በባሕር ዳር ከተማ በተከሰተ የእሳት አደጋ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
(አብመድ) አደጋው መንስኤ እና የደረሰው ጉዳት ላይ የማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡
እንደ ፖሊስ መረጃ ቃጠሎው የተከሰተው ትናንት ማታ 5፡00 አካባቢ ነው፡፡ በዚህም የሰው ሕይወት ማለፉን፤ በአካል እና በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ለአብመድ አስታውቋል፡፡ ስለአደጋው መንስኤ እና ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ጉዳዩን እያጣራ መሆኑንም ነው መምሪያው የገለጸው፡፡
ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ አካላትን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የገለጸው ፖሊስ መምሪያው ዝርዝር መረጃውን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ ከወራት በፊት በደረሰ የእሳት አደጋ በርካታ ቤቶች መቃጠላቸው እና የከተማ አስተዳደሩና የከተማዋ ነዋሪዎች ተጎጂዎችን የማቋቋም ሥራ እያከናወኑ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

