‹እስክስታ እችላለሁ› በኢትዮጵያ ለእስራኤል አምባሳደር  ከቁም ነገር መፅሔት የቀረቡ የመዝናኛ ጥያቄዎች

‹እስክስታ እችላለሁ›

በኢትዮጵያ ለእስራኤል አምባሳደር  ከቁም ነገር መፅሔት የቀረቡ የመዝናኛ ጥያቄዎች

ቁም ነገር፦ አሁን ያሉበት ሙያ ላይ ባይሆኑ በሌላ ሙያ ላይ ምን  ሊሆኑ ይችሉ ነበር?

አምባሳደር አብርሃም፦ የልጅነቴን ምኞቴ ትምህርት ቤት እያለው ምኞቴ የነበረው  በህክምና ዶክተር ሆኜ ማገልገል ነበረ፡፡ በአንድ ወቅት ላይ ደግሞ

በፊዚክስ ጥሩ ውጤት አመጣ ሰለነበር ፓይለት መሆን እመኝ ነበር፡፡ ሁለቱም አልሆኑም፤ ነገር ግን ማህበራዊ ችግሮችን እንዳክም አድርጎኛል፡፡ እንደልጅነቴ የተመኘሁትን   የሰውን በሽታ ደዌን መፈወስ ባልችልም  የማህበራዊ በሽታን የመፈወስ እድል አግኝቼ በዚህ ሁኔታ ላይ በመስራት ላይ ነኝ፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡

ቁም ነገር፦  ሙዚቃ ይሰማሉ?

አምባሳደር አብርሃም፦ ሙዚቃ  እሰማለሁ ለማለት ያስቸግረኛል፤ ግን አንዳንዴ እሰማለሁ፡፡

ቁም ነገር፦ እንደው መዝፈን ግዴታ ቢሆንብዎት የማንን ዝፈን ይዘፍናሉ?

አምባሳደር አብርሃም፦ አይ ግዴታ ቢሆንም  ድምጽ የለኝም፤ ድምፅ እንደሌለኝ በመጀመሪያ ማሳወቅ አለብኝ ፡፡ድምጽ የለኝም እስክስታ ግን እችላለሁ፡፡ የጎንደር እስክስታ እችላለሁ፤  ስለዚህ ዝፈን ሞክር ከተባልኩ የይርጋዱባለ ዘፈን ነው የምሞክረው፡፡ ከይርጋ ዱባለ ሌላ  የእነ ጥላሁን ገሰሰ፤ የእነ መሀመድ አህመድ እና አምሳለ ምትኬ የእነሱ ሙዚቃ ሁሉ አልፎ አልፎ ሰማለው፤ በተለይ የድሮ የኔ ትውልድ የነበረበትን ሙዚቃ እነ ነዋይ ደበበን እሰማለሁ፡፡ ግን እኔ መቼም በግዴታ አልሞክራትም፤እስክስታውን ግን ችግር የለውም፡፡

ቁም ነገር፦ ከፖለቲካ እና ከሃይማኖት ክርክር የትኛውን ይመርጣሉ?

አምባሳደር አብርሃም፦ እንደው ቢመጣ ቢመጣ የፖለቲካን ክርክር እመርጣለው፡፡ ምክንያቱም የሃይማኖት ክርክር መሰረቱ እምነት ነው፡፡ መሰረቱ እምነት ስለሆነ አንድ ሰው አምናለሁ ካለ ማሸነፍ አስቸጋሪ ነው፡፡በፖለቲካ በኩል ግን የሚያሳምን  ሳይንሳዊ ትንታኔዎችንም አቅርቦ ማሳመንም የማመንም ሁኔታ ሊመጣ ስለሚችል የፖለቲካን ክርክር እመርጣለሁ፡፡

ቁም ነገር፦ በቀን ስንት ብር ያጠፋሉ? በግምት በአንድ ቀን ውስጥ፤ ለምሳሌ ትላንትና?

አምባሳደር አብርሃም፦ ትላንትና ወጪ ያደረግኩ አይመስለኝም፤ ቢሮ ገባሁ ከቢሮ ተመለስኩ፤ ከቤቴ የተዘጋጀውን በላሁ፤ ጠጣሁ፤ በቃ፤ ወጪ የደረግሁት  ዛሬ ነው፡፡  አንድ ሺህ ሶስት መቶ ብር ወጪ አድርጌያለሁ፡፡

ቁም ነገር፦  አንድ ሰው በህይወቱ ስንት ጊዜ ፍቅር ሊይዘው ይችላል ብለው ያስባሉል?

አምባሳደር አብርሃም፦ ፍቅር  ከባድ ጥያቄ ነው ፤እኔ በመሰረቱ በህይወቴ አንድ ጊዜ ፍቅር ይዞኛል፤ ሃይ ስኩል እያለሁ ፡፡ ፍቅር ካስያዘችኝ ልጅ  ጋር ተጋብቼ ትዳር መስርቼ ልጆችን ወልጄ፤ የልጅ ልጆችን አይተናል፡፡ ስለዚህ በሌላው ሰው መግባት አልችልም፤ ማወቅም አልችልም፤ በራሴ ተሞክሮ ግን አንድ ጊዜ በህይወቴ ፍቅር ይዞኛል፤

ቁም ነገር፦ ማን ይባላሉ ባለቤትዎ?

አምባሳደር አብርሃም፦ ባለቤቴ ሊያ ትባላለች፤ እዚሁ ኤምባሲያችን ውስጥ ትሰራለች፡፡

ቁም ነገር፦  የአዲስ አበባ ሰፈሮችን ምን ያህል ያውቋቸዋል? ለምሳሌ ወርቁ ሰፈር? አለምፀሃይ ድልድይ ? የት አካባቢ ይገኛሉ?

አምባሳደር አብርሃም፦ ወርቁ ሰፈር የሚባል አካባቢ አለ? አላውቀውም ወርቁ ሰፈርን፤ እንግዲህ ምናልባት ቀድሞ ፒያሳ የወርቅ ሱቆች ይበዙ ስለነበር እዚያ አካባቢ ይሆን?፤ አለም ጸሃይ ድልድይ የሚባል አካባቢ አለ? አላውቀውም፤

ቁም ነገር፦ ከሞቱ ሰዎች አንድ ጠቃሚ ሰው አስነሱ ቢባሉ ማንን ያስነሳሉ?

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር

አምባሳደር አብርሃም፦ ካለፉ ሰዎች ለዚች አለም የራሳቸው የሆነ ኮንትሪቢሽን አድርገው ያለፉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ አንድ ብቻ ከተባለ  አልበርት አንስታይን እጠቅሳለሁ፡፡

ቁም ነገር፦  በህልምዎ አይተው በእውን ያጋጠሙት ነገር አለ?

አምባሳደር አብርሃም፦ በህልሜ አይቼው በእውን ያጋጠመኝ ነገር የለም፤ ህልም ሽልፎ አልፎ አያለሁ፡፡ ግን ብዙ ጊዜ በህልም አልመረኮዝም፤ መጥፎ ህልም አይቼው  አልፈራም፤ ጥሩ ህልምም አየሁ ብዬ አልደሰትም፡፡

ቁም ነገር፦ ጠባብ ጫማ ካደረገ ሰው እና በጣም ሽንቱን ከወጠረው ሰው የበለጠ የሚጨነቀው ማነው ብለው ያስባሉ?

አምባሳደር አብርሃም፦ ይሄ አደገኛ ጥያቄ  ነው፤ ሽንቱን የወጠረው ሰው የበለጠ ይጨነቃል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሽንት መጥፎ ነው፡፡

ቁም ነገር፦  ስምዎ አብርሃም ባይሆን ማን እንዲሆን  ይመርጡ ነበር?

አምባሳደር አብርሃም፦ ሌላ ስም? አይ በእውነት በወላጆቼ የተሰጠኝ ስም ስለሆነ  ተደስቼ ተቀብዬ እጠቀምበታለሁ፡፡ መቼም ከአብርሃም የበለጠ ስም ምን ብዬ ልምረጥ? አብርሃም እንግዲህ በታሪክ በኩል የሄድን እንደሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሄር የመረጠው ስም  ነው ፤እና እግዚአብሄር የመረጠውንን ስም ትቼ የሰው ስም ምርጫ መግባት ምን አስፈለገኝ? ስለዚህ እኔ ወላጆቼ ክሰውኛል፤ ይሄን ስም አንድም ቀን እቀይራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ለወደፊቱም አላስብም፡፡

ቁም ነገር፦ በአሁኑ ወቅት ኑሮ ተወዳል ይባላል፤ እናም በአሁኑ ወቅት ገበያ ላይ ያሉ ሸቀጦች  ምን ያህል ያውቃሉ? ለምሳሌ በርበሬ በፈረሱላ ስንት ነው? ጋቢ ሰንት ይሸጣል? ስኳር በኪሎ?

አምባሳደር አብርሃም፦ /ሳቅ/በርበሬ በፈረሱላ በእውነት አላውቀውም፤ ጋቢ ስንት ይሸጣል? በእውነት አላውቀውም፤ ስኳርም አሁን ያለው ዋጋ አላውቀውም፤  ምክንያቱም ገበያ  አልወጣም፡፡ግን እንደምሰማው ከሆነ ግን  ተወደዋል ይሉኛል፡፡

ቁም ነገር፦  እጅግ አድርገን ነው የምናመሰግነው ክቡር አምባሳደር ለሰጡን ጊዜ፡፡

አምባሳደር አብርሃም፦ ለኤምባሲያችን ድረስ ስለመጣችሁ እኔም በጣም አመሰግናችኋለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe