‹‹የዓመቱ ሰዎች››

ኢንጂነር ታከለ ኡማ
በ2010 ዓ.ም የምርጫ ጊዜውን ያጠናቀቀው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ከንቲባው ተከታዩ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ አቶ ታከለ ኡማ እንዲመሩት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሸሙትት እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት መግቢያ ላይ ነበር፡፡ያም ሆኖ አቶ ታከለ ወደ ፅ/ቤታቸው ከገቡበት ዕለት ጀምሮ ወቀሳ ያስተናገዱ ከንቲባ ናቸው፤ ኢንጂነሩ ወደ ከንቲባነት የመጡት የከተማ አስተዳደሩ ተመራጭ ሳይሆኑ ብቻ ሳይሆን የምክር ቤት አባል ሳይሆኑም ጭምር ስለነበር አመጣጣቸው ህገወጥ ነው በሚል የተለያዩ ትችቶችን አስተናግደዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ታከለን ለመሾም ብለው የከተማ አስተዳደሩን ቻርተር በተወካዮች ምክር ቤት ቤት ማሻሻያ አድርገውበታል፤ እስከ ዛሬ ከነበረው የከንቲባ አሻሻም በተለየ መልኩ ምክር ቤቱን እስከ መጪው ምርጫ ድረስ እንዲቀጥል ሲያደርጉ ከንቲባውን በተመለከተ የምክር ቤት አባል ባይሆንም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሚል አንቀፀ በመጨመር ቦታውን እንዲይዙ አድርገዋል በሚል ይተቻሉ፡፡
ይህንኑ በተለመከተ የምክር ቤት አባል ያልሆነ ሰው በከንቲባነት ሾመዋል ተብለው ተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹አልሾምኩም፤ ምደባ ነው ያካሄድነው› የሚል ምላሽ ነበር በወቅቱ የሰጡት፡፡ በኢህአዴግ ቋንቋ ሹመትና ምደባ ልዩነታቸው ግልጽ አይደለም፡፡ ኢንጂነር ታከለ በከንቲባነት ወደ ቢሮ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በልዩ ልዩ መልኩ የከተማ ነዋሪዎችን ችግሮች ለመቅረፍ ከቢሮ ውጭ የሚያሳልፉ ከንቲባ መሆናቸውን ያሳዩ ሲሆን በተለይም በአረጋውያን ቤቶች እድሳትና፤ የአዲስ አበባ ስታዲየም የደጋፊዎች የፀጥታ መደፍረስ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊነታቸውን አሳይተዋል፤
በቅርቡም የቀጣዩን ዓመት የትምህርት ዘመን መጀመር ምክንያት በማድረግ በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶችን ያሳደረሱ ሲሆን የተማሪዎችን ቁሳቁስም በመንግስት እንዲሸፈን ለማድረግ የተለያዩ ድርጅቶችን በማስተባበር ውጤታማ ስራ ስለመስራታቸው ይነገርላቸዋል፡፡ የከተማዋን ገፅታ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዎ እያሳረፈ የመጣውን የጎዳና ተዳዳሪነትና የተረጂነትን መንፈስ ለማስቆምም የጎዳና ተዳዳሪውን በዘላቂነት ለማቋቋምና ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የ100 ሚሊዮን ብር ከከተማ አስተዳደሩ በጀት መመደባቸው ችግሩን ከስረ መሠረቱ ለመቅረፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ እንኳ የታቀደለትንና የተወራለትን ያህል ባይሆንም የከተማዋን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት ያግዛል የተባለ የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ከህብረተሰቡ ለማሰባሰብ ዘመቻ ቢጀመርም የታሰበውን ያህል ውጤታማ አለመሆኑ ተነግሯል፡፡
ኢንጂነር ታከለ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ ባለስልጣን ሳይሆን እንደ አንድ የከተማ ዜጋ ታች ወርደው ለመስራትና ሰርተው ለመስራት ያላቸው ፍላጎት በብዙዎች ዘንድ የተደነቀ ይሁን እንጂ ከፀጥታ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ አስተዳደራቸው በተለይም የባለአደራው ምክር ቤት አባላት ላይ የሚደርሰው ማዋከብና ህግን ያልተከተለ ተግባራት ላይ ስማቸው በበጎ እንዳይነሳ ካደረጉ ጉዳዮች መሀከል ይጠቀሳል፡፡ ኢንጂነር ታከለ ከባለአደራው ምክር ቤት ሰብሳቢ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር በፅ/ቤታቸው ተገናኝተው መነጋገር መቻላቸው በበጎ ጎኑ የሚጠቀስ ተግባር ቢሆንም ከውይይታቸው በኋላ ህግን ተከትሎ መግለጫ ለመስጠት በየሆቴሉ እንዳይችል የተደረገበት አግባብ ብዙዎች አሳዝኗል፡፡ ከዚህ አልፎም በፅ/ቤቱ ጋዜጣዊ መግላጫ ለመስጠት በጠራበት ወቅት ወጣቶች ጋዜጣዊ መግለጫውን ሲያውኩ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ህግ የማስከበር ሀላፊነቱን አለመወጣቱ የከተማ አስተዳደሩን ያስወቀሰ ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ከዚህ ሌላም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለአስር ዓመታት ያህል ሲቆጥቡ ቆይተው የኮንዶሚኒየም ቤት ይሰጠናል ብለው ተስፋ ያደረጉበት የቤት እጣ የውሃ ሽታ የመሆኑ ጉዳይ ከንቲባውን አጣብቂኝ ውስጥ ከከተታቸው ጉዳዮች መሀል ይጠቀሳል፤
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ድንበር የማካከል ጉዳይም በከንቲባውና በድርጅታቸው ላይ ትችት ካስነሱ ጉዳዮች መሀከል ይጠቀሳል፡፡ የሁለቱን አስተዳደር ወሰኖችን ለመወሰን ከተሰየሙት ሰዎች መሀከል ከንቲባው የህዝብ ውክልና ሳኖራቸውና በምርጫ ሳይመረጡ ይህንን ትልቅና አደገኛ አጀንዳ እንዲወስኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሾማቸው ጉዳይ አነጋጋሪነቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡
ከንቲባው ምን እንኳ በተላያዩ የኪነጥብብ ዝግጅቶች ላይ በመገኘት ያልተጠበቁ ንግግሮችንና ሽልማቶችን በመስጠት የመገናኛ ብዙሃን መነጋጋሪያ ቢሆኑም ይህ የግል ዝናን ፍለጋ የሚከናውኑት ተግባር ነው በሚል ከእህት ድርጅታቸው ሳይቅር እየተተቹበት ነው፡፡ በቅርቡ ለአንድ በመፅሐፍ ንግድ ላይ ለተሰማራ ወጣት የከተማ አስተዳደሩን መኪና መሸለማቸው እንዲሁም ለተለያዩ ግጥም ምሽት አዘጋጆች እስከ 100 ሺ ብር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው እንዲሁም የኮንዶሚኒየም ቤት ስጦታ ማበርከታቸው የህጋዊነት ጥያቄ እያነሳባቸው ነው፡፡ያም ሆኖ ከንቲባው በያዝነው ዓመት አነጋጋሪነታቸው እንደቀጠለ ይገኛል፡፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe