የአመቱ ዜና እረፍት

ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ

Madingo_Afework

‹የተወለድኩት በጎንደር ክፍለሀገር በምትገኘው የአዘዞ ከተማ ሲሆን፣ ወላጅ አባቴ ወታደር ነበር። አባቴ ወታደር ከመሆኑ በፊት የቤተክህነት አገልጋይ ሆኖ አሳልፏል። የተወለድኩበት ስፍራም ሰባተኛ ክፍለ ጦር የወታደር ካምፕ ውስጥ ነው። የሶስት ወር ህፃን ሳለው ከካምፑ ወጥቼ ዕድገቴም፣ ትምህርቴም በደብረ ታቦር ከተማ ሲሆን እናቴም በቤተክነት ውስጥ የኖረች መልካም እናት፣ እኔም ሆንኩ ወንድሜ ያሬድ፣ እንዲሁም እህቶቼ ቲጂና ቤቲም በእነዚህ ፈሪሃ እግዚአብሔር ባላቸው ወላጆች ስር ተኮትኩተን ያደግን ባህልና ጨዋነትን ከእናት አባት ወርሰን የኖርን፣ የደስተኛ እና ተብቃቅቶ አዳሪ ቤተሰብ ፍሬዎች ነን፣ …. በአጭሩየጎንደር ልጅ ነኝ፣ ሲጠቃለል የማላፍርባትና በሄድኩባት የምኮራባት የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ።› ብሏል በአንድ ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ– አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ፡፡ ማዲንጎ ዕድሜው 11 አመት ሲሞላ የታሪኩ ምዕራፍ ወደተከፈተበት ወታደር ካምፕ ገባ። በዚሁ አራተኛው ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ውስጥ ከዝነኛዋ ድምፃዊት ፍቅረአዲስ ነቃጥበብ እና ከድምፃዊና የዘፈን ደራሲው አዱኛ ቦጋለ ጋር የመተዋወቅና አብሮ የመስራቱ ዕድል ተከፈተለት።

በ603ኛው ኮር ውስጥ በሚገኘው በዚህ መካናይዝድ ክፍለጦር ውስጥ አዛዥ የነበሩትና እንደልጃቸው በስስት በሚያዩት ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ ስር ሆኖ የማይረሱ ጊዜያት ያሳለፈ ሲሆን፣ የሙዚቃንም፣ ሆነ የኑሮን ሚስጥር ያወኩበት ስፍራ በመሆኑ በህይወቴ መቼም የማረሳው ቦታ ሆኖ ውስጤ ይኖራል ይላል።

በ1983 የመንግስት ለውጥ ከተፈጠረ በኋላ የወታደር ቤት ቆይታው አበቃ። ለጥቂት ጊዜ ጎንደር ከሰራ በኋላ ወደባህርዳር አቅንቶ የምሽት ክበብ ውስጥ መስራት ጀመረ። እዚያ በመስራት ላይ ሳለው አምስት አባላት ካሉትና በወቅቱ “እርጎዬዎች” በሚል የጋራ መጠሪያ ከሚታወቁት የቤተሰብ ሙዚቀኞች ጋር ተዋወቀ። በተለይ ነብሱን ይማረውና የቤተሰቡ ብቸኛ ወንድ ልጅ የሆነው ንጋቱ ዱባለ አብሯቸው እንዲሰራና ያለውን የሙዚቃ ክህሎት የሚያወጣበት ዕድሉን ስላመቻቸለት ጨርቄን ማቄን ሳልል ባህር ከሆነችው አዲስ አበባ ገባ።

ማዲንጎ ወደ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የሙዚቃ ችሎታ ውን ለማሻሻልና በካሴት ስራ አድማጩ ጋር ለመድረስ ባደረገው ጥረት የተለያ አልበሞችን ሰርቷል፡፡ በድንገተኛ ህመም መስከረም 17 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ወጣቱ ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ በሀገራዊ ዘፈኖቹና በሚያስጨፍር የአጼ ቴዎድሮስ ዘፈኖቹ ይበልጥ ይታወሳል፡፡

የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ

Fekeru kidane

ታላቁ የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ በተወለዱ በ88 ዓመታቸው ነው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው የተሰማው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው ፍቅሩ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ በዋናነት የሚነሱት ሰው ናቸው፡፡ ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ የተወለዱት በ1927 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነው።አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በስፖርት ጋዜጠኝነት ፣ አመራርነት እና ደራሲነት የሚታወቁት አንጋፋው የስፖርት ሰው ነበሩ።

የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፍቅሩ ኪዳኔ ከሀገር ውስጥ ተቋማት በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማትን በኃላፊነት መርተዋል። አቶ ፍቅሩ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞ  ማህበር በ1961 ዓ.ም ሲመሰረት የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የነበሩ ሲሆን በብስክሌት ፌዴሬሽን፣ ቴኒስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በዋና ፀሐፊነት፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል።

በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥም በአመራርነት ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት የኢሳ ሃያቱ አማካሪ ጭምር እንደ ነበሩ ተዘግቧል ። ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ያደረጉት አቶ ፍቅሩ በሀገሪቷ ለሚገኘው ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ለኪፕ እና ሳምንታዊ የእግር ኳስ መጽሔት ፉትቦል ፍራንስ፣ ዶቼቬሌ (የጀርመን ድምፅ) እና ሌሎች የአለም አቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን መስራት ከመቻላቸው በተጨማሪ “የፒያሳ ልጅ” እና “የስፖርት ጨዋነት ምንጮች” የተሰኙ መጻሕፍት መጻፍ ችለዋል። ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ አንድ ልጅ ያላቸው ሲሆን ሁለት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።

አርቲስት ዓሊ ቢራ

Ali beera

በ ኢ ት ዮ ጵ ያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ባለውለታ ከሆኑት አንጋፋ ከያኒያን መካከል ዓሊ ቢራ በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ይመደባል። በበርካታ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጭምር በተጫወታቸው ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው አርቲስት ዓሊ ቢራ በተለይ በአፋን ኦሮሞ በተጫወታቸው በርካታ ሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን በመቻሉ የቋንቋው ምልክት እስከመሆን ደርሷል ይሉታል በርካቶች።

በግንቦት 1940 ዓ.ም በድሬዳዋ የተወለደው አርቲስት ዓሊ ቢራ ፣በህጻንነቱ የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን እያደመጠ ማደጉን እና ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ እና ለቤተሰቦቹ በማንጎራጎር የሙዚቃ ህይወቱን መጀመሩን በተለያያ ጊዜ ከሰጣቸው ቃለ ምልልሶች መረዳት ይቻላል።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በድሬዳዋ ከተማ ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አሜሪካ ሀገር በሚገኘው የሳንታ ሞኒካ ኮሌጅም የሙዚቃ ትምህርቱን ተምሯል። አርቲስት ዓሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም የኦሮሞን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ የባህላዊ ሙዚቃ ቡድን “አፍረን ቀሎ”ን በመቀላቀል ነበር የሙዚቃ ስራውን የጀመረው። በቡድኑ ውስጥ ሌላ ዓሊ የተባለ ልጅ በመኖሩ ሁለቱን ለመለየት መጀመሪያ ከሚያዜመው “ቢራ ዳ ባሬ” ዘፈን ተወስዶ “ዓሊ ቢራ” የሚለው ሰም ተሰጠው። ዓሊ ስለ አፍረንቀሎ የሙዚቃ ባንድ ወቅት ሲናገር “ እኔ ከመስራቾቹ አንዱ ነኝ እንጂ መስራች አይደለሁም፤በእድሜ ከነሱ አነስ እላለሁ።

አፍረንቀሎን ከመሰረቱት ውስጥ ዓሊ ሸቦ የሚባል እሱም ከሃረማያ ዩኒቨርሰቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶታል። እኔ ከነሱ ጋር ተቀላቅዬ አፍረንቀሎን መሰረትኩ” ብሏል። አርቲስት ዓሊ ቢራ በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተቀጥሮ ለሦስት ዓመታት ሰርቷል፤ እንዲሁም ‘አይቤክስ’ ባንድን በመቀላቀል ለስምንት ዓመታት የሙዚቃ ስራዎቹን በዲ አፍሪካ ሲያቀርብ ቆይቷል። ስለ ፍቅር፣ አካባቢ እና ፖለቲካ በጥቅሉ ከ267 በላይ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል። ዓሊ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኡድ እና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይጫወታል። ከአርባ በላይ ሀገራት (በሁሉም አህጉራት) እጅግ በርካታ በሆኑ መድረኮች የሙዚቃ ስራዎችን ተጫውቷል። ዓሊ ቢራ “Birra Children’s Education Fund” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር አቋቁመው ለሕፃናት ትምህርት ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

አርቲስት ዓሊ ከኦሮምኛ በተጨማሪ፣ በሶማሊኛ፣ በአፋርኛ፡በሐረሪ፣ በአማርኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች በርካታ ዘፈኖችን መጫወት ችሏል።አንድ ሰሞን ስለ ራሱ የተናገረው አርቲስት ዓሊ ቢራ “ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው” ብሏል።

የ75 ዓመቱ አርቲስት ዓሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነትና ማህበራዊ ትስስር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል።በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ መልካም ትውልድ እንዲቀረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።የተለያዩ ፈተናዎችን ተሻግሮ በከፍተኛ ጽናትና ብቃት ለረጅም ዓመታት በኪነ ጥበቡ ውስጥ ያሳለፈ መሆኑ ደግሞ አሁን ላለው ትውልድ ታላቅ ተምሳሌት ያደርገዋል።

አርቲስቱ በተስረቅራቂ ድምፁ ዘመን ተሸጋሪ ጥዑም ሙዚቃን ከመጫወት በተጨማሪ የግጥምና ዜማ ደራሲም ነው። አርቲስት ዓሊ ቢራ ባለፉት 50 ዓመታት በኦሮሞ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ እንቁ ሆኖ ቆይቷል። ለቋንቋው የሙዚቃ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በኪነጥበቡ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ የክብር ዶክተሬት ማዕረግ የተሰጠው አርቲስት ዓሊ ቢራ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ተቋማት የተለያዩ እውቅናዎችን እና ሽልማቶችን አግኝቷል።

ሎሬት ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር

Dr Teweld berhan

በብዝሃ ሕይወት ሳይንቲስትነት አንቱታን ያተረፉት ሎሬት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ባደረባቸው ሕመም በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በተጠናቀቀው ዓመት ነው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ እና ተከራካሪ የነበሩት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ከአባታቸው ከቄስ ገብረእግዚአብሔር ዮሐንስ እና ከእናታቸው ወ/ሮ መዓዛ ወልደ መድኅን በትግራይ ክልል ዐድዋ ርባገረድ መንደር የካቲት 12 ቀን 1932 ዓ.ም ተወለዱ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ 1ኛ ደረጃ እንዲሁም ወደ ጀኔራል ዊንጌት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማምራት በ1959 ዓ.ም በከፍተኛ ውጤት ወደ ቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል።ሎሬት ዶ/ር ተወልደብርሃን በሕይወት ዘመናቸው ለአገራቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ እና አርዓያነታቸው በጉልህ ቀለም ከሚጻፍላቸው ጀግና ኢትዮጵያዊያን መካከል በግንባር ቀደምትነት የተቀመጡ ነበሩ።በብዝሃ ሕይወት ጥናት እና ምርምርም በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘት ችለዋል። ዶ/ር ተወልደ ብርሃን የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ሲሆኑ ከ60 በላይ ሌሎች ልጆችን ያሳደጉ ልበ ቀና ሰው ነበሩ።

ዘማሪ/ድምፃዊት ሂሩት በቀለ

Hirut Bekel

“የወርቃማዉ ዘመን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንግስት” ድምፃዊት ሂሩት በቀለ ከ50ዎቹ መጀመሪያ እስከ 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ ባሉት አመታት ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር የሴት አርቲስቶች መካከል አንዷና ተወዳጅ ድምፃዊ ነበረች። ሂሩት በቀለ ከድምፃዊነት ባሻገር ተወዛዋዥና እንዲሁም የግጥምና የዜማ ደራሲ ነበረች። ሂሩት በቀለ የተጫወተቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዋቿ አሁን ድረስ በህዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅና እንደውም ለብዙ አዳዲስ ወጣት ሴት ድምፃዊያን ወደ ሙዚቃው አለም ለመሳብና እንዲሁም ለድምፃዊነት ብቃት መነሳሻና አቅም መፈተሻ መሆናቸው ግልጽ ነው።

ሂሩት በቀለ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በእለተ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም. ከእናቷ ወ/ሮ ተናኜወርቅ መኮንንና ከአባቷ የመቶ አለቃ በቀለ ክንፈ በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደች:: እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ቀበና ሚሲዮን ት/ቤት በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷ ተከታትላለች:: ሂሩት በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅት ለክፍል ጓደኞቿና ለሰፈሯ ልጆች ማንጎራጎርና ራፕ ማድረግ ታዘወትር ነበር:: ይህን ችሎታዋን የተመለከቱት ጓደኞቿም ወደሙዚቃው አለም እንድትገባ በተደጋጋሚ ያበረታቷትና ይገፏፏት ነበር:: በዚህ መሰረት እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1951 ዓ.ም.ችው የሙዚቃ አስተዋፅዖ ከኢትዮጵያ አብዮታዊ ጦር የፖለቲካ አስተዳደር የምስጋና ደብዳቤና ሽልማት ተቀብላለች፡፡ ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የቲያትር እና ሙዚቃ ክፍል የ25-ዓመታት ከፍተኛ ስኬት እና የላቀ አስተዋፅኦ የምስክር ደብዳቤ ከፍተኛ ሽልማት ፤ ከቀድሞ የሰሜን ኮርያ ፕሬዚዳንት ኪም ኢል ሱንግ እጅ ከወርቅ የተሰራ ሜዳልያ፤ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነር: ለፖሊስ ሃይል ስፖርት ፌስቲቫል ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና ሰርተፍኬት፤ ከመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን: ላበረከተችው አስተዋፅኦ ልዩ እውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት፤ ከወንጌል ብርሃን አለማቀፍ አገልግሎት ቤተክርስቲያን: በሃይማኖታዊ ህይወት ላሳየችው ትጋትና አስተዋፅኦ የምስጋና ሰርተፍኬት ወዘተ ይገኙበታል።

በ16 አመቷ ከቅርብ ጓደኛዋ ጋር በመሆን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል በመሄድ በድምፃዊነት ተፈትና ለመቀጠር በቃች:: ብዙም ሳትቆይ ለመጀመሪያ ግዜ በተጫወተችው “የሐር ሸረሪት” በተሰኘው ዜማ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን አገኘች:: ይሄኔ ነበር የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል አይኑን የጣለባት። ጥሎባትም አልቀረ በ 1952 ዓ.ም. ላይ ከምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል እውቅና ውጪ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ሂሩትን በመጥለፍ በጊዜው ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ወደሚባለው የፖሊስ ማሰልጠኞ ካምፕ በመውሰድ በልዩ ኮማንዶዎች የ24 ሰዓት ጥበቃ እየተደረገላት ከወር በላይ ተደብቃ ቆየች::

ከአንድ ወር ያላሰለሰ ጥረት በኃላ የምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ፍለጋውን ለማቋረጥ በመገደዱ: የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል ሂሩትን በይፋ በቋሚነት የሠራዊቱ የሙዚቃ ክፍል አባል አድርጎ ቀጠራት:: ሂሩት ከተጫወተቻቸው አያሌ ሙዚቃዎቿ መሀከል አንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውና ከትንሽ እስከ ትልቅ በሀገር ፍቅር ስሜት እስከአሁን የሚያዜመው “#ኢትዮጵያ” አንዱ ነው:: ሂሩት በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃና የቴአትር ክፍል ውስጥ በቅንነት ለ35 ዓመት አገልግላለች:: በነዚህም 35 ዓመታት ውስጥ ከ¬¬¬200 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወተችና ለህዝብ ጆሮ ያደረሰች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በሸክላ የታተሙት ከ38 በላይ ሙዚቃዎች ሲሆኑ: በካሴት ደረጃ ደግሞ 14 ካሴቶች እያንዳዳቸው 10 ፈኖችን የሚይዙ ለሙዚቃ አፍቃሪዎቿ አበርክታለች:: ሂሩት በሙዚቃ አለም በቆየችባቸው 35 አመታት ውስጥ ከብዙ ስመጥር ድምፃውያን ጋር በመሆን ስራዋን ለህዝብ አቅርባለች: ከነዚህም መሀከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል: ማህሙድ አህመድ፣አለማየሁ እሸቴ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ መልካሙ ተበጀ፣ ታደለ በቀለ፣ መስፍን ሀይሌ፣ ካሳሁን ገርማሞና ሌሎችም ይገኙበታል። ሂሩት በቀለ ከ1987 ዓ.ም. በኃላ እራስዋን ከሙዚቃ አለም በማግለል ሙሉ ጊዜዋን በመንፈሳዊ ህይውት ውስጥ ሆና ኖራለች፡፡አርብ ግንቦት 4 ቀን 2015 በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የራሷን አሻራ ያስቀመጠችው አንጋፋዋ ድምጿዊት ሂሩት በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ ተሰምቷል።ሂሩት በቀለ የ7 ልጆች እናት፣ የ10 ልጆች አያት እና የ7 ልጆች ቅድመ አያት ነበረች።

አርቲስት ተሾመ አንዳርጋቸው

Artist Teshome

የአዲስ አበባ ትያትርና ባሕል አዳራሽ የረዥም ዓመታት ባልደረባ የነበሩት አርቲስት ተሾመ አንዳርጋቸው በተወለዱ በ 73 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ቴአትር ቤቱ አስታውቋ፡፡አርቲስት ተሾመ አንዳርጋቸው የተወለዱት ጥቅምት 20 ቀን 1942 ዓ.ም ነው፡፡ ትምህርታቸውን በመድሀኒያለም ት/ቤት የተማሩ ሲሆን በኤሌክትሪክ ሲቲ ከሙያና ቴክኒክ ት/ቤት የ6ወር ሰርተትኬት አግኝተዋል፡፡ በትወና ጥበብ ሙያ ከ1962 እስከ 1966 ዓ.ም ቴዎድሮስ የቴያትር ቡድን ውስጥ ሰርተዋል፡፡

በቴአትር ቤቱ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ የወጣው የህይወት ታሪካቸው እንደሚገልፀው ከሆነ በ1968 የካቲት 16 በአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ ባልደረባ ሆነው የተቀጠሩ ሲሆን:-

* በትወና ጥበብ ስራ ከ1968 እስከ 1970 ዓ.ም

*በቴክኒክ አገልግሎት ሀላፊነት ከ1970 አስከ 1983

*ከ1983 አስከ 1988 በቴያትር አዘጋጅነት እንዲሁም

* ከ1988 አስከ 1995 የቴያትር ጥበባት ኢክስፐረት 2

አገልግለዋል በዋና አስተባባሪነት እና ተዋናይነትም፦

• እሳት ሲነድ

• መልእክት ወዛደር

• አቦጊዳ ቀይሶ

• ቴውድሮስ ቲያትር ከብዙ በጥቂቱ ሲሆን በኦቴሎ ቴያትር ላይ የመድረክ ዲዛይን፤የአልባሳት ዲዛይን፤እንዲሁም

ሜካፕ ከስራቸው ጎን ለጎን በመስራት የድርብ ተሰጥኦ ባለቤት መሆናቸውን አስመልክተዋል፡፡ቴድሮስ ቴያትርም ወደ ሰሜን የአገሪቱ ክፍል ሲጉዋዝ ከዋና አስተባባሪነት ባሻገር ቡድኑን በመምራት ተጉዘዋል፡፡በአዘጋጅነት፦

• ታርቲዩፍ የሞሌር ድርሰት የጸጋዬ ገ/መድን ትርጉም በአዘጋጅነት በመድረክ ዲዛይነርነት እና በአልባሳት ዲዛይነርነት

ሰርተዋል

• የሚተኑ አበቦች ላይ በቲያትር ላይ በአዘጋጅነት ሰርተዋል• በተለይ የአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ ከተሰሩ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ቴያትሮች የጀርባ አጥንት ሆነው ቆይተዋል፡፡

• በማዕድ ጥበባት ትርኢት ላይ በማዛጋጀት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል

• በ1984 ዘግሬት ባታሊዮን የተሰኘ የሆሊውድ ፊልም ላይ በአስተባባሪነት እንዲሁም የአድዋ ዶክመንተሪ ሲሰራበዋና አስተባባሪነት ሰርተዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ሙያና ችሎታቸውን ለአዲሱ ትውል በማስተማርና በማሻገር ይታወቀሉ።

አርቲስት ተሾመ አንዳርጋቸው የ2 ሴት ልጆች ሲኖሯቸው 4 የልጅ ልጆችም ለማየት የቻሉ ሲሆን የቀብር ስነስርአታቸውም ሰኔ 9/2015 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 የካ ሚካኤል ተፈፅሟል።

አርቲስት ዘሪሁን ወዳጆ

Artist Zerhun wedajo

የአንጋፋው የኦሮሚኛ ሙዚቃ አርቲስት ዘሪሁን ወዳጆ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው በተጠናቀቀው ኣመት ነው፡፡ በችግር ምክንያት የቀን ስራ እስከመስራተ ደርሶ ታሞ መታከሚያ አጥቶ እንደነበር የቅርብ ጓደኞቹ የሚናገሩለት አርቲስት ዘሪሁን የቀብር ሥነ–ሥርዓት ቤተሰቦቹ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አርቲስቶች እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነው የተፈጸመው፡፡ አርቲስቱ በሕንድ አገር በሕክምና ላይ እያለ በ66 ዓመቱ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው።

አርቲስት ዘሪሁን ወዳጆ ከአባቱ አቶ ወዳጆ ጎበና እና እናቱ ወ/ሮ ዘውዲቱ መኮ በነቀምቴ ከተማ በ1949 ዓ.ም ተወለደ። አርቲስት ዘሪሁን በሙዚቃ ሥራዎቹ ለኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ አንጋፋ አርቲስት ነበር። የሕይወት ታሪኩ ላይ እንደ ተገለጸው የልጅነት ጊዜውን በነቀምቴ፣ ሸዋ፣ ጊምቢ እና መንዲ አሳልፏል።

በመንዲ የ7ኛ ክፍል ተማሪ እያለ የፀረ ጭቆና ትግሉን ማቀንቀን እንደ ጀመረ የህይውት ታሪኩ ያሳያል።በወቅቱም “የጉቦ ጣጣ ከመንዲ ውጣ” በሚል እንቅስቃሴ ብዙዎችን እያነቃቃ ወደ ትግል ሊያስገባ ችሏል። ሙዚቃዎቹ በባህል፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች እና በአንድነት ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በተለይም በተለያዩ ሥርዓተ መንግሥታት ሕዝቡ ላይ ይደርሱ የነበሩትን ጭቆናዎች በሙዚቃው ሲቃወም ቆይቷል።

አርቲስት ዘሪሁን ከ45 ዓመት በላይ በሙያው ያገለገለ ሲሆን 95 ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን ለሕዝብ አድርሷል።

የኦሮሞ ሕዝብ ብሶትን፣ ድልን፣ ተስፋ እና ደስታን በተዋቡ ቃላት ከ20 በላይ በሚሆኑ የመድረክ ሥራዎቹ አቅርቧል።በሽኝቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአርቲስቱ ቤተሰቦች እና ወዳጆች እንዳወሱት፣ አርቲስት ዘሪሁን ወዳጆ በዘመኑ መሥራት የሚገባውን በመሥራቱ በሥጋ ቢለይም በሥራዎቹ ኅያው ሆኖ ይኖራል። አርቲስቱ በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ሐሳቦችን ስላስቀመጠ ለሙዚቀኞች አርአያነት ያለው ሥራ መሥራቱ ለሙያው ክብር ነውም ተብሏል። አርቲስት ዘሪሁን ወዳጆ ባለትዳር የነበረ ሲሆን የአንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆች አባት ነበረ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው

Associate proffesor Zerhun Asfaw
Associate proffesor Zerhun Asfaw

የአንጋፋው የሥነ ጽሑፍ መምህር እና ሐያሲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ስርዓተ ቀብር በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በኢትዮጵያ የሥነ ፅሑፍ እድገት ላይ ጉልህ አሻራ ያኖሩት የአንጋፋው የሥነ ጽሑፍ መምህር እና ሐያሲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ሰኔ 1111 ቀን 2015 ነው ማረፋቸው የተሰማው፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማግስቱተፈጽሟል።

ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ ተመራማሪነትና በአማካሪነት ሲሰሩ የቆዩትበስነ ፅሑፍ ሃያሲነታቸው አንቱታን ያተረፉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን፤ በዩኒቨርሲቲው የቋንቋና ስነ ፅሑፍ ትምህርት ክፍል ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል።

አንጋፋው የስነፅሑፍ ሰው “የሥነ ጽሑፍ መሰረታውያን”፣ “ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ” ስነ ፅሑፋዊ ተሀዝቦት እንዲሁም “የልብ ወለድ አዋጅ” የተሰኙ ሶስት መጻሕፍትን ለንባብ አብቅተዋል።በተጨማሪ የአጭር ልብወለድ ንድፍና ተግባራዊነት ላይ የሚያተኩር መፅሐፍ አጠናቀው ለሕትመት በማሰናዳት ላይ ነበሩ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ያቀርቧቸው የምርምር ሥራዎች፣ በውጭና በሀገር ውስጥ የምርምር መፅሔቶች ላይ ታትመውላቸዋል፡፡በ1944 ዓ.ም በደሴ ከተማ የተወለዱት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተከታትለው፣ በበዕደ ማርያም ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል።በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።በዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው ላይ እንዳሉ ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው አገልግሎት በኤርትራ ከረን ለአንድ ዓመት እንዳስተማሩና በእድገት በህብረት ዘመቻ በዓድዋ በአካባቢ ዘምተው የህብረተሰብ አገልግሎት መስጠታቸውን በህይወት ታሪካቸው መመዝገቡን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ መጀመሪያ በአለማያ ኮሌጅ ቀጥሎም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ42 ዓመታት በምርምር፣ በማስተማርና በማማከር አገልግሎት ላይ ቆይተዋል።በሥራ ዘመናቸው የተለያዩ ሽልማቶችን የተቀዳጁት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን የአንድ ሴት ልጅና የሶስት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ከህልፈተ ህይወታቸው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ኢቢሲ ከሰው መሆን ፊልም ፕሮዳክሽን ጋር በመተባበር “ፍቅር እስከ መቃብር” መፅሐፍን በቴሌቪዥን ድራማ ለማቅረብ እያደረገ ላለው ዝግጅት ሙያዊ ሀሳቦችን አካፍለው ነበር። በፍቅር እሰከ መቃብር መፅሐፍ ዙሪያ መልከ ብዙ ጥናቶችን እንዳደረጉም የሙያ አጋሮቻቸው መስክረዋል።

ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው ኃይሉ

Dawit Ferew

በአስደናቂ ክላርኔት ጨዋታው የሚታወቀው ዳዊት ፍሬው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ለስራ ከሄደበት ጣሊያን መሆኑ ተሰማቷል፡፡ ዳዊት በሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታው የታላላቅ ሙዚቃ አቀናባሪዎች /ኮምፖዘሮችን/ የክላርኔት ሥራዎች ተጫውቷል።

ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው ኃይሉ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ትምህርቱን ‘ሜጀር ክላርኔት’ በማድረግ የተመረቀ ሲሆን የአልቶ ሳክስፎንና ክራር ተጨዋችም ነበር። በአስደናቂ ክላርኔት ጨዋታው የሚታወቀው ዳዊት ፍሬው በሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታው የታላላቅ ሙዚቃ አቀናባሪዎች / ኮምፖዘሮችን/ የክላርኔት ሥራዎች ተጫውቷል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቢግ ባንድ ውስጥም በክላርኔትና አልቶ ሳክስ ተጨዋችነት ለተወሰኑ ዓመታት በማገልገል በግሉ የመጀመሪያውን በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበረ አልበም በፈለቀ ኃይሉ አቀናባሪነት ለማሳተም ችሏል።

ከ2000 እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር ከተቋቋመው የ”አዲስ አኩስቲክስ” ባንድ ጋር አልበም የማሳተምና በበርካታ አገራት ኮንሰርት የማቅረብ ዕድል ነበረው። በተከታታይ ሦስት የመሣሪያ ቅንብር ሥራዎችን በአልበም ያሳተመው ዳዊት ፍሬው ለሙዚቃ ሥራ በሄደበት ጣሊያን ሮም ከተማ በ44 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በድንገት በሞት መለየቱ ይታወቃል።

አስከሬኑ በክብር ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ የተለያዩ የሽኝት መርኃ ግብሮች ተሰናድተውለት በዛሬው እለት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብሩ መፈፀሙን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ግንቦት 6/2015 የሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው የቀብር ሥነ ሥርዓት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲፈፀም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የሙዚቀኛው አድናቂዎችና ዘመድ ወዳጆቹ ተገኝተዋል፡፡

ከአርቲስት ዳዊት ፍሬው ስራዎች መካከል አንዱ “ ጥላ ከለላዬ “ የተሰኘው በመሳሪያ የተቀነባበረ መዚቃ ሲሆን በዚሁ ስራ ይህ ስንኝ ይገኝበታል። በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ በተቀነባበሩት የሙዚቃ አልበሞቹ ላይ አንጋፋው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያምና አርቲስት ተፈሪ ዓለሙን የመሳሰሉ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን አንጋፋው የሙዚቃ መምህርና ባለሙያ ፈለቀ ኃይሉ ያቀናበራቸው ናቸው፡፡ ታዋቂው የክላርኔት የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፤ ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው መስከረም 7 ቀን 1971 ዓ.ም በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ደጃች ውቤ ሠፈር ተወለደ፡፡

ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በራስ አበበ አረጋይ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በእንጢጦ አጠቃላይ ከአጠናቀቀ በኋላ ከልጅነቱ ጀምሮ በውስጡ ይመኘው የነበረውን የሙዚቃ ትምህርት ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ትምህርቱን አጠናቆ ተመርቋል፡፡

ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው በዋነኛነት ከሚታወቅበት የክላርነቴ የሙዚቃ መሳሪያ በተጨማሪ አልቶ ሳክስፎን፣ ክራር የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይጫወታል፡፡ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው አራት የሙዚቃ መሳሪያ የተቀነባበሩ የሙዚቃ አልበም ለህዝብ አቅርቧል ፡፡

በተጨማሪም ከአዲስ አኩስቲክ ባንድ ጋር በነበረው ቆይታ ትውስታ ቢል ርዕስ በተዘጋጀ አልበም ላይ ያለውን በቃት በማሳያቱ የተለያዩ የውጭ ሀገር ሚዲያ ስላለው የኢትዮጵያ ዜማዎች በኢትዮጵያ ቅላፄ አጨዋወት መስክረውለታል፡፡ ዳዊት በሙያው በመላው ኢትዮጵያ ተዟዙሮ ስራዎችን ከማቅረቡ በላይ ከሀገር ውጪ በፈረንሳይ፣ ጀርመን ዴንማርክ፣ ሲዊድን፣ ሆላንድ ኳታር፣ ለንደን፣ ጅቡቲ ዘዋውሮ ስራዎቹን አቅርቧል፡፡

ሙዚቀኛ ዳዊት ፍሬው በኢትዮጵያ ቀደምትና የመጀመሪያ ከነበሩ ድምፃዊያን መካከል የታዋቂው ድምፃዊና ሙዚቀኛ የፍሬው ኃይሉ ልጅ ሲሆን ወደ ሙያው ለመምጣት የአባቱ ተፅእኖ ቀላል እንዳልሆ ይናገራል፡፡

“ ጥላ ከለላዬ ፤ #ኢትዮጵያ ❤️ሀገሬ

#ኩራት ይሰማኛል ፤ ካንቺ መፈጠሬ።

ጋዜጠኛ አለማየሁ ግርማ

Alemayhu Girma

በተለየ የራዲዮ ዜና አቀራረቡ ብዙዎች የሚያውቁት የጋዜጠኛ አለማየሁ ግርማ በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው በተጠናቀቀው ዓመት ነው፡፡ጋዜጠኛ አለማየሁ ግርማ ከአባቱ ከሃምሳ አለቃ ግርማ ዳዲ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ዘውድነሽ መንግሥቱ በ፣1966 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ቦታው ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን አከባቢ ተወለደ፡፡እድሜው ለአቅመ አዳም እንደ ደረሰ በወንድሟሟቾች ከ 6 ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ ከ7 – 8 ንፋስ ስልክ ት/ቤት ትምህርቱን በመቀጠል ከ9-12ኛ ጂሲኤ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በመከታተል ልዩ ክላስ በተቋቋመው ክፍል ውስጥ እጅግም በጣም አስደሳች ውጤት በማምጣት በከፍተኛ ነጥብ ተብሎ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና በማለፍ ትምህርቱን በጋዜጠኝነት ሙያ በማዕረግ ተምሮ ድግሪውን ወስዷል፡፡

በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሳለ ከ(800)ስምንት መቶ ተወዳዳሪዎች መሀከል በዚሁ ደረጃ ውጤቱ ከፍተኛ አንደኛ በመሆን በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተቀጥሮ ሲሰራ ቆይቶ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ከፍተኛ እውቀት ይበልጥ እንዲያዳብሩ – ስኮላርሺፕ ተሰጥቶት ሙያውን ያዳበረ ጎበዝ ሰራተኛ ነበረ፡፡ ጋዜጠኛ አለማየሁ ግርማ ትዳር መስርቶ ( 1 ) አንድ ወንድ እና ሁለት ሴቶች ልጅም አፍርቷል፡፡

ጋዜጠኛ አለማየሁ ግርማ መልካም ስነ ምግባር ያለው እና ከማንም ሰው ጋር ተግባቢ፤ ማኅበራዊ ኑሮን የተላበሰ ሰው ነበር ::ጋዜጠኛ አለማየሁ ግርማ በድንገት ታሞ ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በተወለደ በ49 ዓመቱ ታሞ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።ሥርዐተ ቀብሩ በዮሴፍ ቤተክርስቲያን እና ቅዱስ ሚካኤል ቅጥር ግቢ ከቀኑ በ7:00 ሰዓት ላይ ተፈፅሟል፡፡

ካራማራው ጀግና አሊ በርኬ

Ali Berke

ትውልድና እድገታቸው በቀድሞ ወለጋ ክፍለሀገር ነው።በልጅነታቸው ከፍተኛ የአደን ፍቅር ነበራቸው።በ1969 አ.ም ሀገራችን ከተስፋፊው ወራሪ የዚያድባሬ ጦር የተቃጣባትን ጥቃት ለመታደግ ታጠቅ ጦር ሰፈር ከከተሙ ቆራጥ የሚሊሻ አባላት አንዱ ናቸው።የሶስት ወር ስልጠናቸውን አጠናቀው የ94ኛ ሚሊሻ ብርጌድ ሁለተኛ ሻለቃ ባልደረባ በመሆን ወደ ግንባር ዘመቱ።

በአውሸሪፍ ግንባር በህዳር ወር 1970 አ.ም በራሳቸው ተነሳሽነት ተንቀሳቅሰው ሶስት የጠላት ታንኮችን ከነአዛዦቻቸው ደመሰሱ። ለዚህ አኩሪ ጀግንነታቸው ከወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኮ/ል መንግስቱ ሀ/ማርያም እጅ የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ አንደኛ ደረጃ የጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ሆነዋል።እኚህ ጀግና የደርግ መንግስት በኢህዘዴግ መንግስት ሲተካ ወደኬንያ ተሰደው ከፍተኛ እንግልትና መከራ ተቀብለዋል።ከስደት ሲመለሱም የወጣትነት አፍላ እድሜያቸውን ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ቆስለው ከጠላት በታደጓት ሀገራቸው ያለምንም ምክንያት ለዘጠኝ አመት በአለም በቃኝ እስር ቤት ተጣሉ።ከእስር ሲፈቱም ጫኝና አውራጅ ሆነው የእለት ኑሯቸውን ለመግፋት ተገደዱ።እኝህን ጀግና ከወደቁበት ፈልጎ በማንሳት ተሸላሚ እንዲሆኑና እና የገንዘብ እገዛ እንዲያገኙ በማድረግ በአርቲስት ታማኝ በየነ አስተባባሪነት ይመራ የነበረው የጀግኖች ምሽት አዘጋጅ ኮሚቴ ቀዳሚነቱን ተወጥቷል።

እኚህ ብሄራዊ ጀግና ሻለቃ ባሻ አሊ በርኪ ከዘመናት እንግልትና ውጣ ውረድ በሗላ ግንቦት 28/2015 ዓ_ም ማረፋቸው ተሰምቷል፡፡ በችግርና በድህነት የኖሩት እኝህ ብሔራዊ የካራማራ ጀግና ሲሞቱ በብሔራዊ የክብር ዘብ አስከሬናቸው ታጅቦ እንዲቀበር መደረጉ ለመላው ቤተሰባቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናኛ ሆኗል፡፡

መምህር ቴዎድሮስ ቦጋለ

Tewodros Bogale

በያኔው የዲላ መምህራን ትምህርት እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በአሁኑ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በ1989 ዓ.ም ከተመደቡ የመጀመሪያዎቹ መስራች መምህራን አንዱ ነበር መምህር ቴዎድሮስ ቦጋለ። ላለፉት 26 ዓመታት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምርና ሲመራመር በተለየ ሀሳቡ፣ በንባብና የእውቀትክህሎቱ፣ ነገሮችን በአንክሮ በመመልከት በሚሰጠው የሰላ ምሁራዊ ሂስ ይታወቃል።

“ቴዲ ምን አለ?” ተብሎ በተማሪዎች፣ በመምህራን እና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጭምር የሚጠበቅ የሀሳብ መለኪያ፣ መወሰኛም ነበር። በአማርኛ ቋንቋና ሥነ–ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ዘለግ ያለውን ጊዜ ሲያስተምር መምህር ብቻ አልነበረም። ሥነ– ጽሁፍን በሚገባ የመረመረና ድንቅ የሥነ–ጽሁፍ ሀያሲም ነበር። መምህር ቴዎድሮስ ቦጋለ ተፈሪ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ የነበረ ቢሆንም እንደተመኘው ሳይሆን ቀርቶ ሰኞ፣ ሰኔ 26/2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የቀብር ስነ– ስርአቱም በማግስቱ ማክሰኞ፣ ሰኔ 27/2015 ዓ.ም ከጧቱ 4:00 ላይ በአዲስ አበባ አርባ አንድ (41) ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈፅሟል።እንደ መምህር ቴዎድሮስ አይነት ምሁር እና አሳቢ ማጣት ለዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ተማሪዎች እና አጠቃላይ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሥነ–ጽሁፍ ሁነኛ እና ንቁ ሃያሲ፣ ተመራማሪ፣ አንባቢና የመርህ ሰው እንደማጣት ይቆጠራል ሲል ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

መምህር ቴዎድሮስ ቦጋለ ተፈሪ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ያለመታከት በማስተማር፣ በመመራመርና በልዩ ልዩ መድረኮች ባቀረባቸው ሙያዊ ጽሁፎች ያበረከተው ምሁራዊ ስራ፣ ለሀገር ያበረከታቸው የእውቀት ልጆቻቸው ህያው ምስክሮች ናቸው። በቅርቡም በግደኞቹ ጥረት ለዘመናት ያዘጋጃቸውን ፅሁፎች በማሳተም ለአንባቢያን ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ሰዓሊ አብድርኽማን ሸሪፍ

Artist Abedurahman

በአለ_የሥነጥበብና_ዲዛይን_ት_ቤት ከአምስት አስርት አመታት በላይ በመምህርነት ያገለገሉት ሰዓሊ አብድርኽማን ሸሪፍ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸው የተሰማው በተጠናቀቀው ዓመት ማብቂያ ላይ ነው፡፡

ታ ላ ቁ የሥነጥበብ ምሑር ፣ ሠዓሊ እና መምህር አብድርኽማን ሸሪፍ የቀድሞውን የአዲስ አበባ ስነ ጥበብ ት/ቤት በደርግ ዘመን ለ17 ዓመታት በዳይሬክተርነት በትጋት አገልግለዋል።ሕ ይ ወ ታ ቸ ው እስካለፈበት ጊዜ ድረስም በአስተማሪነት ሥራቸው ላ ይ መቆየታቸው የህይውት ታሪካቸው ያስረዳል። ሰ ዓ ሊ አብዱራህማን ሀገራችን ካፈራቻቸው አንጋፋና ዓለምአቀፍ ሠዓልያን መካከል ቀዳሚው ሙያተኛ ነበሩ። አርቲስቱ ለሙያቸው የተሰጡ፣ በአኗኗር ፈሊጣቸው ለተማሪዎቻቸውና ለሙያ ጓደኞቻቸው አርዓያ የሆኑ ሰዓሊ እንደነበሩ የሙያ ጓደፈኞቻቸው ይናገራሉ፡፡ ከዘመን የሥነ ጥበባት ጽንሰ ሐሳባዊ ለውጦችና ሙግቶች እኩል መራመድ የቻሉ፣ ንቁ የጥበብ ሰው እንደነበሩ የዘርፉ ሙያተኞች በኵራት የሚመሰክሩለት ሰው ነበሩ። በሐይማኖት ጉዳይ ሳውዲ አረብያ በሔዱበት ወቅት ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በማረፋቸው ቀብራቸውም በዚያው ሀገር መፈጸሙን ተሰምቷል::

ጋዜጠኛ ሠሎሞን ገብረአምላክ

Journalist solomon

የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ባልደረባ የነበረው፣ በተለያዩ የግል ጋዜጣና መፅሔቶች ሞገድ ፣ምኒልክ ፣ ሳተናው፣ ማዕበል፣ አንደበት ይሰኙ በነበሩት እና በሌሎችም ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ በአዘጋጅነት፣ በዜና ዘጋቢነት፣ በዐምድ ጽሑፍ አቅራቢነቱ… ይታወቅ የነበረው ጋዜጠኛ ሠሎሞን ገብረአምላክ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው በተገባደደው ዓመት ነው፡፡

ሠሎሞን ገብረአምላክ በራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሕይወቱ ያለፈው ረቡዕ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም በማግስቱም የቀብር ስነ ስርዓቱ ተፈፅመዋል፡፡አይረሴው ጋዜጠኛ ሠሎለሞን ገብረ አምላክ በበርካታ ጋዜጦች እና መጽሄቶች ላይ በውል ስሙ እንዲሁም በተለያዩ የብዕር ስሞች የጻፈ ፣ በነጻው ፕሬስ የኅትመት ውጤቶች ላይ አሻራውን ያሳረፈ! ከሙያው ጋር በተያያዘም ሁሉንም ዓይነት መስዋእትነት የከፈለ ጋዜጠኛ ነበር።

አርቲስት አብነት ዳግም

Artist Abenet dagem

 

ለረዥም ጊዜ በህመም ላይ የቆየው አርቲስት አብነት ዳግም ነሐሴ 3 ቀን 2015 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡አርቲስት አብነት በበርካታ ቴአትሮች ፣ ፊልሞች እና ድራማዎች ላይ በተዋናይነት በመሳተፍ እውቅናን ያተረፈ ነበር።

ከዚህ ውስጥ አሉላ አባነጋ፣ የቼዝ ዓለም፣ ዳኛው፣ እስረኛው ንጉስ እና ነቅዕ ቴአትሮች ላይ ተውኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አያስቅም፣ አንድ እድል፣ ላምባዲና፣ ሰበበኛ፣ ባንቺ የመጣ፣ ቁልፉን ስጭኝ፣ የነገርኩሽ እለት፣ ፍቅር እስከ መቃብር እና አትሸኟትም ወይ በተሰኙ ፊልሞች ላይ በመተወን አድናቆትን አግኝቷል። ስንቅ ፣መለከት፣ ትርታ እና ለወደዱት ደግሞ የተሳተፈባቸው የቴሌቪዥን ድራማዎች ሲሆኑ፥ በግሉም የቅብብሎሽ ድራማን ደርሷል።

ወ/ሮ አልማዝ አበራ የደራሲ በዓሉ ግርማ ባለቤት/

Wro Almaz Abera

የዝነኛው ደራሲ በዓሉ ግርማ ባለቤት ወ/ሮ አልማዝ አበራ ሱማሌ ተራ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ የተሰማው ህዳር 23 ቀን 2015 ነው፡፡ ወ/ሮ አልማዝ ሁሌም ስለባለቤቷ እና ስለልጆቿ አባት ተናግራ አታበቃም ነበር፤ ዓመት በዓልን ላይ ከሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ቀጥሎ አጀንዳው በዓሉ ነው፤ የዛሬ 8 ዓመት ለታሪክ እንዲሆን ከሶስት ሰዓታት በላይ በቁም ነገር መፅሔት ላይ የተደረገው ቃለ ምልልስ በበዓሉ ጉዳይ ተስፋዋ እንዳልተሟጠጠ ይታይ ነበር፤ ‹ በዓሉ ይመጣል ብዬ አሁንም በር በሩን አያለሁ›› ነበር ያለችኝ፤ ‹መጨረሻውን የሚያውቁ ሁሉ ለህሊናቸው ሲሉ ቢናገሩ ጥሩ ነው › የምትለው ወ/ሮ አልማዝ ባዶ ቤት ሶስት ልጆቹን ጥሎ እንደ ወጣ የቀረውን ባለቤተቷን ፅናት ተጋርታ ልጆቿን አስተምራ ለወግ ለማዕረግ ያበቃች ጠንካራ ሴት ናት፤ በዓሉ ግርማ የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 11 ገደማ ከቤቱ እንደወጣ አልተመለሰም፤ ለባለቤቱም ሆነ ለልጆቹ እዚህ ነው የወደቀው፤ እዚያ ነው የተቀበረው ብሎ የነገራቸው ሰው የለም፤ ጉዳዩን ያውቃሉ የተባሉ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም ጀምሮ ወንጀሉን ሲያድበሰብሱት ኖረዋል፤ ባለቤቱ ግን አሁንም በር በሩን እያየች ኖራ ኖራ ኖራ ወደ እርሱ ጋር ሄዳለች፤ ነፍስ ይማር !የወ/ሮ አልማዝ አበራ የቀብር ስነ ስርዓት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ቤተሰቦቿና የደራሲ በዓሉ ግርማ አድናቂዎች በተገኙበት ተፈጽመዋል፡፤

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ

Dawit kebebed

በዕለተ– ቅዳሜ መጋቢት 2/2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 2 ሰአት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ድንቅ ብዕረኛን እንዘክር ዘንድ የማስታወሻ መርሀ–ግብር ያዘጋጀን ሲሆን ‹‹ዳዊት ያቺን ሰአት›› የሚል ርዕስ ያለውም የማስታወሻ መርሀ–ግብር ነው። መርሀግብሩ የዳዊት ከበደ ወየሳ ቤተሰቦች ከተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ጋር ያዘጋጁት ሲሆን ከዳዊት ስራ ምን እንማር በሚልም ንግግሮች ይቀርባሉ፡፡

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ በመዲናችን አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ቄራ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በ1961 ዓ.ም የተወለደው። ከልጅነቱ አንስቶ ከንባብ ጋር በነበረው ትስስር አማካኝነት የሰላ ባለብዕር እንዲሆን አ ስ ች ሎ ታ ል ። ዳ ዊ ት በ1988 ‹‹ፊያሜታ›› የተሰኘችውን በታሪክ እና በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረች ጋዜጣን ሲያሳትም የነበረ ሲሆን ከዚያ ቀደም ብሎም በነጻው ፕሬስ ምስረታ ላይ የጎላ ሚና ከነበራቸው አንዱ ነበር፡፡ በታሪክ እና በፖለቲካ ጉዳዮችም ላይ ብእሩን ከወረቀት በማዋሀድ በሳል ብእረኛ መሆኑን ያስመሰከረ ነው፤ የሚጽፋቸው ግጥሞች ብስለትን የተላበሱ ፤ የሚያቀርባቸው ሂሳዊ መጣጥፎች ለማንበብ የሚጋብዙ ነበሩ፡፡

የቴአትር ስክሪፕቶችን በመጻፍ እውቅና ያተረፈው ዳዊት እውነትን ለመናገር ወደ ኋላ የማይል ደፋር ጋዜጠኛ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ በዚህ ድፍረቱም ለእስርና እንግልት የተጋለጠ ሲሆን አጠቃላይ የሀገሪቱን ሁኔታ በመረዳት ከጊዜው የቀደሙ ስራዎች እንዲሰሩ አድርጓል፡፡

በ1992 በሀገሪቱ በጋዜጠኞች ላይ በሚደርሰው እስር ለስደት የተዳረገው ዳዊት ለ23 አመት መኖርያውን በአትላንታ አድርጎ ነበር፡፡በባህር ማዶም ሳለ በልዩ ልዩ ምክንያት በስደት ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን በማገዝና በማሰባሰብ የማይተካ ተወጥቷል፡፡

ዳዊት በአትላንታ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ‹‹አድማስ›› የተሰኘውን የሬድዮ ጣቢያን እና ‹‹ድንቅ›› መጽሄትን በመመስረት ሙያዊ ግዴታውን የተወጣ ባለሙያ ነበር፡፡ ዳዊት ከበደ ወየሳ ገና ብዙ እየተጠበቀበት ድንገት በጥቅምት 29/2015 ለእረፍት ኢትዮጵያ እንደመጣ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡ ስራዎቹ እና አበርክቶውን መነሻ በማድረግም ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን አማካይነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የመታሰቢያ ዝግጅት ‘’ዳዊት ያቺን ሰዓት’’ በሚል የተዘጋጀ ዶክመንተሪ ፊልም ተመርቋል፡፡

አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ(ባባ)

Tariku baba

በበርካታ የአገራችን ፊልሞች ላይ በመሳተፍ የሚታወቀው ወጣቱ ተዋናይ ታሪኩ ብርሃኑ/ባባ/ በድንገተኛ ህመም ያረፈው ታሕሳስ 2 ቀን 2015 ማለዳ ላይ ነው፡፡ ላውንደሪ ቦይ፣ 300 ሺ፣ ሹገር ማሚ፣ ፍቅር እና ፌስቡክ፣ ኢንጂነሮቹ፣ ህይወቴ፣ ወደው አይሰርቁ፣ ከቃል በላይ፣ ህይወት እና ሳቅ፣ ሀገርሽ ሀገሬ፣ እዮሪካ፣ ከባድ ሚዛን፣ ወፌ ቆመች፣ ይመችሽ ያአራዳ ልጅ 2፣ በቁም ካፈቀርሽኝ፣ እንደ ቀልድ፣ እርቅ ይሁን፣ አስነኪኝ፣ ሞኙ ያአራዳ ልጅ 4፣ ወቶ አደር፣ አባት ሀገር፣ ወጣት በ97 እና ባሌ ማነቅያ፤ ተዋናይ ታሪኩ ብርሃኑ(ባባ) ከተወነባቸው ፊልሞች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። በተጨማሪም ተዋናይ ታሪኩ የጉዳዬ ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ሲሆን፤ በ2ተኛው ለዛ አዋርድ፣ በ7ተኛው አዲሲ ሙዮዚክ አዋርድ እንዲሁም በ12 ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ላይ በምርጥ ተዋናይነት አሸናፊ ነበር።

በሰላሳዎቹ የእድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኘው ተዋናይ ታሪኩ ተውልዶ ያደገው አዲስ አበባ ተክለ ሐይማኖት አካባቢ ሲሆን፤ የአንድ ልጅ አባትም ነበረ። አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ/ባባ/ ባደረበት ድንገተኛ ህመም ምክንያት ታሕሳስ 2/2015 ከዚህ አለም በሞት ተለይቶ በማግስቱ የቀብር ስነስርዓቱ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና የጥበብ አፍቃሪያን በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፀሟል፡፡ ባባ ከዓመታት በፊት የአይን ብሌኑን ለመስጠት ቃል በመግባቱና ተፈጻሚም በመሆኑ፤ በፊልሞቹም ጭምር ለትውልድ የሚተርፍ ስራ በመስራቱ በህይወት ባሉ ሰዎች አይን እና ልብ ውስጥ ህያው ሆኖ ይኖራል።

ዳይሬክተር ዘካርያስ ኃይለማርያም

Zekeriyas hailemariyam

ዘካርያስ ኃይለማርያም ጉደታ በጥበቡአለም ፣ድንቅ አሻራ ያኖረ ለ20 አመት በሚድያው እና በመዝናኛው ዘርፍ በትጋት ያገለገለ ብርቱ ባለሙያ ነበር፡፡ ጎሬ ተወልዶ ልጅነቱን በዚያው ያሳለፈ ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶም ቴአትርን ያጠና ነው፡፡ ዘካርያስ የገና ሙሽራን፤ የዘማሪዋ ወፍ ህልም ሰናይት የተሰኙ ፊልሞችንም የሰራ ነበር፡፡

ህዳር 22 2015አ.ም ህይወቱ ያለፈው ዘካርያስ ኃይለማርያም ቅዳሜ ህዳር 24 2015 በለቡ ገብርኤል ስርአተ–ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡ ከ1978-1998 በሀገራችን የቲቪ ድራማዎች፣ ፊልሞች እና ማስታወቂያዎች ጀርባ ዘካርያስ ነበር፡፡ ለብዙዎች ወደ ሚድያው እና ጥበቡ አለም መምጣት ምክንያት ሆኗል፡፡ ዘካርያስ ኃይለማርያም ባለፉት 37 አመታት በኪነ–ጥበብ እና በመንፈሳዊ አገልግሎት በተለይ መጽሀፍ ቅዱስን በማስተማር ለብዙዎች መትረፍ የቻለ ነበር፡፡ ዘካርያስ በ1998 አ.ም ሙሉ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ሜሪላንድ ክፍለ ግዛት ደረሰ፡፡ በኋላም encore global or psiv በተሰኘ ተቋም ውስጥ የሁነት ከፍተኛ ኤክስፐርት ሆኖ ስራ አገኘ፡፡ ገና በሄደ በ3 ወሩ ስራ ማግኘቱ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር ፡፡ ሀገር ቤት ሳለ 4 የሚሆኑ ፊልሞችን÷ ከ200 በላይ ዶክመንተሪዎችን በርካታ ማስታወቂያዎችን የሰራው ዘካርያስ አሜሪካን ሀገር ከደረሰ በኋላ ከጥበቡ አለም ሙሉ ለሙሉ ወጥቶ በሁነት ዝግጅት ሁለተኛ ዲግሪውን ተቀብሎ በአዲስ ሙያ አዲስ ኑሮን መኖር ጀመረ፡፡ የ 5 አመት እና የ4 አመት ሴት ልጆቹን አይካን እና አይዳን ይዞ ባለቤቱ ገነት ተስፋዬ ጋር በመሆን ኑሮን በሜሪላንድ አሀዱ ብሎ ጀመረ፡፡

1998 ዓ.ም ወደ አሜሪካ የገባው ዘካርያስ በዋናነት የልጆቹን የወደፊት እጣፋንታ ምቹ ለማድረግ በሚል ነበር መኖርያውን ወደ አሜሪካ ለማድረግ ከውሳኔ ላይ የደረሰው ፡፡ በነገራችን ላይ አይካ ልጁ ስትሆን ጸማኮ ከሚለው ፊልም ላይ አይካ የምትባል ገጸ–ባህሪይ ነበረች፡፡ ፀማኮ የካቲት20 1993 የተመረቀ በዘካርያስ ኃይለማርያም የተደረሰ የመጀመርያው ኤትኖግራፊክ ፊልም ሲሆን በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነበር፡፡

አብይ ኤፍሬም

Abiye Ephem

የምክትል ጠቅለሳይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ የነበረው አቶ አብይ ኤፍሬም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው በተገባደደው አመት ጵጉሜ 2 ነው፡፡ ከወላጅ አባቱ ከአቶ ኤፍሬም ሞትባይኖር እና ከእናቱ ከወ/ሮ አሰለፍ ተሰማ በመዲናችን አዲስ አበባ ነሐሴ በገባ በ29ኛው ቀን በንግስት ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ይህችን ዓለም የተቀላቀለው አብይ የቤተሰቦቹ አምሮት ገና ከጅምሩ አገሩንና ወገኑን የሚያስጠራ ሰው ሆኖ ማየት ነበር፡፡ አላመነቱም ስሙን ዐብይ አሉት፡፡ አላቆሙም ብቸኛውን ወንድ ልጃቸውን ለስሙ እንዲመጥን በጠንካራ ሥነ–ምግባር እንዲታነፅ ይደክሙ ነበር፡፡

በወላጅ አባቱ የሥራ ጠባይ ምክንያት ከመቂ ከተማ ጋር ሕብረት የፈፀመው በ-1980 ዓ.ም ነበር፡፡ ለአንድ ዓመት የቄስ ትምህርት ቤት በመግባት እንደመሰሎቹ መደብ ላይ ተቀምጦ ፈደል እና ቁጥር በፍጥነት የመለየት ትምህርት ተከታትሏል፡፡ በ-1981 ዓ.ም ጀምሮ በመቂ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ተከታትሏል፡፡ ወደ የኢትዮጵያ መገኛኛ ብዙሃን በመግባት ዲፕሎማውን እንዳጠናቀቀ በግሉ የሚዲያ ዘርፍ The Sun በተሰኘች ሳምንታዊ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ላይ በሪፖርተርነት ተቀጠረ፡፡ ለአንድ መንፈቅ በሚሆን ዕድሜ ዜና የማምረት ልምምዱን አጠናክሮ ገፋበት፡፡

በ-1995 አጋማሽ ላይ በዩኒቨርስቲው መደበኛ የቀን ተማሪ በመሆን የጋዜጠኝነት ትምህርቱን መማር ጀመረ፡፡የዜ ዕቅድ በመንደፍ የተቀጠረበትን የስራ ሃላፊነት ሳይሸራርፍ ሁለቱንም የዲግሪ ትምህርቶቹን በመከታተል በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ ሃምሌ 1998 ዓ.ም ለመመረቅ በቃ፡፡ በ2001 – 2007 ዓ.ም ጀምሮ በሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን አገልግሏል፡፡ ከየካቲት 2008 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በመዛወር የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን በኃላፊነት መምራት ዕድል የገጠመው ሲሆን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት እና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግል ቆይቶ በድንገተኛ ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለይተል፤ የቀብር ስነ ስራቱም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈጥማል፤/ ምንጭ– ተወዳጅ ሚዲያ/

እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ

Pianist Tege maryam geberu

በዓለም ዙሪያ ባሉ በርካታ የሙዚቃ ኃያስያን እውቅናና አድናቆት ያገኙት ፒያኒስት እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ በ99 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት በተጠናቀቀው ዓመት ነው፡፡እማሆይ ፅጌማርያም በክላሲካል ሙዚቃ ታዋቂ የነበሩና የሚያስደምሙ ሙዚቃዎችን በመጫወት ይታወቃሉ፡፡ለረጅም ዓመታት መንኩሰው ኑሮአቸውን በእየሩሳሌም ያደረጉት እማሆይ ፅጌማርያም ለዘመናት ሲጫወቱበት የኖሩትን ፒያኖ ለያሬድ ሙዚቃ ትምህር ቤት እንዲሰጥላቸው መናዘዘቸውን በስማቸው የተቋቋመው

ፋውንዴሽን አስታውቋል፤ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እዛው እየሩሳሌም ውስጥ ተፈፅሟል፡፡

ቦክሰኛ በቀለ አለሙ (ጋንች)

Gach

ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ መድረክ በመወከል ቀዳሚ ከሆኑት መከካል አንዱ የሆነው ቦክሰኛ በቀለ አለሙ (ጋንች) ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው በተጠናቀቀው ዓመት ማገባደጃ ላይ ነው፡፡

የ3 ጊዜ የኦሎምፒክ ተሳታፊው በቀለ ዓለሙ በ82 ዓመቱ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው። ቦክሰኛ በቀለ በሮም፣ በቶክዮ እና በሜክሲኮ ኦሎምፒክ በቦክስ ዘረፍ ኢትዮጵያን ወክሎ ተሳትፏል። ከ ሜ ሲ ኮ ው ኦሎምፒክ የተሳትፎ ሜዳሊያም ያገኘ ሲሆን የሌጎስ የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆኑም የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።

ቦክሰኛ በቀለ አለሙ የህይወት ታሪኩን የሚዳስስ “ያልተነገረለት የአገር ባለውለታ “በሚል ርዕስ በ2004 ዓ/ም መጽሐፍ ታትሞለታል። በ1933 ታህሳስ 29 የተወለደው ቦክሰኛ በቀለ አለሙ፤ የ11 ልጆች አባት ነበር። የቦክሰኛ በቀለ ዓለሙ የቀብር ስነ–ስርዓት በሸጎሌ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡

ዳይሬክተር አሸብር ካብታሙ

Director Asheber

ትውልዱ በሐረር ከተማ ልዩ ስዩ ስሙ ቀላዳ’ምባ ነው። 1978ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትያትር አርት ከተመረቁ ከመጀመሪያዎቹ አንዱ ነው። እነዚያ ተመራቂዎች እስከዛሬ ድረስ በዲፓርትመንቱ እጅግ ተደናቂውና በተውኔት ዘርፉ እጅግ የገነኑ ባለሙያዎችን ያወጣ ነበር።

ፍሰሃ በላይ ይማም፣ ሙሉጌታ ባልቻ፣ ቶማስ ቶራ፣ ገነት አጥላው፣ ሀይሉ ፀጋዬ፣ ጀማነሽ ሰለሞንና አሸብር ካብታሙ ይጠቀሳሉ። “ወጣቱን በተውኔት ስልጠና ለማብቃት” በነበረ የመንግሰት ፖሊሲ አሸብር ካብታሙ በቀጥታ ወደ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ተመልሶ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶችና አማተር ቡድኖች ስልጠና ሰጥቶ አስመርቋል።አሰበተፈሪ (ጭሮ)፣ ሂርና፣ ገለምሶ፣ ደደር፣ በደኖ፣ ድሬዳዋ ፣ ሐረር፣ ጂጂጋ፣ ኦጋዴን፣ ቀብሪደሃር እና ጎዴ… ወዘተ እየተዘዋወረ በርካቶችን አሰልጥኗል።

የጥበብ ልጆቹ በክብር ይመሰክራሉ፤ ለክብሩ እጅ ይነሳሉ። ዛሬም ድረስ … ዝምተኛው ጀግና አሸብር ~ በተለይ ሐረር ከተማ ላይ እስከ 1985 ዓም ድረስ ከአምስት ዙር በላይ ስልጠናዎች የሰጠ ሲሆን በርካታ ታዋቂ ክበባትም ለማደራጀት ችሏል።አዲስ ገብረማርያም፣ መስፍን ጌታቸው፣ ሠይፉ ፋንታሁንና አብይ ደምለው ወዘተ ከነዚሁ ሰልጣኞቹ መሃከል ነበሩ።

ከ1985ዓ.ም በኋላ በተለይም በምዕራብ ሐረርጌ አሠበ ተፈሪ ከተማ ትልቅ የትያትር ቡድን በመመስረት በየገጠሩ እየገባ በHIV/ ኤድስ ዙሪያ የፈጠረው ንቅናቄ በመንግሥት ጭምር እውቅናን ያሰጠው ነበር። ይሁንና አበዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አሸብር ካብታሙን ያወቀው ሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል ገብቶ ይሰራቸው በነበሩ አይሬሴ፤ አይነኬ ሥራዎች ነበር።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይቀርቡ የነበሩ ተከታታይ ድራማዎች በእርሱ ዳይሬክተርነት የሚሰሩ ነበሩ።አሸብር በተለይም የተከታታይ (Serial) ድራማ ዳይሬክቲንግን በማስተዋወቅ በርካታ ድራማዎችን ሰርቷል። በህዝብ በከፍተኛ ደረጃ የተወደዱ እንደ ገመና ቁጥር 1 እና ገመና ቁጥር 2፣መለከት፣ እንዲሁም ለ15 ዓመታት ሳይቋረጥ እስካሁን የሚቀርበው ችሎት ድራማ በእርሱ ዳይሬክተርነት የተሰሩ ናቸው።

የአዲስ አበባ መስተዳደር ቴሌቪዥን “መስኮት”ን በማስከፈት ለዓመታት ከቁጥር በላይ የሆኑ አጫጭር ድራማዎችን ራሱ እየፃፈ ጭምር በዳይሬክተርነት የሰራው አሸብር ካብታሙ በተለይም በ90ዎቹ በርካታ ፊልሞችን ለዕይታ ያበቃ ድንቅ ባለሙያ ነው። በዚህም ከጀማሪ ተዋናይነት አንስቶ ዛሬ ከፍ ያለ ደረጃ የደረሱ ባለሙያዎችንም ማፍራት የቻለ ሰው ነው። አሸብር ካብታሙ በጠና ታሞ ነው ከዚህ አለም በሞት የተለየው::

 ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም

Ato yakob

አቶ ያዕቆብ ወልደ ማርያም የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅና በኢትዮጵያ የእንግሊዝኛ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ለ56 ዓመታት ያለማቋረጥ በመሥራት የሚታወቁት ጉምቱ ጋዜጠኛ ሲሆኑ፣ በ94 ዓመታቸው ትናንት ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓም ከዘህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

አቶ ያዕቆብ ከሄራልድ ከለቀቁ በኋላ በመነን መጽሔት፤ በቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ፤ በአዲስ ሪፖርተር በኤዲተርነት የሠሩ ሲሆን በሚሠሩትም ሥራ ደስተኛ ነበሩ፡፡ በንጉሡ ዘመን ለ15 ዓመታት፤ በደርግ ዘመን ለ17 ዓመታት፤ ከዚያ በኋላ ላለፉት 24 ዓመታት በጠቅላላ ለ56 ዓመታት በሙያቸው አገልግለዋል፡፡ አቶ ያዕቆብ ከ1983ዓም በኋላ ዘሰን፤ ዘሪፖርተር፤ ፎከስ በተሰኙ የኅትመት ውጤቶች ላይ ሠርተዋል፡፡

አቶ ያዕቆብ የራሳቸውን ግለ ታሪክ በ1995 ዓም አሳትመዋል። አቶ ያዕቆብ ባለትዳርና የ ልጆች አባት ናቸው፡፡ ቀብራቸው ገገ ነሐሴ 17 ቀን 2015 ዓም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተፈጸማል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe