ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አዲስ ብስራት እየመጣ ነው!

በጥበቡ በለጠ
ሔንዝ ሪትማን /Heinz G.Rittman/ ይባላሉ፡፡ በጀርመን አገር BAUVERBANDE. NRW በተባለ ድርጅት ዉስጥ ም/ስራ አስፈጻሚ ናቸዉ፡፡ ድርጅቱ በጀርመን አገር የኮንስትራክሽን ባለሙያዋች ማህበር ነዉ፡፡ በስሩ ከ5000 በላይ አባላት አሉት፡፡ ስራዉም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ዉስጥ ያሉትን ባለሙያዋች የዕዉቀት ክህሎት በመስጠት መርዳት ነዉ፡፡
ሔንዝ ሪትማን ኢትዮጲያ ዉስጥ በተደጋጋሚ በመምጣት በኮንስትራክሽን ዘርፍ አያሌ ፕሮጀክቶችን ሰርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ከዩንቨርስቲ የሚመረቁ የምህንድስና ተማሪዋችን እና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ዉስጥ በልምድ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎችን የተለያዩ ስልጠናዋችን በመስጠት ሙያዊ ብቃት እንዲኖራቸዉ የሚያስችል ፕሮጀክት ይዘዉ መጥተዋል፡፡ ይህን ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ጋር በመሆን አዳብረዉት አሁን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ በመግባት ላይ ናቸዉ፡፡
ይህን የኮንስትራክሽን ተግባራዊ ዕዉቀት በኢትዮጵያ ዉስጥ ለማስረጽ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዉይይት ማድረጋቸዉን ሔንዝ ሪትማን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ዉይይታቸዉም ስልጠናዉ በምን አግባብ መካሄድ እንዳለበትና የወደፊት ተጨባጭ ዉጤቶች ላይም ተነጋግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት ሔንዝ ሪትማን ሲናገሩ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከዩንቨርስቲ እና ከልዩ ልዩ ኮሌጆች የሚመረቁ ተማሪዋች የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ላይ ሰፊ ዕዉቀት ቢኖራቸውም ተግባራዊ እውቀት ላይ ግን አናሳ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የኒቨርሲቲ ትምህርት ሳይኖራቸው በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የተሰማሩትም ኢትዮጵያዊያን፣ በንድፈ-ሀሳቡም ሆነ በተግባራዊ ትምህርቱ ብዙ ገፍተውበት ባለመሄዳቸው ሁለቱንም ወገኖች በጋራ ተግባራዊ ስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲም የተመረቁት ተማሪዎች እና በልምድ የሚሰሩትን ባለሙያዎች በጋራ ተግባራዊ ትምህርት የመስጠት ፕሮጀክት ወደ ኢትዮጵያ ይዘው መምጣታቸውን ሔንዝ ሪትማን ይገልጻሉ፡፡
በዚህ ስልጠና ውስጥ የሚካተቱት ትምህርቶች አንድ የኮንስትራክሽን ኩባንያ እንዴት ተመስርቶ ያድጋል፣ የቢዝነስ ፕላኑ እንዴት ይሰራል፣ የገንዘብ አቅሙን እንዴት ማሳደግ ይቻላል፣ ወደ ከፍተኛ ደረጃስ እንዴት ማሳደግ ይቻላል በሚሉትና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በአለም አቀፍ ባለሙያዎች ስልጠናው እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ይህ ስልጠና አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከስልጠናው በኋላም አዳዲሶቹ ምሩቃን ተማሪዎች የየራሳቸውን የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በጋራም ሆነ በተናጠል በመክፈት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩበትን አጋጣሚ እንደሚያመጣ ሚስተር ሔንዝ ሪትማን ይናገራሉ፡፡
የዚህን ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ገንዘብ ከየት ታገኛላችሁ ተብለው የተጠየቁት ሔንዝ ሪትማን፣ ገንዘቡ ከጀርመን የገንዘብ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚገኝ ሲሆን የሚያስተባብረው ሴኳ/ Sequa/ የተባለው የጀርመን ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵ የጀርመን ኤምባሲም የሀሳቡ ደጋፊ መሆኑንም አውስተዋል፡፡
በመጨረሻም ሲናገሩ፣ በዚህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊያን የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም አልፎ ለሀገርም በሙያው የዳበረ የኮንስትራክሽን ባለሙያ መፍጠር እንሚያስችል አውስተዋል፡፡በሂደትም ከአለማቀፉ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ የሚሆኑ ድርጅቶችንም ኢትዮጵያ ውስጥ ማብቃት እንችላለን ብለዋል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe