ኢሳያስ መብራቱ ይባላል፤ 46 ዓመት ጎልማሳ ነው፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ከምሽቱ 2፡30 አካባቢ ከአዲስ አበባ ወደ ካናዳ ቶሮንቶ ለመጓዝ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የውጭ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ሁለት አውሮፕላን ለመሳፈር ደርሷል፤
ኢሳያስ ወደ አውሮፕላን ከመግባቱ በፊት የያዛቸውን ሻንጣዎች በፍተሻ ማሽኑ ውስጥ እንዲያሳልፍ ሲጠየቅ ያልምንም ማመንታት ነበር ሻንጣዎቹን የጫነው፤ እናም ሻንጣዎቹ በማሽኑ ውስጥ ሲያልፉ በምስል ማሳያው ሰሌዳ ላይ አንዳች እንግዳ የተጠቀለለ ነገር ለፍተሻ ሰራተኞቹ ያሳይ ነበር፤ወዲያው ሻንጣውን ከፍቶ እንግዳውን ነገር እንዲያሳይ ሲጠየቅ የጉምሩክ አዋጅን የሚተላለፍ 40 ሽህ ብር የሚያወጣ ጫት በሻንጣው ውስጥ ተገኘ፤
በትልቅ ኮምፎርት ብርድ ልብስ ተጠቅልሎ የተገኘው 29 ኪሎግራም የሚመዝነውን ጫት እንደተገኘ ምነው አለው ፖሊስ;
የኢሳያስ ምላሽ ግን ግልጽና አጭር ነበር፤
‹“ጫቱን የያዝኩት ለንግድ ሳይሆን ከጓደኞቼ ጋር ልቅመው አስቤ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ጫት ይዞ መገኘትና መቃም ክልክል ስላልሆነ ጫት ከሀገር ይዤ ብወጣ አይከለከልም ብዬ በማሰብ ነው ” ሲል ቃሉን የሰጠ ፤
ፖሊስ ጊዜ ሳያጠፋ ኢሳያስን ከጉዞው አስቀርቶ ወደ ማረፊያ ቤት ላከው፡፡ በማግስቱም አቃቤ ህግ የክስ መዝገብ አዘጋጅቶ ፍርድ ቤት አቆመው፤
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አቶ ኢሳያስ መብራቱ የተባለው ተከሳሽ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀፅ 168/1 እና የአየር መንገድ ተጓዦች ከኢትዮጵያ ይዘው መውጣት የሚችሉትን የተለያዩ የግብርና ምርቶችና የፋብሪካ ውጤቶች መጠን ለመወሰን የወጣ መመርያ ቁጥር 008/2007 አንቀፅ 62.1 ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ድርጊቱን ፈፅሟል ሲል ለፍርድ ቤቱ አቤት ይላል፤
በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ለተከሳሽ ክሱ ሲያነብለት ክሱን ሳይቃወም ‹በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን በፍፁም አላውቅም ” ሲል ቃሉን የሰጠ ፤
ፍርድ ቤቱም ‹ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም› የሚለውን የተለመደ የህግ አንቀፅ ከጠቀሰ በኋላ 35 ሽህ ብር የገንዘብ ቅጣት በመጣል ለሚቀጥሉት 4 ዓመታት ኑሮህን በእስር ቤት ይሁን ብሎታል፡፡

