በመጨረሻም ኢህአዴግ ወደ መቃብር …. ከ1981- 2011

በመጨረሻም  ኢህአዴግ ወደ መቃብር …. ከ1981- 2011

‹ኢህአዴግ  አብረን እንሁን ብሎ ማንንም አያስገድድም ›

‹‹ሰማዕታ የወደቁለትን ዓላማ ሳናሳካ ድርጅቱን አናፈርስም›

መነሻ

ጠቅላይ ሚኒስት ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ከጥቂት ወራት በኋላ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ እንደሚመሠርቱ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከ3 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ከሐረሪ፣ ጋምቤላ፣ ቤኔሻንጉል ጉሙዝ፣ ከአፋርና ከሶማሌ ክልል ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው በሀገራዊ ለውጡ መሠረታውያንና አካሄድ ዙሪያ ምክክር ሲያደርጉ ከዋሉ በኋላ ነው ይህንን ያሳወቁት፡፡ ‹‹ከጥቂት ወራት በኋላ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የሶማሌ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ … ፓርቲ እያልን አንሄድም። እንደ ኢህአዴግ ከጫፍ ጫፍ ያሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በነፃነት የሚሳተፉበት አንድ ሀገራዊ ፓርቲ እንመሠርታለን›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ኢህደዴግ የሚባለው ግንባር የተመሰረተው በ1981 ዓ.ም አጋማሽ ሲሆን የግንባሩ ዋነኛ ተዋንያን ህወሃትና የቀድሞው ኢህዴን/ብአዴን ነበሩ፡፡ በዓመቱ የተማረኩ ወታደሮችና ሌሎች ተራማጅ የኦሮሞ ወጣቶችን ያሰባሰበው ኦህዴድን በመመስረት የግንባሩ አካል ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በ1985 ዓ.ም ደግሞ የደቡብ ህዝቦችን ለማቀፍ የተመሰረተው ደህዴን የግንባሩ አንድ አባል በመሆን ወደ ምርጫ ጉዞ ጀምሯል፡፡

ለኢህአዴግ ምስረታ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ህወሃት የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ያስደሰተው አይመስልም፡፡ ምንም እንኳ አጋር ፖርቲዎችን የማቀፍና በኢህአዴግ ውስጥ የማስገባት ፍላጎትና ጥያቄ በየጊዜው ሲነሳ የቆየ ጉዳይ ቢሆንም በዚህ ቀውጢ ሰዓት ኢህአዴግን ለማፍረስና በአዲስ ፖርቲ ለመተካት የተያዘውን ሩጫ ህወሃት በጥርጣሬ እየተመለከተው ነው፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ገዢው ፖርቲ ኦዲፒ በአንድነት ሀይሎች ዓላማው ተጠልፏል በሚል ለተጀመረበት ዘመቻ ምላሽ በሚመስል ሁኔታ ‹በፌደራሊዝም ስርዓቱ ላይ ድርድር የለም› የሚል መግለጫ ቢያወጣም ህወሃት አሁንም ልቡ ከኦዲፒ ጋር ለማድረግ መቸገሩን የፖለቲካ ሳይንስ ሙሑራን ይመሰክራሉ፤

በመሆኑም ህወሃት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተነገረውን  ኢህአዴግን የማፍረስ እርምጃ ለመቀበል እያንገራገረ መሆኑ ይታያል፡፡ ህወሃት ብቻ ሳይሆን የብሔር ፌደራሊዝሙ የህልውናችን መሠረት ነው ብለው እንደ ህወሃት የሚያምኑ የአፋር፤ የቤንሻ ጉል ጉምዝና የጋምቤላ ፖርቲዎችም የህወሃትን መንገድ ለመከተል እንደሚፈልጉ ከድርጅቶቹ መሪዎች መግለጫ መረዳት ይቻላል፤

ያም ሆኖ ግን ይህ ኢህአዴግን ወደ አንድ ሀገራዊ ፖርቲ የማምጣ ውሳኔ በሀዋሳው የኢህአዴግ ውሳኔ ላይ የተነሳ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ህወሃትም ሆኑ  ሌሎች አጋር ፖርቲዎች ኢህአዴግን እያለቀሱ  ወደ መቃብር ከመሸኘት  በቀር አማራጭ ያላቸው አይመስልም፡፡ ምናልባት የኢህአዴግን መቃብር ለማዘግየት አልያም ለማስቆም የሚሞከር እርምጃ በእነ ህሰወሃት በኩል እየተደረገ ስለመሆኑ የተረጋገጡ መረጃዎች ባይኖርም ራስን ከሚመሰረተው አዲስ ሀገር አቀፍ ፖርቲ የማግለል እርምጃ እንደ ዋነኛ አማራጭ ሊኖር እንደሚችል ግን ይገመታል፡፡

ለዚህም ይመስላል በጠቅላይ ሚኒስትር አብይና በኦዲፒ በኩል  የሀገራዊው ፖርቲ አባል ለመሆን የማይፈልግ ድርጅት ካለ ‹መንዱን ጨርቅ ያርግለት› አይነት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ንግግር የሚያስታውስ ምላሽ ያስነገረው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ እንደ ማስረጃ  የሚጠቀስው የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ፤ ለአዲስ ዘመን ሰሞኑን በሰጡት ማብራሪያ    ‹በዓላማ የሚጣጣም ካለና ዓላማውን የሚደግፍ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ አብሮ ለመስራት ከፈለገ የኢህአዴግ በር ክፍት መሆኑን ገልጸው፤ ግን አብረን እንሁን ብሎ ማንንም አያስገድድም ብለዋል። ኢህአዴግ የህዝብ ድርጅት ነው ያሉት አቶ መለሰ፤ በባህሪይው ተራማጅ በመሆኑ እንደየጊዜው ስልቶቹን በመንደፍ አገሪቱን ከኋላ ቀርነት በማውጣትና የዳበረ ዴሞክራሲ በመፍጠር የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት ይሰራል።› ማለታቸውን የዙሩን ክረት ያሳያል፡፡

በመሆኑም ኢህአዴግ የመፍረሱና ወደ መቃብር የመውረዱ ጉዳይ የማይቀር ቢሆንም የኢህአዴግን ግብር ይዘው የሚቀጥሉ እንደ ህወሃት አይነት ድርጅቶች በዚያው መንገድ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ሳያደርጉ የሚቀጥሉበት እድል ዝግ አለመሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ህወሃት ለድርጅት ካድሬዎቹና ለአባላቱ እንደተናገረው ‹ሰማዕታ የወደቁለትን ዓላማ ሳናሳካ ድርጅቱን አናፈርስም› የሚል ይዘት ያለው መልዕክት ማስተላለፉ ተሰምቷል፡፡ ይህም ህወሃት ከኢህአዴግ ውህድ አዲስ ፖርቲ ጋር ላለመጓዝ ፍላጎት እንዳለው ማሳያ ነው፡፡ ህወሃት በዚህ ጊዜ የኢህአዴግን መፍረስ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል በተቃዋሚነት ጎራ ውስጥ የተሰለፉ እንደነ አቶ ሌንጮ ለታ አይነት ድርጅት አስቀድሞ ከኦዲፒ ጋር የመዋሃዳቸው ጉዳይ የመስመር ልዩነቱን ግልፅ ሳያደርገዋል አልቀረም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይም ሆኖ ግን የኢህአዴግ መፍረስና የአዲስ ፖርቲ መመስረት በምን መልኩ ይሆናል የሚለው ውሰብስብ ጥያቄ መቼና እንዴት እንደሚፈታ ለመገመት ሁኔታዎች አስቸጋሪ ናቸው፡፡

ኢህአዴግ የቅርፅ ብቻ ሳይሆን የስም ለውጥም እንደሚያካሂድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገረዋል፡፡ ይህም ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ ከተፈፀሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ሰቆቃዎች ጋር ተያይዞ ስሙ ምቾት ለማይሰጣቸው ወገኖች እፎይታ መስጫ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

ኢህአዴግ ወደ መቃብር መቼ

በጥቂት ጊዜ ውስጥ የጥናቱ ውጤት ተጠናቅቆ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች መክረው የጋራ ካደረጉት በኋላ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ የሚመሠርቱ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር አብይ  ኢህአዴግ በሐዋሳው ጉባዔ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት አጋር ድርጅቶችን ወደ ግንባሩ ለማስገባት ጥናት እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውሰዋል::

“በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ በመላ ኢትዮጵያዊ ጥረትና መስዋዕትነት መሆኑ ተረድተን ካላከበርነው ልክ በፍጥነት እጃችን እንደገባው በፍጥነት ከእጃችን ሊወጣ ይችላል:: ስለዚህም ያገኘናቸውን ድሎችና ውጤቶች በትክክል እያከበርን የቀረውን ለመሙላት መጓዝ ያስፈልጋል” ያሉት ዶ/ር አብይ  “የመንግሥትን የለውጥ እንቅስቃሴ መደገፍ እንዲችሉ የተቋማትን አቅም መገንባት አስፈላጊ ነው:: ከዚህም በተጨማሪ የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማዳበር የሕዝቦች ፈጣንና ወትሮ ዝግጁነት ያለው ተሳትፎ አስፈላጊ ነው::  የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለማየት የሁላችንንም ተሳትፎ ይፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።

“አንድ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ሁላችንም ያለንበት በመፍጠር ሁሉም ኢትዮጵያ እኩል የሚነጋገርበት እኩል የሚወስንበት ድምጹ የሚሰማበት ከየትኛውም ጫፍ ብቃት ያለው ሰው በየትኛውም ኃላፊነት ክለከላ የማይደረግበት ስርዓት ለመፍጠር ለውጡ በፍጥነት እየተጓዘ ይገኛል”  ያሉት ዶ/ር አብይ  ከአጋር ድርጅቶችና የማኅበረሰብ አባላት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎችም ምላሽ ሲሰጡም “ችግሮች የሌሎች ክልል ናቸው ከማለት ይልቅ ኃላፊነትን በመውሰድ የትብብርና መፍትሔ ፈላጊ ባሕልን ማስፈንና በየክልሉ የነዋሪዎችን ቅሬታ መስማት የመሪዎች ተግባር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል:: የህግ የበላይነትን በተመለከተም የሕግ የበላይነት የሚሰፍነው ሕዝቦች ለሰላም ዋጋ ሲሰጡና ሲንከባከቡት እንጂ በጠመንጃ እንደማይመጣ መረዳት መገንዘብ ያስፈልጋል::  የመንግሥት ምጣኔ ሀብታዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ፣ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በማሳደግ ዘርፍ በቅድሚያ የሚከወን ይሆናል” ብለዋል::

ቀዳሚው ቃል

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውሱን ለመፍታት እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት ውስጣዊ ችግሮቹን ፈትቶ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን ያስጠነቅቃሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ ከብሄራዊ ድርጅቶች ግንባርነት ወደ ተዋሃደ አንድ ፓርቲ ለመሸጋገር የያዘው ዕቅድ ሊሳካም ላይሳካም ይችላል የሚሉት ምሁራኑ ለውህደት ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ግንባሩ እና አጋሮቹ መቶ በመቶ የተቆጣጠሩትን የፓርላማ ሥርዓትም ማሻሻል እንደሚገባም አመልክተዋል::

በፖለቲካ ቀውስ እና አለመረጋጋት የሚናጠው ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ ከአመታት በፊት ወጥኜው ነበር ባለው ወደ ተዋሃደ አንድ ፓርቲ የመሸጋገር ዕቅድ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠው ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ በሀዋሳ በተካሄደው ጉባኤ ነበር::

አዲሱ የኢህአዴግ መንገድ ወዴት?

ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔር አገር መሆኗን በተደጋጋሚ የሚጠቅሰው ኢህአዲግ በመተዳደሪያ ደንቡም ይሁን በሚመራባቸው አጠቃላይ የአደረጃጀት መርሆዎች የግንባሩን ዓላማ ለማሳካት ብሔረሰባዊ አደረጃጀቶች ብቻ አዋጭ መሆናቸውን ነው ደጋግሞ የሚገልጸው:: ግለሰቦችን በተናጥል የሚያሰባስብ ኅብረ ብሔር ድርጅት ግን ሕገ መንግሥታዊ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ብሔር ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦችን ለማታገል አቅም አይኖረውም የሚል ዕምነት አለው::  ይህን እምነቱን ንዶ ወደአንድ ሀገራዊ ፓርቲ ራሱን ለመቀየር መወሰኑ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

ይህ ውሳኔ ለ 27 ዓመታት በዘለቀው የግንባሩ አመራር መጻኢ ዕድልም ሆነ በአገሪቱ የወደፊት ጉዞ ላይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ከወዲሁ መተንበይ እንዳማይቻል ብዙዎች ይስማማሉ::

‹‹ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልፅግና›› በሚል መሪ ቃል በሀዋሳ ለሶስት ቀናት በተካሄደው የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ ላይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጉዳዩን አስመለክቶ በሰጡት አስተያየት ኢህአዴግ የሁሉም ህዝቦች ፓርቲ እንዲሆን የተቀመጠው አቅጣጫ በአገራዊ አለመረጋጋቱ ምክንያት ጥናቱ ተጠናቆ ባይደርስም ፣ የክልል አጋር ፓርቲዎች የኢህአዴግ አካል መሆን እንዲችሉ የሚደረግበት ወቅት አሁን መሆኑን አመልክተው ነበር፡፡

የዓመታት ፈተና

እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ የአራት ክልሎች እና የፌዴራል መንግሥቱ ገዢ ፓርቲ ነው። የሌሎቹ አምስት ክልሎች ገዢ ፓርቲዎችን ‘አጋር’ በሚል ይጠራቸዋል። በምርጫ ቦርድ አሠራር ‘አጋር’ አደረጃጀት ስለሌለ ቦርዱ እንደተለያዩ ፓርቲዎች ነው የሚመለከታቸው። ‘አጋር ድርጅቶቹ’ ጋር ኢሕአዴግ ያለው ግንኙነት ግን በምርጫ ቦርድ ያልተመዘገበ፣ ደንቡም ግልጽ ያልሆነ ነው። የሚታወቅ የጋራ የሥራ አስፈፃሚ የላቸውም። ይህ ጉዳይ ኢሕአዴግ የእነዚህን አምስት ክልላዊ መንግሥታት “ሁኑ እንዳላቸው ብቻ የሚሆኑ አሻንጉሊቶች ናቸው” ለሚለው ሕዝባዊ ጥርጣሬ ማረጋገጫ ሆኖ ዓመታትን ዘልቋል ይላል ወጣቱ አክቲቪስት በፍቃዱ ኃይሉ በአንድ ጽሑፉ፡፡ ምክንያቱን ሲያሰቅምጥም ‘አጋር ድርጅቶቹ’ ከኢሕአዴግ ያፈነገጠ ውሳኔ አሳልፈው አለማወቃቸውን ይጠቅሳል፡፡

ፕሬዚዳንት አብዲ ኢሌይ በቁጥጥር ስር ውለው ወደወህኒ ከመወርወራቸው አስቀድሞ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የተፈጠረው ችግር እና የፌዴራል መንግሥቱ ሊቆጣጠረው መቸገሩ የዚህ አዛዥ-ታዛዥነት ዘመን ሊያበቃ እንደሚችል አመላካች ሆኖ አልፏል።

የሶማሊ ክልል የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ ወዲህ ባሉት 23 ዓመታት ውስጥ አሁን በጊዜያዊነት የተቀመጡትን ክልላዊ ፕሬዚደንት ሳይጨምር፥ 10 ፕሬዚደንቶችን አፈራርቋል። ከፕሬዚደንት አብዲ ሞሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌይ) በስተቀር ቀደሚዎቹ ዘጠኝ ፕሬዚደንቶች መካከል ከ3 ዓመት በላይ ሥልጣን ላይ ለአንድ ሙሉ የምርጫ ጊዜ ያገለገለ ፕሬዚደንት በክልሉ አልነበረም። ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ ግን ለ8 ዓመታት ሥልጣን ላይ በመቆየት የክልሉን ሪከርድ ሰብረዋል። የክልሉ አመራሮች ሥልጣን ላይ የማይቆዩት በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጦስ ነው።

ከዚህ አለመረጋጋት በመነሳት የፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ ይህን ያክል ሥልጣን ጨብጦ መቆየት መቻል አስገራሚ ሊሆን ይችላል። ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ ወደ ሥልጣነ መንበሩ ከመምጣታቸው በፊት፥ በወቅቱ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን የኦጋዴን ብሔራዊ  ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ሠራዊትን ከኦጋዴን ጠራርጎ ለማስወጣት የተቋቋመውን ‘ልዩ ፖሊስ’ መርተዋል። ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ የክልሉን ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላም ቢሆን ‘ልዩ ፖሊስ’ በክልሉ የሚንቀሳቀስ ትልቁ የታጠቀ ኃይል ሆኖ ከመቀጠሉም ባሻገር፥ ከፍተኛ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን በማደረስ ሥሙ ይነሳል። ከሁሉም በላይ ግን የፕሬዚደንቱን ሥልጣን ለማስጠበቅ መሣሪያ ሆኗል በመባል ደጋግሞ ይወቀሳል።

የሶማሊ ክልል ነዳጅ የተገኘበት መሆኑ የክልሉን ሀብት አስጠብቃለሁ በሚለው ኦጋዴን እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ዘላቂ ውጥረት ፈጥሯል። ይህም ላለፉት ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች መንስዔ ነበር። በፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ ይመራ የነበረው የሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ) ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ በመሥራት ክልሉ ውስጥ ያለውን ተቃውሞ በኃይል በመቆጣጠር ለክልሉ ጊዜያዊ መረጋጋት አስገኝቶ ነበር። ምንም እንኳን ክልሉ “የኮንትሮባንድ ንግድ መነኻሪያ ሆነ” የሚል አቤቱታ በተደጋጋሚ ቢሰማም፥ ኢትዮጵያ ከአል ሻባብ ጋር በምታደርገው ውጊያ ክልሉ ወሳኝ ጂኦግራፊያዊ ፋይዳ ነበረው። ስለዚህም የፌዴራል መንግሥቱ የክልሉን መንግሥት ጥፋቶች በዝምታ ሲያልፍ ነበር። እንዲያም ሆኖ በፌዴራሉ መንግሥት ውስጥ የነበረው ፖለቲካዊ ውክልና እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።

የአጋር ፓርቲዎች እጣ ፋንታ

ቀጣይ የኢሕአዴግ ‘አጋር’ ፓርቲዎች ሁለት አማራጮች አሏቸው ይላል በፍቃዱ ኃይሉ። ከኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች መርጠው ለአንዱ በመወገን ሌላኛው ላይ የፖለቲካ ብልጫ ማሳየት፤ አልያም ነጻነታቸውን አስከብረው በራሳቸው መወሰን። ይሁን እንጂ፣ እነዚህ የኢሕአዴግ ‘አጋር’ ፓርቲዎች የሚገዟቸው ክልሎች የሕዝብ ቁጥራቸው እንዲሁም የፖለቲካ ልኂቃኖቻቸው ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በተናጠል ፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ደካማ ነው። ይህንን አስቀድሞ የተረዳ የሚመስለው እና በኦሕዴድና ብአዴን ትብብር ተገፍቻለሁ የሚል ቅሬታ ያለው ሕወሓት፥ ከነዚህ የኢሕአዴግ ‘አጋር’ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተወሰነ ተፅዕኖ ለመፍጠር ይሞክር ይሆናል ሲልም ይጠቅሳል።

መቼ ይመሰረታል?

የዘጠኙንም ክልል ፓርቲዎችን ያካተተ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት የተወሰነው ውሳኔ በ11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ላይ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየተጓዘ መሆኑን የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ከሰሞኑ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው ከጥቂት ወራት በኋላ የአፋር፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ፣ የሶማሌ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ  ፓርቲ የሚባል ነገር የለም ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን አቶ ብናልፍ እንዳሉት ውሳኔው ሁሉም ዜጎች በእኩልነት በብቃታቸው እንዲሳተፉ እድል የሚፈጥር ነው።

ለሌሎች ፓርቲዎች ምን ይነግራል?

ኢህአዴግ አጋሬ የሚላቸው ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከቤንሻንጉል፣ ከጋምቤላና ከሐረሪ ክልሎች ለተውጣጡ አካላት የነገረው ይህ የለውጡ እሳቤ ኢህአዴግ ውህደቱ በውስጡ ብቻውን ሳይሆን አጋር ፓርቲዎችን ጨምሮ ለመዋህድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ያረጋገጠ ነው ይላሉ ምሁራን፡፡

እንደሚታወሰው ግንባሩ በ11ኛ ጉባዔው ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው የአቋም መግለጫ ለአጋር ፓርቲዎቹ ተመሳሳይ አቋሙን እንዲህ ሲል ገልጾም ነበር፡፡ “በጉባኤያችን መክፈቻ ስነ – ስርዓት ላይ እንዳስተላለፋችሁት መልዕክት ሁሉ ኢህአዴግም ከእናንተ ጋር በመዋሀድ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ በመሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት እና የሚታገሉበት የጋራ መድረክ ይሆን ዘንድ የጥናት ሥራዎችን ተጀምረዋል፡፡ በመሆኑም እንደ አንድ ህብረ ብሄራዊና ሀገራዊ ድርጅት ለመንቀሳቀስ በሚያስችለን ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታ ላይ መሆናችንን እየገለጽን ለዚህ ዓላማ ስኬት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን”

ይህ የኢሕአዴግ እንቅስቃሴ በብሔር ስም እየተደራጁ ለሚገኙትና ለተደራጁት ፓርቲዎች ምን መልዕክት ያስተላልፍ ይሆን የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡

ከ70 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ አብዛኞቹ በብሄር ስም የተደራጁ ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በተለይ ደግሞ ተቀራራቢ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው በአንድ ላይ በመሰባሰብ ወደ ሦስት ወይም አራት ዝቅ ቢሉ የበለጠ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማጠናከር ጠቃሚ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ህዝብንና ሀገርን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ምክረ ሀሳብ እንደሚደግፉት በመግለጽ ከዚህ ቀደም ባለመሰባሰባቸው ያጡትን ዕድሎች፤ ቢሰባሰቡ ሊያገኙ ስለሚችሉት ጥቅም፤ ለመሰባሰብ ስላለው አስቻይ ሁኔታና ተግዳሮት አስተያየታቸውን መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡

ለፓርቲዎች በተወሰኑ ርዕዮተ ዓለሞች ዙሪያ አለመሰባሰብ የገዢው ፓርቲ ስውር እጆች ትልቁ ችግር ሆኖ ቆይቷል የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ገዥውን ፓርቲ የሚወክሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ፓርቲዎችን ለመፈረካከስ የሚዳርጋቸው ችግር እንደማይኖር እየተናገሩ መሆኑ ዕድል የሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡

ከዚያም አልፎ ኢህአዴግ ራሱን በአንድ ሀገራዊ ፓርቲ ለማዋቀር መወሰኑ ሌሎችን ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡና በጣም ጥቂት ጠንካራ ፓርቲዎች ተመስርተው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ በር ከፋች ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ፍላጎቱ ካላቸው የዚህ አገራዊ ፓርቲ አካል መሆን እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጅ የፖለቲካ ምሁራን ይህ ሁኔታ ይፈጠራል ብለው አያምኑም፡፡ ሁሉንም ግን በጊዜ ሂደት እናያለን፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe