ስለአልኮል ማስታወቂያ ክልከላ የሚዲያ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አዲስ የምግብና የመድሃኒት አስተዳዳር አዋጅ የአልኮል መጠጦችን በራዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በቢል ቦርድ ማስተዋወቅ የሚከለክለው ደንብ ከትናንት ግንቦት 21፣ 2011 ዓ. ም ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል።

በዚህ መሠረት ማንኛውንም መገናኛ ብዙሃን የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ ሕጉ ከሚፈቅደው ሰዓት ውጭ ማስተላለፍ እንደማይችል ተነግሯል።

በኢትዮጵያ በርካታ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዲሁም የሕትመት ውጤቶች በቢራ ፋብሪካዎች ድጋፍ አድራጊነትና ከአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ በሚገኝ ገንዘብ ይደገፋሉ። አንዳንዶቹ እንደውም ዋና የገቢ ምንጭ የሚያገኙበትም መንገድም ነው።

ታዲያ አዲሱ ሕግ ምን ዓይነት ተፅእኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል?

የቁም ነገር መፅሔት አዘጋጅና ባለቤት ታምራት ኃይሉ “ለመጭው ትውልድ በማሰብ ከሆነ በመልካም ጎኑ ሊወሰድ ይችላል፤ ነገር ግን እኛ አገር የማስታወቂያ ችግር በራዲዮና በቴሌቪዥን መተዋወቁ ሳይሆን አቀራረቡ ነው” ይላል።

እሱ እንደሚለው፤ የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ በሌሎች አገራትም የተለመደ ሲሆን አቀራረቡ ግን የተጠና ነው። ባለው ልምድ፤ የቢራ ማስታወቂያዎቹ የሚተላለፉበት መንገድና ህፃናትን ሊስብ በሚችል መልኩ መቅረባቸው እንጂ ማስታወቂያው ሰዉን ጠጪ አድርጓል? ጠጪስ አለ? የሚለው ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራል።

ታምራት እንደሚለው፤ ከፍተኛ ማስታወቂያ አስነጋሪዎች ቢራ ፋብሪካዎች በመሆናቸው ሕጉ የመዝናኛ ዘርፉንና ሚዲያውን ይጎዳል።

አዋጁ ተግባራዊ ሳይሆን በፊት የቢራ ፋብሪካዎች ማስታወቂያ መስጠት ማቆማቸው ተፅእኖ አሳድሯል የሚለው ታምራት፤ ከመከልከል ይልቅ በአቀራረቡ ላይ መነጋጋር ይሻላል ይላል።

ከዚህም ባሻገር የቢራ ፋብሪካዎቹ ከፍተኛ ገንዘብና በርካታ ሠራተኞች የያዙ በመሆናቸው፤ ባለማስተዋወቃቸው ገበያቸውን የሚያጡ ከሆነ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ይጎዳል የሚል ስጋትም አለው።

“በርካታ ፕሮግራሞች የሚደገፉት የቢራ ፋብሪካዎች በሚያሰሩት ማስታወቂያ ነው” የምትለው በብስራት ኤፍኤም የፋሽንና ውበት ፕሮግራም አዘጋጅና ጋዜጠኛ ኤልሳ አሰፋ ጉዳዩን በሦስት መንገድ እንደምታየው ትገልፃለች።

የመጀመሪያው በተለይ ከአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች በሚገኝ የድጋፍና የማስታወቂያ ገንዘብ የተቋቋሙና በዚያም ፕሮግራማቸውን የሚያስኬዱ ተቋማትን ገቢ ያሳጣል።

በሌላ በኩል እንደአንድ ማኅበረሰብ ማስታዋቂያዎች ከሚሠሩበት መንገድና ከቢራ ፋብሪካዎቹ ስያሜ ታዳጊዎች ምን እየተማሩ ያድጋሉ? የሚለው ጥያቄ ያስነሳል ትላለች።

“ቢራ እንደመድሃኒትና እንደምግብ ነበር ሲተዋወቅ የነበረው” የምትለው ኤልሳ፤ ህፃናትን በማይጎዳ መልኩ ጥናት ተሠርቶ ማስታወቂያዎቹ እንዲተላለፉ ማድረግ ይቻል ነበር ስትል ትሞግታለች።

የአሀዱ ኤፍኤም ራዲዮ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ የተለየ ሃሳብ አላቸው።

“ባለፉት ዓመታት በማስታወቂያና በፕሮሞሽን ድጋፍ ጉልህ ቦታ የነበራቸው የቢራ ፋብሪካዎች ነበሩ፤ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ለመክፈት ከቢራ ፋብሪካዎች ጋር መነጋጋር የተጀመረበት ወቅትም መጥቷል” ይላሉ።

በአብዛኛው ቢራዎች ሚዲያውን የመቆጣጠር ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚሉት አቶ ጥበቡ፤ ማስታወቂያዎቹንም ከኢትዮጵያዊነት፣ ከማንነት፣ ከታላቅነት ጋር በማያያዛቸው ሰዎች ጠጪ እንዲሆኑ የማድረግ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ መቆየታቸውን ያምናሉ። ነገሩ ያሳስባቸው እንደነበርም አልሸሸጉም።

በመሆኑም የቢራ ማስታወቂያዎቹ መከልከላቸው በአገሪቱ ላይ በጎ አሻራ ያሳርፋል ይላሉ።

“ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፤ ትውልድ ላይና አገር ላይ የሚሰሩ ጉዳዮችን የቢራ ፋብሪካዎች ሲደግፉ አይታዩም” በማለት ሚዲያው ሊወጣ የሚችለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሚና እንደጎዱት ያብራራሉ።

አቶ ጥበቡ እንደሚሉት፤ ከቢራ ፋብሪካዎች ውጭ ከሚዲያ ጋር መሥራት የሚፈልጉ ሌሎች ድርጅቶችም ቢኖሩም የቢራ ፋብሪካዎቹ ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ሌሎቹ ገፍተው እንዳይመጡ የማድረግ ሚናም ነበራቸው።

የሚዲያ ተቋማቱ ጥራት ያለውና ሊደመጥ የሚችል ፕሮግራም ማቅረብ ከቻሉ ድጋፍ የሚያደርግላቸው አያጡም የሚል እምነትም አላቸው።

ሕጉ ለሕትመት ሚዲያዎች ተስፋ ይሰጥ ይሆን?

አዲሱ የምግብና የመድሃኒት አስተዳዳር ሕግ የአልኮል ማስታወቂያዎችን ማስተላለፍ የሚከለክለው በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በቢል ቦርድ ነው። በመሆኑም በህትመት ዋጋ ውድነትና አንባቢ ባለመኖሩ ለሚንገዳገዱት የህትመት ሚዲያዎች ተስፋ ይሰጥ ይሆን?

የቁምነገር መፅሔት አዘጋጅና ባለቤት ታምራት በዚህ ረገድ ተስፋ አለው።

መፅሔትና ጋዜጣ የሚያነቡት ኃላፊነት የሚሰማቸውና ትልልቅ ሰዎች እንደሆኑ የሚናገረው ታምራት፤ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የህትመት ዋጋ መቋቋም የሚቻለው በማስታወቂያ ገቢዎች ነው ይላል።

በዚህም ጥራቱን ማሻሻል፣ ሥርጭቱን ማሳደግ፣ የንባብ ባህልን መጨመር ይቻላል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ይሁን እንጂ አሁንም በሕጉ ላይ ብዥታ በመኖሩ፤ የቢራ ፋብሪካዎችም ሆኑ የአልኮል ማስታወቂያ የሚሰጡ ድርጅቶች ክልከላው ለሁሉም መገናኛ ብዙሀን ነው በማለት እየተንቀሳቀሱ እንዳልሆነ ገልጿል።

“በኢትዮጵያ የህትመት ሚዲያው ሥርጭት የተዳከመ ነው፤ ግፋ ቢል ከአምስት ወይም ስድስት ሺህ ቅጂ በላይ አይሸጥም” የሚሉት አቶ ጥበቡ፤ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎች በህትመት ሚዲያዎች ላይ ቢወጡ አቀራረባቸው የተገደበ ስለሚሆን፣ በተለይም ለህጻናት ፊት ለፊት ስለማይታዩ ተፅእኖ አይኖረውም ይላሉ።

“ፋብሪካዎቹ ብራንዳቸው እንዳይረሳ ወደህትመት ሚዲያ ሊመጡ ይችላሉ” የምትለው ኤልሳ፤ አሁን በመነቃቃት ላይ ያለውን የህትመት ሚዲያው የበለጠ እንደሚያበረታው እምነት አላት።

በሚዲያው ላይ ምን ተፅእኖ አሳረፈ?

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ላይ ጥናት እንዳደረጉ የሚናገሩት አቶ ጥበቡ፤ ወሳኝ የሚባሉት ሰዓቶች ከድጋፍ አድራጊ አካላት ጋር ግንኙነት አላቸው ይላሉ። ከቢራ ፋብሪካዎች ጋር ተፈራርመው ገንዘብ ይዘው የሚመጡ ፕሮግራሞች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸውም ያክላሉ።

ዋና ዋና የሚባሉት ሰዓቶች ‘መዝናኛ’ ለሚባሉና በቢራ ፋብሪካዎች ለተደገፉ ፕሮግራሞች ይሰጣሉ። ይህም በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ፋይዳ የሌላቸው ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ እንዲደረጁ እንዳደረገ ያስረዳሉ።

የታምራት ሀሳብም ተመሳሳይ ነው። የስፖንሰርሺፕ (ድጋፍ) ሃሳብ ተግባራዊ የሚደረገው በተዛባ መልኩ ነው ይላል። “የውጭ አገር ሚዲያዎችና ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎች ይተላለፋሉ፤ ነገር ግን እንደ እኛ መልክ ያጣ አይደለም” ሲል የማስታወቂያ አሠራር እውቀትና አቅም ችግር እንዳለ ይናገራል።

“ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ቁጭ ብለው ቴሌቪዥን ማየት የተቸገሩበት ጊዜ ላይ ደርሰን ነበር” ሲልም ያክላል።

ኤልሳ በበኩሏ የአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎቹ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ የራሳቸው ምርጫ ቢኖራቸውም፤ በአብዛኛው አስተማሪና ጠንከር ያሉ ፕሮግራሞችን ተመራጭ ሲያደርጉ አይታይም ስትል ልምዷን አጋርታናለች።

“በቤተሰብ ላይ ያተኮረ ተወዳጅ ፕሮግራም ነበረኝ፤ ነገር ግን ዓመቱን ሙሉ አንድም የቢራ ስፖንሰር አልነበረኝም፤ ምክንያቱም ፕሮግራሙ ስለሚያስተምር አያዝናናም የሚል ነው” ስትል በርካታ ቁም ነገር አዘል ፕሮግራሞች ያለድጋፍ ሲሠሩ እንደሚስተዋል አክላለች።

የፋብሪካዎቹ የገበያ ዘርፍ ኃላፊዎች (ማርኬቲንግ) የየራሳቸው አድማጭ ሊኖራቸው ቢችልም፤ በተለያዩ መንገዶች ማኅበራዊ ግዴታዎችን መወጣት እንደሚገባቸው አስተያየቷን ሰጥታለች።

Source: BBC Amharic

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe