ምኒልክን እንደ ጭራቅ የሚስሉ ሰዎች ለመሆኑ ከምኒልክ በፊት የነበሩ ባላባቶችን ታሪክ ያውቃሉ?

በዘመናችን ምኒልክን የዱር አውሬ ነው፣ ሂትለር ነው ተብሎ ተዘፍኖበታል። ረጋሚዎችንና ዘላፊዎችን ልቦና ይስጣችሁ፣ ህሊናችሁ ይፍረድባችሁ ብሎ ዞር ማለት በቂ አይደለም። በምኒልክ ላይ ቀፋፊ ስድቦችና እርግማኖች የሚወርዱበት ምን የተለየ ነገር አድርጎ ነው? ዶሴው ይውጣና ይታይ። ንጉሡ የኦሮሞና የትግራይ አውራዎችና ጦረኞች ካደረጉት የተለየ ነገር አድርጓል?

(ከአሜን ባሻገር የተወሰደ)

ምኒልክን እንደ ጭራቅ የሚስሉ ሰዎች ለመሆኑ ከምኒልክ በፊት የነበሩ ባላባቶችን ታሪክ ያውቃሉ?

የራስ ሚካኤልን ታሪክ አላነበቡም ይሆን? የአድዋ ተወላጁ ራስ ሚካኤል ስሑል በአንድ ወቅት ወረኛ ፋሲል ከተባለ የኦሮሞ ጉልበተኛ ጋር ተዋጋ። ፋሲል ተሸንፎ ሸሸ። ስሑል ሚካኤል ድል አድርጎ የማረካቸውን ሃያ የሚደርሱ የኦሮሞ ወታደሮች ዐይናቸውን በወስፌ እየጎለጎለ አውጥቶ ጅብ እንዲበላቸው በተከዜ ዳርቻ ጣላቸው። ወረኛ ፋሲል በዚህ መንገድ የታወሩት ወታደሮች ወደ አገራቸው ተመልሰው ህዝቡን እንዳያሸማቅቁበት ስለሰጋ ገደላቸው። ብሩስ የተወሰኑትን አትርፎ ለራሱ እንዳስቀራቸው ጽፏል።

ዋጨቃ የተባለ ሌላ ምርኮኛ በራስ ሚካኤል ፈራጅነት ከነሕይወቱ ቆዳው እንዲገፈፍ ተፈርዶበታል። የሚካኤል ስሑል አድናቂ የነበረ የዓይን ምስክር ይህን አስመልክቶ ሲጽፍ፣ “ወእምድኅረዝ ተውህበ ዋጨቃ ለእለ ይጠብህዎ ከመ ዳቤላ ጠሊ (ከዚያ በኋላ ዋጨቃን እንደፍየል ይበልቱት ዘንድ አስረከቡት) ብሏል።

በወቅቱ አገሪቱን የጎበኘው ያዕቆብ ብሩስ የዋጨቃ ቆዳ በአደባባይ ይጎበኝ እንደነበር ዘግቧል። የጭካኔ ሥራ ከትግራይና ከአማራ በመነጩ አምባገነኖች ብቻ የሚተገበር አልነበረም። ራስ ወልደሥላሴ ትግራይን ለብቻው በሚያስተዳድርበት ዘመን ከቱለማና ከጃዌ ጎሳ ወገን የሆነው የዘመኑ አባዱላ ጉጂ የተራቀቁ ጭካኔዎችን ይፈጽም ነበር። ባላንባራስ ወልደ ተክሌ የተባለውን የላስታ ባላባት ከማረከ በኋላ ጣቶቹ እንዲቆረጡ አድርጓል።

ጉጂ በጭካኔ የሚዝናና ሰው ነበር። በ1809 ጉጂ ከራስ ወልደሥላሴ ጋር ይጣላል። እናም የትግራዩ ባላባት ከሁለት ዓመት በፊት የፈጸመበትን ወረራ ለመበቀል ከህንጣሎ 12 ሰላማዊ ሰዎችን ያስጠልፍና ወደ ቦታው ይመለሳል። ከዚያ ከአስራ ሁለቱ ውስጥ የአስራ አንዱን ምርኮኞች ዓይን እንደ ሙጃሌ እየተነቀለ እንዲወጣ ያደርጋል። የአስራ ሁለተኛው ሰለባ አንድ ዓይኑን ያወጣና አንድ ዓይኑን ያስተርፍለታል። ጉጂ ይህንን ያደረገው እንጥፍጣፊ ርህራሄ ስለተረፈው አልነበረም። አንድ ዓይናው ሰውዬ አስራ ሁለቱን ሰለባዎች እየመራ ወደ አገራቸው እንዲመልሳቸው ነው። ይህንን ታሪክ የሚነግረን ጉጂን በአካል የሚያውቀው ናትናኤል ፒርስ፣ ይህንን ጉደኛ ታሪክ የሚዘጋው በሚከተለው አንቀጽ ነው፣ “This is a trifling instance of Gojee’s barbarity of which i have heared examples to horried to relate” “ይህ ከጉጂ የጭካኔ ሥራዎች ውስጥ እዚህ ግባ የማይባለው ነው። ሌሎች ግን እጅግ በጣም ዘግናኝ በመሆናቸው የተነሣ ለወሬ እንኳን አይመቹም።”

ናትናኤል ፒርስ ለወሬ አይመቹም ብሎ የዘለላቸውን ጭካኔዎች አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ መዝግቧቸዋል። አለቃ እንደሚነግረን፣ “ጉጂ…የታላላቆችን ራሳቸውን ያስፈልጥ ነበር።”

አይን በማሳወር መቅጣት ምኒልክ ወደ ሥልጣን እስኪመጡ ድረስ ቀጥሏል። በዝብዝ ካሳ (በኋላ አፄ ዮሃንስ) ንጉሠ ነገሥት ተክለጊዮርጊስን በጦርነት ከማረከ በኋላ አይኑን በጋለ ብረት እንዳጠፋው የሚገልጽ ታሪክ በልዩ ልዩ ሰነዶች ተመዝግቦ ይገኛል።

እንግሊዛዊው ጄኔራል ጎርደን በ1879 በአፄ ዮሃንስ ስር ትተዳደር ስለነበረችው ኢትዮጵያ በጻፈው ማስታወሻ፣ “የምጽፈው በጥድፊያ ነው። ይሁን እንጂ ስለኢትዮጵያ ያለኝን ትዝብት በአጭሩ እገልጻለሁ። ንጉሡ እየለየለት ነው። ሱረት የሚስቡ ሰዎችን አፍንጫ በመፎነን፣ ትምባሆ የሚያጨሱ ሰዎችን ከንፈር በመቁረጥ ይቀጣል፤ የበደሉትን ሰዎች እጅና እግር ይቆርጣል።” በማለት ጽፏል።

ራስ አሉላ አባ ነጋ፣ በ1886 የባርያ ብሔረሰብ መሪ በቂ ግብር አላስገባም በማለቱ፣ በነዋሪው ላይ የጅምላ ቅጣት ፈጽሟል። ይህንን አስመልክቶ ሀጋይ ኤርሊክ የተባለው የራስ አሉላ አድናቂ ታሪክ ጸሐፊ ሲጽፍ፣ “አሉላ በባርያ ብሔረሰብ ታሪክ ውስጥ ከባድ የሚባለውን ውድመት አስፈጸመ። በሕዳር የመጨረሻዎቹ ሳምንታት በጋሽ ወንዝ ሰሜን ክልል የሚኖረው ሁለት ሦስተኛው የባርያ ኩናማ ብሔረሰብ ሕዝብና ቀንድ ከብት አለቀ” ይላል።

አፄ ዮሐንስ አራተኛ ለንግሥት ቪክቶርያ በጻፈው ደብዳቤ የሚከተለውን ይላል፣ “ከግዛቴ ውስጥ አንዲት ሀገር አለች። ስምዋ አዘቦ የምትባል። በውስጥዋ ያሉ ሰዎች እስላምና ኦሮሞ ናቸው። እነዚያ ሸፈቱ። እኔም ዘመትኩባቸው። የወጣሁበት ነገር በእግዚዓብሔር ኀይል ቀንቶኝ ተመለስሁ።”

ዮሃንስ ለቪክቶርያ ቀንቶኝ ተመለስሁ ያለውን ለንጉሥ ዊሊያም አራተኛ ሲያብራራለት፣ “በአገሬ አዘቦ የሚባል የኦሮሞ እስላም ሀገር አለ። ከርሱ ሽፍታ ተነሳብኝ፤ እርሱን ለማጥፋት ዘመትሁ። እርሱንም በእግዚአብሔር ሃይል አጠፋሁት።” ብሏል። የአዘቦ ሙስሊም ኦሮሞዎች የአፄ ዮሃንስን የሃይማኖት ፖሊሲ በመቃወማቸው በሰይፍ ተደብድበዋል።……………………

ጥንታዊ የኦሮሞ ጦረኞችም በጦርነት ወቅት ከዚህ የአማራው ወይም የትግራዩ መስፍን ከሚያደርገው የተለየ የሚያደርጉ አልነበሩም። ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ በሚል አይነት፣ ጦር ሜዳ ላይ ከሚያገኙት ወታደር ባሻገር፣ በሰላማዊው ነዋሪ ላይ በትራቸውን ያሳርፉበት ነበር። ይህንን ታሪካዊ ሐቅ ለመካድ ተረት የሚፈጥሩ፣ ያልተመዘገበ የሚተርኩ ሰዎች አልጠፉም።

ብሔርተኛው ምሁር ፕሮፌሰር መሀመድ ሀሰን ምኒልክ ሀገር ለማስገበር ባደረገው ጦርነት ስለደረሰው ሰብአዊ ውድመት አውግቶ አያባራም። ነገር ግን፣ በሌላው ገጽ፤ ኦሮሞ ውስጣዊ መስፋፋት ባካሄደ ጊዜ ስለነበረው ሁኔታ ሲጽፍ የኦሮሞ ወታደሮች ላባ ጨብጠው ወደ ጦር ሜዳ የገቡ ይመስል ከደም ነጻ ሊያደርጋቸው ይጥራል። ለምሳሌ፣ በ Ethiopian Review/ June 1992 ላይ በጻፈው መጣጥፍ ኦሮሞዎች ውስጣዊ መስፋፋት ባደረጉበት ወቅት ከፊታቸው የገጠማቸውን ነዋሪ ምን እንዳደረጉት ሲነግረን፣ “በመጀመርያዎቹ የፍልሰት አሥርት ዓመታት ኦሮሞዎች በጂሃድ ጦርነት በወደሙትና ከሞላ ጎደል ሰው አልባ በሆኑ ጠፍ መሬቶች አቋርጠው ተንቀሳቅሰዋል። የተረፉት ነዋሪዎች ወይ ከኦሮሞዎች ፊት ሸሽተዋል አለበለዝያም ወደ ኦሮሞነት ተለውጠዋል” ይላል።

መሀመድ ሀሰን በዚህ ዓይነት፣ ነዋሪዎች ቦታቸውን ማንነታቸውን መነጠቃቸውን ያምንና ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ይዘለዋል። ኦሮሞ ሲያስገብር የገባር ነዋሪዎች እጣ ሽሽትና በአዲስ ባህል መዋጥ ብቻ አልነበረም። አያሌዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በግራኝ አህመድ ጂሃድ ጦርነት ማብቂያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ቤርድሙዝ በጊዜው ለነበረው የኦሮሞ እንቅስቃሴ የዓይን ምስክር ነው። አስገባሪ ወታደሮች ምን እንደሚያደርጉ ሲጽፍ፣

“ባስገበሩት ሀገር ውስጥ ያገኙትን ወንድ ሁሉ ይገድላሉ። የወንድ ልጆችን ብልታቸውን ይቆርጣሉ። አሮጊቶችን ገድለው ወጣቶችን ለአገልጋይነት ይማርካሉ” ይላል።

ምኒልክን “የዱር አውሬ” ብሎ፣ የሚዘፍን ሰው፣ ምኒልክ ጥቁር እባብ Minilik bofa gurracha ብሎ የሚገጥም ሰው፣ ከምኒልክ በፊት የነበሩት ባላባቶች እንዴት ያለ ጠባይ እንደነበራቸው እንዲያውቅ የሚከተለውን አንቀጽ እጋብዘዋለሁ። በንጉሥ ሣህለሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያን የጎበኘው ሀሪስ፣ Ethiopian highlands በተባለው መጽሐፉ ቅጽ ሦስት ላይ ስለ ጎማው ኦሮሞ ባላባት ሲነግረን፣ “የጎማው ባላባት የሚፈጽመውን ጭካኔ ለማሰብ ይከብዳል። ጥፋተኞች እጃቸውን አፍንጫቸውንና ጆሮአቸውን ይቆረጣሉ። ዓይናቸው በጋለ ብረት ይፈርጣል በዚህ ዓይነት ከተቆራረጡ በኋላ ሕዝቡ ይማርባቸው ዘንድ በገበያ መሃል እንዲያልፉ ይደረጋል። የጦር ምርኮኞች በመቶ በመቶ እየተመደቡ አንገታቸው ላይ ድንጋይ ታስሮ ዳማ ተብሎ ይጠራ በነበረው ወንዝ ውስጥ ይወረወራሉ” በማለት ጽፏል።…………….

በምኒልክ ዘመን ሌቦችንና አመጸኞችን እጅና እግራቸውን በመቁረጥ መቅጣት አልቀረም። ያም ሆኖ ምኒልክ ከሱ በፊት የነበሩት ባላባቶች የሚፈጽሙትን ዓይነት ብዙ የእብሪት ግፍ አስቀርቷል። በኦሮሞ፣ ትግራይ፣ ከፋ፣ አማራና አፋር ወታደሮች የሚተገበረው የመስለብ ባህል እንዲቀር አዋጅ አውጥቷል። ይሁን እንጂ ባህሉ ሥር የሰደደ ስለነበር በቀላሉ ሊወገድ አልቻለም።

በወላይታ ዘመቻ ከምኒልክ ጋር አብሮ የዘመተው ከዘመቻው በኋላ የምኒልክ ነቃፊ የሆነው ፈረንሳዊ ወዶ ገብ ይህን አስመልክቶ ሲጽፍ፣

“ንጉሥ ምኒልክ በጦርነት ወቅት ቁስለኛ መስለብ እንዲቀር ትልቅ ጥረት አድርጓል። ይሁን እንጂ በወላይታ ዘመቻ አብሬው ስዘምት ይህ ባህል በአማሮችና በኦሮሞዎች እና በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ጎሳዎች ልብ ውስጥ ሥር የሰደደ ባህል መሆኑን ተረድቻለሁ። አዋጅ ቢያስነግርም፣ ህግ ቢያወጣም፣ በዜጎች ዘንድ እጅግ የተከበረ ቢሆንም ንጉሡ ይህንን ዘግናኝ ልማድ ሊያስወግደው አልቻለም” ይላል።

ለማጠቃለል፡

 

በጥንታዊት ኢትዮጵያ ሰዎች ይመሩበት የነበረው የሕዝብ አስተዳደር ሕግ ጥንታዊ ነው። ገዥዎች የፈጸሙትን ግፍ በዘመናዊ የስነምግባር እና ሰብአዊ መብት መለኪያ በማየት ፊት መፍጀትና ደረት መድቃት የሚጠበቅብን አይመስለኝም። አባቶቻችን የዘመናቸው ሥርዓትና ወግ ባርያ በመሆናቸው፣ ያደረጉትን ከማድረግ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም። ጠላትን መቁረጥ መፍለጥ ለኛ በደል ሲሆን ለቀደምቶቻችን ግን ደንብ ነበር። በዘመናቸው በቦታቸው በሁኔታቸው ውስጥ ብንሆን እኛም እነሱ ያደረጉትን ከማድረግ አንመለስም ነበር።

የሁላችንም አባቶች የሁላችንም ጌቶች በፈረቃ ግፍ መፈጸማቸው በታሪክ ተመዝግቧል። ይሁን እንጂ ከዳግማዊ ምኒልክ ጀምሮ እስከቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ድረስ በአስተዳደር ብዙ ጉልህ መሻሻሎች ታይተዋል። ከእብሪት የሚመነጭ የጭካኔ ቅጣት በመጠንና በአይነት ቀንሷል። ዘመናዊ ትምህርትን የቀሰሙ ኢትዮጵያውያን እና አውሮፓዊ አማካሪዎች ተጽእኖ እንዲሁም የመሪዎች ብሩህነት እና ቀናነት ለዚህ መሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል። በዘመናችን የምሬትንና የቂም በቀል ፉከራን ርግፍ አድርገን ትተን በሚያቀራርቡ በሚያስተባብሩ ሐሳቦች ላይ ከተጠመድን ከአባቶቻችን የተሻለ ዓለም እንደምንፈጥር ጥርጥር የለኝም።

********************************

(ከአሜን ባሻገር የተወሰደ)

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe