የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ለአምስት አዳዲስ ድርጅቶች የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ለካፒታል ገበያው እንቅስቃሴ ቁልፍ ሚና ለሚኖራቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ የመስጠት ሥነ-ሥርዓት አካሂዷል።
በዚህም ለሲቢኢ ካፒታል አ.ማ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ለወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ አ.ማ፣ ለኢትዮ-ፊደሊቲ ሴኩሪቲስ አ.ማ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አከናዋኝ፣ ለኤች ኤስ ቲ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ሰርቪስስ ኃ.የተ.የግ.ማ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ እና ለኢኴዥን የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ኃ.የተ.የግ.ማ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ፈቃድ ተሰጥቷል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ማሞ ምህረቱ፥ ባለስልጣኑ ለአምስት የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ መስጠቱን አስታውቀዋል።
ይህም ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት መሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ፥ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያለው ገበያው በአግባቡ ሳይሰራበት መቆየቱን በማስታወስ፤ አሁን ግን የካፒታል ገበያ ባለስልጣንን በማቋቋምና የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሁኑ ፈቃድ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያዎቹ የኢንቨስትመንት ባንክ እና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አከናዋኝ ድርጅቶች ፈቃድ የተሰጠበት እና አጠቃላይ ፈቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎችን ቁጥር ከ4 ወደ 9 ከፍ ያደረገ ነው።
5 ድርጅቶች የካፒታል ገበያ አገልግሎት ፈቃድ ተሰጣቸው

