 11፡00 ሰዓት ላይ መጡ እና ድጋሚ ቤቱን ፈተሹ፤ አሁንም እኛ ከኮርኒሱ ስላልወረድን የወንድሜን ሚስት አስፈራርተው ባልሽን ካላመጣሽ እንገድልሻለን በማለት ገልጋይና ተገልጋይ ሆነው ተመልሰው ሄዱ” ይላል።

አስደንጋጩ ነገር የተከሰተው ግን ከምሽቱ 1፡30 ነው። ሁለት ጊዜ ወደ ቤት መጥተው አንድም ወንድ ሳያገኙ የተመለሱት ወጣቶች የእነ ጥላሁንን ቤት ለመፈተሽ ለሦስተኛ ጊዜ ምሽት 1፡30 ሰዓት ላይ ተመልሰው መጡ።

“በዚህ ጊዜ የወንድሜን ባለቤት ከቤት አስወጥተው ‘ባልሽ የት እንዳለ የማትናገሪ ከሆነ አንችን እንገድልሻለን’ ብለው ጩቤ አወጡ። በቃ ግደሉኝ ስትላቸው ‘እንዲያውም ከአንቺ በፊት ልጅሽን ነው የምንገድለው’ ብለው ልጁን ሊወስዱት ሲዘጋጁ ከልጄ በፊት እኔን ግደለኝ ብላ እርሷ ተጠጋች” በማለት በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ይገልጻል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ጥላሁን ከወንድሙ ጋር ኮርኒስ ውስጥ ተቀምጠው የሚሆነውን ይከታተሉ ነበር።

ባለቤቱን ሊገድሏት ሲሉ ግን ወንድሙ ሁኔታውን መቆጣጠር አለመቻሉን ይገልጻል። “ይህንን ወንድሜ ሲያይ ‘እኔ ቁሜ አስከሬን አልቆጥርም’ ብሎ ወርዶ ወደ እነሱ ሄደ። ከዚያም በያዙት ነገር ሁሉ ሲደበድቡት ባለቤቱ ጩኸት አሰማች፤ እሷንም ትካሻዋ ላይ መትተው አቆሰሏት” በማለት ይህንን ግድያ ለማምለጥ ሰዓታትን አብሮት ኮርኒስ ላይ ተቀምጦ የነበረው ወንድሙን ያጣበትን ክስተት ያስታውሳል።

በወቅቱ የነበረውን የሰው ብዛት ሲገልጽ “የሳምሪ ወጣቶች በሙሉ ነው የመጡት፣ ቁጥራቸው ከ150 በላይ ይሆናል። ጥቃቱን ሲፈጽሙ የታጠቁ ሚሊሻ እና ፖሊሶች አብረዋቸው ነበሩ” ብሏል።

በወቅቱ ከግድያ በተጨማሪ ዝርፊያም መከሰቱን የሚናገረው ጥላሁን፤ ወንድሙ ከቀናት በፊት ሰሊጥ ሸጦ ባንክ ዝግ ስለነበር በጥሬ 90 ሺህ ብር በቤት ውስጥ አስቀምጦ ነበር። ያንን ብርም እነዚህ ወጣቶች መውሰዳቸውን ገልጿል።

ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለበት ማይካድራ ከሁመራ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ ትገኛለች
የምስሉ መግለጫ,ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለበት ማይካድራ ከሁመራ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ ትገኛለችወይዘሮ ሃዳስ መዝገቡም ማይካድራ ውስጥ ግምብ ሰፈር ነው የምትኖረው። ከባለቤቷ ብርሃኑ ጋር በትዳር ተጣምረው 17 ዓመታትን በመኖር ሦስት ልጆችን አፍርተዋል። የማይካድራው ግድያ ሲፈጸም በጅምላ ከተገደሉት መካከል አንዱ የእርሷ ባል ነው።

“ከቀኑ 6፡00 መጥተው ሲም ካርድ እና መታወቂያ ለዩ። በ9፡00 ግድያው ተፈጸመ” ያለችው ወ/ሮ ሃዳስ “በአካል የምናውቃቸው ሚሊሻዎችና የሳምሪ ልጆች ናቸው ግድያውን የፈጸሙት” ትላለች። ሌሎች ደግሞ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሰዎች ላይ የሚጠቁሙ ግለሰቦች እንደነበሩ ገልጻለች።

“ባሌ ሚሊሻ ነበር፤ ትጥቁን አስወርደው ነው የገደሉት” የምትለው ሃዳስ “ፍተሻውን ለማድረግ የወሰኑት ያለውን የሰው ብዛት ለማወቅ ነው። ባለቤቴ እና የእህቱ ልጁ ተገድለዋል” በማለት አሰቃቂውን ድርጊት ታስረዳለች።

ከተገደሉት የቤተሰቧ አባላት በተጨማሪ የሟች ባሏ የአጎት ልጅ ደግሞ ቆስሎ ጎንደር ህክምና ላይ እንደሚገኝ የተናገረችው ሃዳስ “በማግስቱ ተረኞቹ ሟቾች እኛ ነበርን፣ ነገር ግን መከላከያ ደረሰልን። የሞቱት ሰዎች ከሦስት ቀን በኋላ በኅዳር 2 ነበር የተቀበሩት” ብላለች።

አቶ ገብረ መስቀል መንግሥቱ ደግሞ ነዋሪነታቸው በማይካድራ ከተማ ሲሆን በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው ኑሯቸውን ይመራሉ። በማይካድራ ግድያ ሲካሄድ በቦታው እንደነበሩና ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ተከታትለዋል።

እንደአቶ ገብረ መስቀል ገለጻ ከግድያው በፊት በርካታ ወጣቶች በትራክተር 40 እና 50 እየሆኑ ወደ አንድ ቦታ ሲሰባሰቡ መመለክታቸውን ይገልጻሉ።

በወቅቱም ሌላው ነዋሪ ስለሁኔታው ምንም የሚያውቀው ነገር ስላልነበረ አንዱን ሰው ከቤቱ አስወጥተው ሲገድሉ ሌላው “ምን እየሆነ ነው ብሎ ከቤቱ ሲወጣ እዚያው ይጨምሩታል” በማለት የሁኔታውን አጀማመር ያስረዳል።

ጥቃቱ ከቀኑ ሰኞ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም 9 ሰዓት ላይ መጀመሩን የሚገልጹት አቶ ገብረ መስቀል እንደሚሉት ጥቃቱ መጀመሪያ ላይ የተፈጸመው በከተማው በነበሩ የጉልበት ሠራተኞች ላይ ነበር።

“ድብደባው ሲፈጸም እነሱን [የጉልበት ሠራተኞቹን] ገድለው ሲጨርሱ ወደ እኛ ለምመምጣት ነበር፤ እነሱን መጀመሪያ መግደል የፈለጉበት ምክንያትም ለእኛ ድጋፍ ለመስጠት እንዳይመጡ ነው” ይላል።

የቀን ሠራተኞች በአንድ አካባቢ ተሰባስበው ይኖሩ ስለነበር “ከአንድ ቤት እስከ 20 ሬሳ ተሰብስቧል” ያሉት አቶ ገብረመስቀል እስከ ቅርብ ቀን ድረስ ቆይተው የተገኙ አስከሬኖችን ሲቀብሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ከዚህ አሰቃቂ ጥቃት በፊት “እንደዚህ የከፋ ባይሆንም አልፎ አልፎ ችግሮች በከተማዋ ይከሰቱ” እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ገብረመስቀል “ይህ ግን ያልጠበቅነው መአት ነበር” ይናገራሉ።

አሁን በከተማዋ ያለው ስሜት በጣም ይከብዳል፤ ሰው ተረብሿል። በርካቶች ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ በማየታቸው ያንን መርሳት ከባድ እንደሆነባቸው አቶ ገብረመስቀል ይናገራሉ።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመግባባት ተካሮ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ነበር በማይካድራ ከተማ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ የተሰማው።

ጥቃቱን በማስመልከት በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ የተለያዩ አሰቃቂ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች መሰራጨታቸውን ተከትሎ አምነስቲ ኢንትርናሽናል ባደረገው ማጣራት በማይካድራ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጅምላ ግድያ መፈጸሙን የሚገልጽ ሪፖርት አውጥቶ ነበር።

በማስከተልም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በከተማዋ ውስጥ በተፈጸመ ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት ቢያንስ 600 ሰዎች እንደተገደሉና በድርጊቱ ውስጥም ‘ሳምሪ’ የተባለው መደበኛ ያልሆነ የወጣቶች ቡድንና የአካባቢው ፖሊስና ሚሊሻ እጃቸው እንዳለበት አመልክቷል።

የፌደራል መንግሥቱም በማይካድራ ለተፈጸመው ጅምላ ግድያው የህወሓት አመራርን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፤ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ግን ውንጀላውን “መሰረተ ቢስ” በማለት ጥቃቱ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጥሪ አቅርበው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሚሸል ባሽሌት ጭፍጨፋውን በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ “የግድያው ድርጊት በምርመራ ከተረጋገጠ እንደጦር ወንጀል የሚቆጠር ነው” ነው ሲሉ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው። ?BBC/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe