251 ኮሚዩኒኬሽን ኤንድ ማርኬቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ይዘት እና ዓላማ ያላቸው ዝግጅቶች አንዱ የሆነውን አመታዊ የሪል እስቴት እና የቤት ኤክስፖ ለሰባተኛ ጊዜ ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉትን ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ከታህሳስ ወር 18, 19 እና 20 ቀን 2017 በሸራተን አዲስ ኢንተርናሽናል ሆቴል ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚያደርግ አሰታወቀ።
ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጊ ኢኮኖሚ እያስመዘገበች ያለችበት ወቅት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚሁ ረገድ በቤት ልማት ዘርፍም እያሳደገች ያለችውን እድገት ተከትሎ የግሉ ዘርፍ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ እንዲረዳ ታስቦ መዘጋጀት የጀመረው ኢቲ ሪል ስቴት እና ሆም ኤክስፖ የሪል ስቴት አልሚዎችን ከቤት ባለቤቶች፣ ከገዥዎች፣ ከሻጮች፣ እና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኝ ቀዳሚ ኤግዚቢሽን ነው።
ኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ለመደገፍና የህዝብ አገልግሎቶችን በተለይም የመሰረተ ልማትን ጥራት ለማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን የሚያመቻች አዋጅ በቁጥር 1076/2018 ማፅደቋ ይታወቃል። ይህ ኤክስፖም ለዚህ አላማ አጋዥ ግብእት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ይህ ለሦስት ቀናት የሚቆየው ታላቅ ዝግጅት በኢትዮጵያ የሪል ስቴት እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ባለድርሻ አካላትን ማለትም ከፍተኛ አልሚዎችን፣ ባለሀብቶችን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ የቤት ገንቢዎችን እና የቤተ ውበት ባለሙያዎችን ጨምሮ በአንድ ላይ ያሰባስባል። ኤክስፖው በሪል እስቴት ዘርፍ ውስጥ ያሉ አዳዲስ እድገቶችን፣ ፈጠራዎችን እና የኢንቨስትመንት እድሎችን ለማሳየት ያለመ ሲሆን በኢንዱስትሪ መሪዎች መካከል ትስስር እና ትብብርን ይፈጥራል።
ይህ የተገለጸው በዛሬው እለት በቱሊፕ ኢን ሆቴል በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲሆን አዘጋጆቹ የኤግዚቢሽኑን ዓላማዎች እና የዘንድሮውን ዝግጅት ዋና ዋና ነጥቦችን ዘርዝረዋል። ኮንፈረንሱ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብርን እና የኢትዮጵያን የቤትና የከተማ ልማት ለማሳደግ ያለውን ጠቀሜታ አፅንዖት ሰጥቶበታል።
የ251 ኮሙዩኒኬሽን መስራች አቶ አዲስ አለማየሁ “የዘንድሮው ኤክስፖ በኢትዮጵያ ሪል ስቴት ዘርፍ ትልቅ ፋይዳ ያለው ክስተት ሲሆን በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸውን ተዋናዮችን ያሰባስባል። ዘላቂ ልማትን፣ ፈጠራን እና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መስተጋብራዊ መድረክ በመፍጠር የዘርፉን እድገት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነን።
በ7ኛው አመታዊ ሪል እስቴት እና የቤት ኤክስፖ ከኤግዚብሽኑ በተጨማሪ በኢንዱስትሪው ላይ ከሚገኙ ዋና ባለድርሻ አካላት እና ከመንግስት ተወካዮች ጋር የመገናኘት እድል የሚፈጠር ሲሆን የፓናል ውይይትም ይኖራል። ኤግዚቢሽኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመቅረፍ ወሳኝ የሆኑ ዘላቂ የግንባታ አሰራሮችን፣ ተመጣጣኝ የቤት መፍትሄዎችን እና የፋይናንስ አማራጮችን የሚያጎላ ሲሆን የሚዲያ ተወካዮች እና የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች በኤግዚቢሽኑ ላይ ተገኝተው በኢትዮጵያ የሪል ስቴት ኢንደስትሪውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀርጹ አዳዲስ ፈጠራዎችን እንዲታደሙ ጥሪ ቀርቧል።
7ኛው አመታዊ ሪል እስቴት እና የቤት ኤክስፖ ከታህሳስ 27-29 ቀን 2024 በሸራተን አዲስ እንደሚከፈት ተገለፀ

