“ምርጫ መራዘም የለበትም ሲሉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ደግሞ ምርጫው እንዲራዘም በመጠየቅ ህዝብን እያደናገሩ ይገኛሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
መንግስት በቀጣዩ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ከዚህ በፊት በተካሄዱ ምርጫዎች ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎች የማይደገሙበት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ምርጫ 2013 ቁልፍ የሽግግር ምዕራፍ በሚል ሃሳብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባካሄዱት የውይይት መድረክ ነው።
በመድረኩም ከፓለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ የሲቨክ ማህበራት ተሳትፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበኩላቸው በኮሮና ምክንያት ህግን ተከትሎ ምርጫ ሲራዘም “መሆን የለበትም” ብለው ሲከራከሩ የነበሩ አካላት አሁን ላይ ምርጫው እንዲራዘም እየጠየቁ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ህዝብን ለማደናገር የሚደረግ ሙከራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት መሰረታዊ ከሆኑ ምሶሶዎች አንዱ ምርጫ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግስት ፍትሃዊ፤ ነጻና አሳታፊ ምርጫ ለማካሄድ ቁርጠኛ ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።
መንግስት የፖለቲካ አመራር የሆኑ ነገር ግን ገንዘብ ባለበት ቦታ ሁሉ እየተገኙ በወንጀል የተዘፈቁ ግለሰቦች ላይ የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይህንን እውነት እያወቁ “ከንቱ ክስ” ከማቅረብ ወጥተው መንግስትን ሊተባበሩ ይገባልም ነው ያሉት።
መንግስት በቀጣዩ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ከዚህ በፊት በተካሄዱ ምርጫዎች ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎች የማይደገሙበት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።
የህወሃት ጁንታ በትግራይ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን አስታውሰው፤ መንግስት ችግሩን ለማስተካካል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የጁንታው መወገድ ለትግራይ ህዝብ እፎይታን እንደፈጠረም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዴዮን ጢሞቲዮስ በቀጣዩ ምርጫ የባለድርሻ አካላት ሚና እንዲሁም የተለያዩ የምርጫ ስርዓት አይነቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በዚህ ወቅት መንግስት ከዚህ በፊት በተካሄዱ አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ላይ የታዩ ህጋዊ ያልሆኑ አካሄዶች እንዲቀረፉ በቁርጠኝነት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከምርጫው በፊት የፓርቲ ቁመና እንዲኖራቸው ራሳቸውን እንዲፈትሹም ነው አስተያየት የሰጡት።
አሁን ላይ በሀገሪቱ “ሰላም ባለመኖሩ” ምክንያት ምርጫው መራዘም አለበት ሲሉ ሃሳብ ያቀረቡም አሉ።
“የፖለቲካ አመራሮች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ታስረዋል፤ በዚህ ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ የለብንም” የሚል ሃሳብም ከተሳታፊዎቹ ተነስቷል።
በትግራይ ክልል የሚወዳደረው አረና ፓርቲ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ህዝብ በተለያዩ አገልግሎቶች መቋረጥ ምክንያት ችግር ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም መንግስት በተለይ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን በአፋጣኝ ጠግኖ ለአገልግሎት ክፍት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለትግራይ ህዝብ ነጻነት ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።