ለማ መገርሳ፤ ሥርዓት አልበኝነትና ሕገወጥ አካሄዶችን መልክ አስይዛለሁ አሉ

 

‹‹ ህዝቡ ሰላም አግኝቶ ህይወቱን እንዲመራ ግጭት፣ ስርዓት አልበኝነትና ህገወጥ አካሄዶችን ከምንም በላይ ትኩረት ሰጥቶ መልክ ማስያዝ የመከላከያ ሰራዊታችን ግዴታ ነው›› ሲሉ የኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ አስገነዘቡ፡፡

 

አቶ ለማ መገርሳ ይህንን ያስገነዘቡት በትናንትናው ዕለት በመኮንኖች ክበብ በተዘጋጀላቸው የአቀባበልና የሽኝት ስነስርዓት ላይ ሲሆን ሰላም በማስጠበቅ በኩል መከላከያ ሰራዊታችን ጠንክሮ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አሁን በአገራችን ባለው ግጭትና ስርዓት አልበኝነት የተነሳ የመከላከያ ሰራዊታችን ከምንግዜውም በላይ ብዙ ችግሮችን እየፈታ ነው ያሉት አቶ ለማ ውስጣዊ ሰላማችንን ማስጠበቅ ካልቻልን የውጭ ተጋላጭነታችን መጨመሩ እንደማይቀር ተገንዝብን እየተፈጠሩ ያሉ ህገወጥ አካሄዶችና ስርዓት አልበኝነትን መልክ በማስያዝ በኩል የመከላከያ ሰራዊቱ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፤ ኃላፊነቱና ግዴታውም ነው ››ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

‹‹የመከላከያ ሰራዊቱ በርካታ ተጋድሎዎችን ሲፈፅም የኖረና ያለ የአገር አለኝታ ነው፡፡ ይህ ሰራዊት ተገቢውን ክብር ማግኘት አለበት›› ያሉት አቶ ለማ ይህንን ኃይል ማዘመን ግዴታችንና ኃላፊነታችን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡ በመሆኑም ዘመኑ ከሚጠይቀው ብቃት አንፃር ሰራዊቱን ማዘመን ሙሉና ጠንካራ ማድረግ ተግተን የምንሰራበት ነውም ብለዋል፡፡ ሰራዊታችን በየዕለቱ ክቡር ህይወቱን እየከፈለ ቢሆንም በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች በኩል ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችን በመስበርና እየከፈለ ስላለው ዋጋና

መስዋዕትነት በተጨባጭ በማሳየት የመልካም ገፅታ ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

‹‹ መከላከያ ቀደም ሲል በልጅነት የነበርኩበት፣ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያየሁበት፣ ስራ የለመድኩበት የምወደው ቤቴ ነው››ሲሉ የገለፁት አቶ ለማ ‹‹ወደዚህ ተቋም ተመልሼ ስቀላቀል ደስታ ተሰምቶኛል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

ሴት የመከላከያ ሚኒስትር በመሆን በቀዳሚነት ተቋሙን ሲመሩ ለነበሩት የስራ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻም ላከናወኑት ተግባር ከፍተኛ ምስጋና አቅርበውላቸዋል፡፡‹‹የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር በመሆን በማገልገልዎ ትልቅ ኩራትና ክብር ሊሰማዎ ይገባል›› በማለትም ቀጣይ የስራ ቆይታቸው የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀውላቸዋል፡፡

 

ኢንጂነር አይሻም በበኩላቸው በተቋሙ በነበራቸው ቆይታ ከፍተኛ ልምድ የቀሰሙበት ፍቅርና መከባበር የሰፈነበት እንደነበር በመግለፅ በስራ ቆይታቸው ድጋፍ ላደረጉላቸው ሁሉ አመስግነዋል፡፡‹‹ መከላከያን መምራት አገርን እንደመምራት ነው የምቆጥረው፡፡ ህይወቱን ሳይሳሳ አገሩን ለመታደግ ከቆመ ከዚህ ሰራዊት ጋር በመስራቴ ዕድለኝነትና ልዩ ክብር ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም በተፈለግሁበት በማንኛውም ወቅት የትኛውንም ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ መሆኔን መግለፅ እፈልጋለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

በዚህ ስነስርዓት ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ሚኒስትር ዴኤታዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡(ምንጭ፡- መከላከያ ሚ/ር)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe