የጀርመን መራሄ መንግሥት በኢራን ጦርነት ምክንያት ዶናልድ ትራምፕን ከተቹ ከቀናት በኋላ የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት 5,000 ወታደሮችን ከጀርመን ለማስወጣት ማቀዱን አስታወቀ።
መስሪያ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ፤ አሜሪካ በኢራን ተደራዳሪዎች “ተዋርዳለች” በማለት የዋሽንግተንን አካሄድ ከተቹ ከቀናት በኋላ ነው።
ሐሙስ ዕለት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ መርዝን “አሳፋሪ ሥራ እየሰራ ነው” ሲሉ ነቅፈው የስደተኞች እና ኢነርጂ ጨምሮ “የሁሉም ዓይነቶች ችግሮች” አሉበት ሲሉ ኮንነዋቸዋል። ትራምፕ በጣሊያን እና ስፔን የሚገኙ ወታደሮችን ለማስወጣት ሃሳብ አንዳላቸው ገልጸዋል።
አሜሪካ፣ ጀርመን ውስጥ ከፍተኛ የሠራዊት አባላትን ያሰፈረች ሲሆን እስከ በመላ አገሪቱ በሚገኙ ጦር ሰፈሮች 36,000 ወታደሮች እንዳሏት ታህሳሥ ላይ የወጣ መረጃ ያመልክታል ።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሺን ፓርኔል በሰጡት መግለጫ ውሳኔው የተላለፈው በመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት መሆኑን ተናግረዋል።
“ይህ ውሳኔ በአውሮፓ ውስጥ የመምሪያውን የኃይል አቀማመጥ በጥልቀት በመገምገም የቲያትር መስፈርቶችን እና በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው” ብለዋል።
ወታደሮቹ መቼ ጀርመንን ለቅቀው እንደሚወጡ ሲያስረዱም “ከስድስት ወራት እስከ 12 ወራት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ተጠቃልለው ይወጣሉ ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ ተናግረዋል።በሌላ በኩል አሜሪካ ቴህራንን ወደ ድርድር ለማምጣት በሚል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን አግዳለች።
ኢራን በበኩሏ በወሽመጡ ላይ የሚደረግን የመርከቦች እንቅስቃሴ በማገዷ የነዳጅ ዘይት፣ የአፈር ማዳበሪያ እንዲሁም መድሃኒቶች እና ሌሎች የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ንረት አጋጥሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትራምፕ አስተዳደር በሁለቱ አገራት መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ምክንያት ጦርነቱ መቋረጡን አስታውቋል።
ትራምፕ አርብ ዕለት በፍሎሪዳ ባደረጉት ንግግር ተቺዎቻቸው አሜሪካ ከኢራን ጋር ያካሄደችውን ጦርነት አላሸነፈችም ብለው መናገራቸውን በመጥቀስ ይህ “ክህደት” ነው ብለዋል።//
አሜሪካ 5,000 ወታደሮቿን ከጀርመን ልታስወጣ ነው

