ትዳር መስርተው ከሆነ መልካም ነው፡፡ ከትዳርዎ ደግሞ ፍሬ አግኝተው ከሆነ እጅግ በጣም እድለኛ ነዎት፡፡ ይህን መልካም ዕድል እስከመጨረሻ የህይወትዎ ጫፍ ለመድረስና ልጆችዎን ለወግ ለማብቃት ለልጆችዎ ወላጅ ብቻ ሳይሆን ጓደኛ መሆን አለብዎት፡፡
ልጆችዎን ጓደኛ ለማድረግ የሚጠበቅብዎት እጅግም ቀላል ያልሆነ እጅግም ያልከበደ ተነሳሽ መሆን አለብዎት፡፡ በቤትዎ ውስጥ የጋራ የሆነ ጊዜ ሊኖርዎት ይገባል፡፡ በአብሮነት ቆይታዎ ልጅዎ ከጠፋ ከመገሰፅ ወደኋላ አይበሉ፡፡ መገሰፅ ማለት ልጅ ማድረግ ያለበትንና የሌለበትን እንዲያውቅ ያደርጋል እንጂ አይጎዳም፡፡ ግሳፄው ካልሰራ መቆጣት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ቁጣ አይሆንምን ለልጆች ይጠቁማል፡፡
ስለልጅዎ ውሎ ለመጠየቅ ካሰቡ በቅድሚያ ስለ ራስዎ ውሎ ይናገሩ፡፡ ቢቻል ያስከፋዎት፣ ያበሳጨዎት ያጠፉት ጉዳይ ካለ አይሸሽጓቸው፡፡ ምክንያቱም ለልጅዎ በድፍረት ትክክልም ሆነ ትክክል ያልሆኑ ገጠመኞቹን ሊነግርዎት ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ልጅዎን ግልፅነትን እንዲለምድና እንዲያዳብር ያደርጋል፡፡
ለልጅዎ ግልፅ መሆን ይጠበቅብዎታል፡፡ ግልፅ መሆን ሲባል ግን ገደብ ሊኖርዎ ይገባል፡፡ የልጅዎን እድሜ በማገናዘብ ግልፅ ይሁኑ፡፡ ከባህል ከወግ ያልወጣ ግን ልጆች ሊያውቁት የሚገባን ነገር ይለዩ፡፡ ያለበለዚያ በግልፅነት ሰበብ ያላስፈላጊ ነገሮችን ልጆችዎ እንዳያዩና ለመሞከር እንዳይጋበዙ ልብ ማለት አለብዎ፡፡
በቤት ውስጥ ልጆች ሀላፊነትና የቤተሰብ አባል ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ መሆናቸውን እንዲያውቁ እድሜያቸውን ያማከለ ሀላፊነት መስጠት፡፡ ለምሳሌ እድሜያቸው ከሰባት አመት በታች የሆኑ ህፃናትን ዕቃ በማቀበል ከቦታ ቦታ በማንሳት አቧራ ከወንበርና ጠረጴዛ ላይ ማንሳት ማስለመድ፡፡ እድሜያቸው ከፍ ሲል ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችን በመስጠት ሀላፊነትን እንዲያውቁ ማድረግ፡፡
የገንዘብ አጠቃቀምና አያያዝን ማስተማርም ይኖርብዎታል፡፡ አስፈላጊ ነው ብለው ልጆች የሚጠይቁትን ብር በመስጠት ብቻ አለማለፍ፤ አለማስለመድም፡፡ ከዚህ ይልቅ ስራ በሰሩ ቁጥር የሚታሰብ ክፍያ መክፈል፡፡
ለልጆችዎ ወላጅ ብቻ ሳይሆን ጓደኛ ለመሆን

