አራት ኪሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ህንፃ በአካባቢው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚገነባው የህዝብ ቤተመፅሀፍት ህንፃ ግንባታ በሚል ሊፈርስ እንደሆነ ተሰማ፡፡
ከሰማኒያ ዓመት በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በፋሽሽት ጣሊያን ወረራ ወቅት ታላላቅ ገድል ለሰሩ አባት አርበኞች መታሰቢያ እንዲሆን በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተቋቋመ ሲሆን አርበኞችንና የአርበኛ ቤተሰቦችን መብቶችና ጥቅም ለማስከበር በሚል ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወሳል፡፡
<የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አሥር አመራሮችን ከኃላፊነት ያነሳበት መንገድ ጥያቄ…>
ማህበሩ አቅመ ደካማ የሆኑ አባትና እናት አርበኞች ቤተሰቦችን ገቢ ለመደገፍ ህንጻ አገንብቶ እያከራየ በሚያገኘው ገቢ የሚተዳደር ሲሆን አሁን ከሚጠቀምበት ህንጻ በተጨማሪ አስር ያህል ኮንዶሚኒየም ቤቶች ከመንግስት ተሰጥቶት በማከራየት ገቢ እንደሚያገኝ ይታወቃል፡፡ አራት ኪሎ የሚገኘው የአርበኞች ህንጻ ባለ አራት ፎቅ ሲሆን በአካባበው በተጀመረው የህዝብ ቤተ መፅሐፍት ግንባታ ጋር በተያያዘ ቦታው ለማስፋፊያነት ስለሚፈለግ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ለማፍረስ በቀድሞው አዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ተወስኖ የተፈረመበት ደብዳቤ በአሁኗ ምክትል ከንቲባ ጠረጴዛ ላይ እንደሚገኝ ምንጮች አመልክተዋል፡፡
የማህበሩ ህንፃ ሲፈርስ ሌላ ምትክ ቦታም ይሁን የህንጻ መስሪያ ገንዘብ የከተማ አስተዳደሩ ለማህበሩ ስለመስጠቱ የታወቀ ነገር የለም ተብሏል፤ በዚህ ዓመት የከተማ አስተዳደሩ በያዘው የ2013 በጀት ዝርዝር ውስጥ የአርበኞች ህንጻ ካሳ ጉዳይ በጀት እንዳልተያዘለትም ታውቋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተጠይቀው ስለተባለው የመስተዳድሩ እቅድ የደረሳቸው መረጃ እንደሌለ ገልፀው የማህበሩ ህንጻ ታሪካዊ በመሆኑና አራት ኪሎ ከሚገኘው የድል ሀውልት ጋር የተቆራኘ ታሪክ ያለው በመሆኑ መስተዳድሩ ህንፃውን ያፈርሰዋል የሚል እምነት እንደሌላቸውና ቦታው የሚፈለግ ቢሆን እንኳ ማህበሩ አስቀድሞ ሊያውቀው እንደሚገባ ለቁም ነገር መፅሔት ተናግረዋል፡፡
ያለ ማህበሩ እውቅና ህንጻውን ለማፍረስ የሚሞከር ከሆነ ከ43 ሺ በላይ የሚሆኑ አርበኞችና የአርበኛ ልጅ ልጆች የሚረዱበት የገቢ ምንጭ ስለሚቋረጥና የህልውና አደጋ ስለሚያጋጥም አስተዳደሩ ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲመለከተው አሳስበዋል፤