‹‹የዓመቱ ሰዎች››

አቶ ልደቱ አያሌው
አቶ ልደቱ አያሌው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስት ሩብ ክፍለ ዘመን ቆይቷል፡፡ ከመአህድ የወጣቶች ሊግ እስከ ቅንጅት ኢዴፖ ድረስ ልደቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ ጥርሱን ነግሏል ለማለት ይቻላል፡፡ልደቱ በ1992 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ዋዜማ የተመሰረተው ኢዴፖ ፖርቲውን ወክሎ ለክርክር ወደ መድረክ ብቅ ሲል በዚያ ወጣትነት እድሜው የኢትዮጵያ ፖለቲካን የሚተነትነው አዲስ ትኩስ ሀይል መምጣቱን አስመስክሮ ነበር፡፡ ልደቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በደንብ የታወቀውና ችላ ሊሉት የማይችሉት ፖለቲካኛ መሆኑን ያሳየው በምርጫ 97 ወቅት ቅንጅትን ወክሎ በተደረጉ የክርክር መድረኮች ላይ በሚሰጣቸው ትንታኔዎችና መግለጫዎቹ ነው፡፡
በምርጫ 97 የቅንጅትን መፍረስና የፖለቲካኞቹ ወደ እስር ቤት መግባት ተከትሎ ልደቱ አያሌው ከባድ የሆነ ወቀሳና ክህደት እንደፈፀመ ሲነገር የኖረ ቢሆንም ልደቱ ግን የመርህ ሰው መሆኑን በመግለፅ በየድረኮቹ ከመርህ ውጭ የሰራው አንዳችም ነገር አለመኖሩን በማስረዳት ለ13 ዓመታት ያህል ፀንቶ የኖረ ፖለቲካኛ ነው፡፡ ብዙዎች ከቅንጅት መፍረስ ጋር በተያያዘ የወያኔ ተላላኪና ሰላይ አድረገው መፅሐፍ በመፃፍ ጭምር ቢገልፁትም እሱም ምላሹን በመፅሐፍ መልክ አቅርቦ ተከራክሯል፡፡
ልደቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከመደገፍና ከመቃወም ሌላ ሶስተኛ አማራጭ እንዳለ ያሳየ የፖለቲካ ሰው ሲሆን በመፅሐፍ መልክ ሳይቀር ሀሳቡን በማቅረብ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተከተሉትን የመደመር ፍልስፍና ቀድሞ ያሳየ አድርገው የሚቆጥሩት ብዙዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጭፍን ደጋፊና ጭፍን ተቃዋሚ ብቻ በሞላበት ወቅት ልደቱ በምክንያት መቃወምና በምክንያት መደገፍን ያሳየ ባለ ራዕይ አድርገው የሚቆጥሩት አሉ፡፡
ልደቱ አያሌው የፖለቲካ ስብዕና ብዙዎችን ያስገርማል፡፡ በመድረክ ክርክሩ ወቅትም ሆነ በቃለ ምልልስ ላይ እንደሌሎቹ የፖለቲካ ሰዎች የማይቆጣ፤ የማይናደድ፤ሀሳቡን በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ለማስተላለፍ የማቸገር መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ልደቱ በየትኛውም የፖለቲካ መድረክ ላይ የሰዎችን ስም አንስቶ በስብዕናቸው ሲያንኳስሳቸው ተሰምቶ እንደማይታወቅ የሚጠቅሱ ብዙዎች ናቸው፡፡
ልደቱ ከ13 ዓመታት በኋላ በቅርቡ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ፖለቲካ መድረኩ የተመለሰ ሲሆን ፖርቲውን በህገ ወጥ መንግድ ለማፍረስና ፖርቲ አልባ ለማድረግ ኢዴፖ አመራሮች ከኢዜማ ጋር ውህደት ስለመፈፀማቸው የተነገረ ቢሆንም ልደቱ ግን መርህን በመከተል ፖርቲውን ከመክሰም ሊታደግ መቻሉ ሰሞኑን ይፋ ሆኗል፡፡ ይልቁንም የፖርቲውን ስም ብቻ ሳይሆን ድርጅታዊ ንብረቶችንና በባንክ የተቀመጠ ገንዘብን በወሰደው ኢዜማ ላይ የመረረ ትችት ከመሰንዘር ይልቅ ‹ባለማወቅ ሊሆን ስለሚችል› በማለት ንብረቶቻቸው እንዲመለሱ የጠየቀበት መንገድ የልደቱን ብስለትና ስብዕና አግዝፎታል፤
ልደቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስና የመጀመሪያ የሆነ ደንብ በፖርቲው በኢዴፖ ውስጥ ያስለመደ ፖለቲከኛ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡በፖርቲው ህገ ደንብ ውስጥ ከሁለት ጊዜ በላይ የድርጅት ሊቀመንበር መሆን እንዳይቻል በማስቀመጥ ይህንኑም በተግባር ስልጣኑን ለቆ ያሳየ ፖለቲከኛ ነው ይሉታል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ገዢውን በፖርቲ ጨምሮ አመራሮቹ አንድ ጊዜ ስልጣን ላይ ከወጡ የማይወርዱ ብቻ ሳይሆን የሚካሰሱ ስለመሆናቸው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ፖርቲዎች ስለ ሀገራዊ ዲሞክራሲ እያወሩ ስለ ውስጠ ዲሞክራሲ የሚጨቃጨቁ በሆኑበት ሀገር የልደቱ ደንብ አፀድቆ በተግባር ስልጣን ለሌሎች በመልቀቅ ውስጠ ዲሞክራሲ ያሳየ ጠበቃ አድርገው የሚወስዱት ብዙዎች ናቸው፡፡
ያም ሆኖ መፈራረጅና የሴራ ፖለቲካ በሰፈነበት በሀገራችን እንደ ልደቱ አይነት በመርህ የሚመራ ፖለቲከኛ ተገቢ ቦታውን የሚያገኝበት ትክክለኛ ሰዓት መምጣቱን ደጋፊዎቹ ያምናሉ፡፡ በቅርቡ ፖርቲው የተጣለበትን እገዳ መነሳቱም ለዚሁ ጉዳይ ማሳያ አድርገው ይወስዱታል፡፡ የልደቱ ወደ ፖለቲካው ዓለም መመለስም የአንድነት ሀይሉን የሚያነቃቃ ፤ ብሔርተኞቹን የሚያሰጋ እንደሚሆን ብዙዎች ያምናሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe