32 ያህል የፌደራል መስሪያ ቤቶች ፈረሱ፤ የሰራተኞቹ ዕጣ ፈንታ አልታወቀም፤

ዛሬ ይፋ የሆነው የአስፈፃሚ አካላትን መልሶ ስለማደራጀት የሚደነግገውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው አዋጅን ተከትሎ 32 ያህል የፌደራል መስሪያ ቤቶች ስለመታጠፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለምክር ቤቱ አስታወቁ፡፡

የታጠፉና እርስ በእርስ የተዋሃዱት ሰራተኞች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ያላብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከበጀትና ከሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በርካታ መስሪያ ቤቶችን የማጠፍ ውሳኔ ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡ በታጠፉት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ስላሉት ሰራተኞች ጉዳይ የምክር ቤት አባላት አንድም ጥያቄ ያለማንሳታቸው የዕለቱ መነጋጋሪያ መሆኑን ቁም ነገር መፅሔት ተረድታለች፡፡

የታጠፉት መስሪያ ቤቶች ቀደም ሲል በአዋጅ ተሰጥቷቸው የነበረው መብትና ግዴታቸው ወደ አዳዲሶቹ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች እንደሚተላለፍ ዛሬ በፀደቀው አዋጅ ላይ ተመልክቷል፡፡በዚህም መሠረት፡-

 • የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣንና የምርት ገበያ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ፈርሰው አዲስ በተቋቋመው ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስር የገቡ ሲሆን
 • በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስር የነበረው ቱሪዝም ኢትዮጵያ ፈርሶ መብትና ግዴታዎቹ ለቱሪዝም ሚኒስቴር ተሰጥቷል፡፡
 • የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፤የፌደራል ከተሞች ስራ አዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ፈርሰው መብትና ግዴታዎቻቸው አዲስ ወደ ተቋቋመውና በወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ወደሚመራው የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ተላልፏል፡፡
 • የፌደራል ትራንስፖርት ባለስጣልን ፈርሶ መብቱና ግዴታዎቹ አዲስ ለተቋቋመውና በወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ለሚመራው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ተላልፏል፡፡
 • የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፤የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባባሪያ ኤጀንሲ፤ የፌደራል ከተሞች መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የፈረሱ ሲሆን መብትና ግዴታዎቻቸው አዲስ ለተቋቋመው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ተላልፏል፡፡
 • የውሃ ልማት ኮሚሽን፤የተደፋሰሶች ልማት ባለስልጣንና የውሃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት የፈረሱ መስሪያ ቤቶች ሲሆኑ መብትና ግዴታዎቻቸው ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተላልፏል፡፡
 • የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ፈርሰው መብትና ግዴታቸው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ለሚመሩት ትምህርት ሚኒስቴር ተሰጥቷል፡፡
 • ሀገር አቀፍ የኤችእቪ/ኤድስ መከላካያና መቆጣጠሪይ ጽሕፈት ቤት የፈረሰ ሲሆን ስራው ለጤና ሚኒስቴር ተሰጥቷል፡፡
 • በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ስም የተሰየመው የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ፈርሶ መብትና ግዴታዎቹ ለአቶ ቀጀላ መርዳሳ ለሚመሩት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተሰጥቷል፡፡
 • የእንስሳት መድሃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ፈርሶ መብትና ግዴታዎቹ አዲስ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ተሰጥቷል፡፡
 • ብሔራዊ የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታ መቆጣጠሪያና ማጥፊያ ኢንስትቲዩት ፈርሶ መብቱና ግዴታዎቹ ለእንስሳት ጤና ኢንስትቲዩት ተሰጥቷል፡፡
 • ብሔራዊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስትቲዩቲ እና የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ፈርሰው መብታና ግዴታዎቻቸው በአዋጁ ለተቋቋመው የእንስሳት ልማት ኢንስትቲዩት ተላልፏል፡፡
 • የኢትዮጵያ አፈር ሀብት ኢንስትቲዩትና የኢትዮጵያ ግብርና ሴክቴሪያት ፈርሰው መብትና ግዴታዎቻቸው በአዋጅ ለተቋቋመው አዲስ መስሪያ ቤት ለግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት  ተላልፏል፡፡
 • የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ ፈርሶ መብቱ ለኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ባለስልጣን ተላልፏል፡፡
 • የምግብና የመጠጥ ፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስትቲዩት፤ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩትና የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት እንዲሁም የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስትቲዩት ፈርሰው መብትና ግዴታዎቻቸው በአዋጁ ለተቋቋመው የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት መተላለፉ ተገልጧል፡፡
 • የነዳጅና ነዳጅ አቅርቦት ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን እና የኢነርጂ ባለስልጣን ፈርሰው ወደ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን መብትና ግዴታዎቻቸው መተላለፉ አዋጁ ይደነግጋል፡፡
 • የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩትና የኬሚካል ኮንስትራክሽን ግብኣት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት የፈረሱ ሲሆን መብትና ግዴታዎቻቸው አዲስ ወደ ተቋቋመው የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ተላልፈዋል፡፡
 • የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና ጂኦፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስትቲዩት ፈርሰው ስፔስ ቴክኖሎጂ እና ጂኦፓሻል ኢንስትቲዩትን ፈጥረዋል፡፡
 • የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለስልጣን የፈረሰ ሲሆን መብትና ግዴታዎቹ አዲስ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ተላልፈዋል፡፡
 • የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስትቲዩት እና የስትራቴጂክ ጉዳዮች ኢንስትቲዩት ፈርሰው መብትና ግዴታዎቻቸው በአዋጁ ለተቋቋመው የውጭ ግንኙነት ኢንስትቲዩት ተላልፈዋል፡፡
 • የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ እና የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስትቲዩት ፈርሰው መብትና ግዴታዎቻቸው ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስትቲዩት ከተሰጡት መስሪያ ቤቶች መሀከል ይገኛሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe