የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ዘይሴ ቀበሌ፤ ከሞሪንጋ ወይም ሽፈራው ተክል ዘይት ማምመረት የሚያስችል ፋብሪካ ሥራ ሊጀምር መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ በዋናነት ተግባራዊ የተደረገው እና ፋብሪካው የተገነባበት ተክሉ በስፋት የሚበቅልበት አርባ ምንጭ ከተማ ዘይሴ ቀበሌ ነው፡፡
የጣሊያን መንግሥት፣ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዲስትሪ ልማት ድርጅት እና የደቡብ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ያስገነቡት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የኢንደስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይ እና የፕሮጀክቱ ቴክኒካል አማካሪ ዶክተር ለምለም ሲሳይ፤ “የሞሪንጋ ተክል ወይም ሽፈራው በአካባቢው ማህበረሰብ “አለኮ” በመባል የሚታወቅ ቢሆንም ከምግብነት ባለፍ በሀገር አቀፍ እና በአለም ገበያ ላይ ተፈላጊ መሆኑ ባለመታወቁ ብዙ ትኩረት አልተሰጠው” ብለዋል፡፡
“የፕሮጀክቱ ዋና አላማ ማህበረሰቡ የሚያውቀውን ተክል በማምረት እና በማቀነባበር ወደ አለም ገበያ እንዲቀርብ ማድረግ ነው” ሲሉም አንስተዋል፡፡
ተክሉ ማህበረሰቡ ለዕለት ተእለት ከሚጠቀምበት ምግብ ባለፈ በፋብሪካ በማቀነባበር የሻይቅጠል ምርት፣ ዘይት እንዲሁም በኪኒኒ መልክ መጠቅም እንደሚቻል በውስጡም የተለያዩ ቫይታሚኖች እንዳሉት፤ በአርባ ምጭ ዩንቨርስቲ በተደረገው ጥናት እና ምርምር መረጋገጡን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
የሞሪንጋ ወይም የሽፈራው ተክልን በዘመናዊ መልኩ አቀነባብሮ እና አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ለኢኮኖሚው ከሚያበረክተው አስተዋጾ በተጨማሪ የጤና ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ፤ በተባበሩት መንግሥታት የኢንደስትሪ ልማት ድርጅት የምግብ ዋስትና እና የመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ፌሪድ ኮንጎ ናቸው፡፡
ተክሉ በወቅቶች መፈራረቅ የማይደርቅ በመሆኑ የምግብ ዋስትናን በማረጋጋጥ አስተዋጾ እንዳለው አቶ ፌሪድ ገልጸዋል፡፡
“ፕሮጀክቱ በገጠር የሚገኙ ሴቶች ራሳቸውን ከማብቃት ባለፍ ቤተሰባቸውን በኢኮኖሚ እንዲደግፉ ያስችላቸዋል” ነው ያሉት፡፡
ሞሪንጋን ወይም ሽፈራውን ለምግብነት ከመጠቅም ባለፈ የተለያዩ የብስኩት አይነቶችን መስራት እንደሚቻልም አንስተው፤ “ከሌሎች ምግቦች ጋር በመቀላቀል ለተማሪዎች ምግባ ላይ መጠቀም ይቻላል” ሲሉም ለአሐዱ አስረድተዋል፡፡
መሠረተ ልማቶችን በማሟላት እና ፖሊሲ በማውጣት የሀገር ውስጥ ገበያ ትስስርን ከመፍጠር አንጻር የክልሉ መንግሥት የሚያደርገው ትብብርም የሚበረታታ መሆኑን ተናግረው፤ ፋብሪካው በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምርም ጠቁመዋል፡፡

