በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ጣት መቀሰር የት ያደርሳል?

71ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ኒውዮርክ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ሲካሄድ እንደሌሎቹ የሃገር መሪዎች ሁሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተሰጣቸውን ደቂቃ የማህበራዊ ሚዲያውን በመውቀስ  የመንግስታቸውን  ‹አቤቱታ› ነበር ለዓለም መሪዎች ያቀረተቡት፡፡ 12 ደቂቃ ገደማ በረዘመው ንግግራቸው ውስጥ ካነሷቸው ነጥቦች አንዱ ማህበራዊ ሚዲያውን የሚመለከት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ሚዲያው እንዲጠፋላቸው የፈለጉ በሚመስል ሁኔታ ምርር ብለው በዓለም አደባባይ ፊት ብሶታቸውን አሰምተዋል፡፡ እንዲህ በማለት፡-

‹‹ማህበራዊ ሚዲያው ምንም እንኳን ዘመናዊ የመረጃ ልውውጥን እያሳለጠ ቢገኝም፣ የህዝብ ለህዝብ ቁርኝትን ቢያጠናክርም፤ በአንጻሩ የአሸባሪዎች መመልመያ፣ የጥላቻ መስበኪያና የተሳሳተ መልእክት ማስተላለፊያ ሆኗል›› የሚል ነው። በተለይ ደግሞ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ መረጃ ተገፋፍተው ወደ አልተገባ መንገድ እየገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹እና ምን ይደረግ?› የሚል ጥያቄ ቢቀርብላቸው ምን ይመልሱ ይሆን? ምንም እንኳን ማህበራዊ ሚዲያው መጥፎ ጎኑ አመዝኗል ብለው በዓለም ህዝብ ፊት አስተያየታቸውን ቢሰጡም የመፍትሔ ሃሳብ ግን አላቀረቡም፡፡ ከላይ ያለው ጥያቄ ቢቀርብላቸው ግን ማህበራዊ ሚዲያው እንዲጠፋላቸው ተማጽኖ የሚያሰሙ ይመስላል፡፡

ሰሞኑንም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐቢይ አሕመድ፣ ስለማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ያስተላለፉት መልዕክት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አተያይ ብዙም የራቀ አይመስልም፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹መርፌ ዓይናማ ናት ባለ-ስለት› በሚል ርዕስ በሰራጩት ፅሑፍ በሀገሪቱ ህግ መሠረት ተቋቁመው ለዓመታት መረጃ ለህብረተሰቡ በሀላፊነት ስሜት የሚሰሩት መገናኛ ብዙሃንን  ስለማጠናከር ሳይሆን ወቅታዊ ስጋት ስለደቀነባቸው ፌስ ቡክ ማተትን ነው የመረጡት  ፡፡

‹የእኛ ሀገር አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦማሪዎችም ልክ እንደ መርፌዋ ናቸው፡፡ እነርሱ ሀገር በሚወጋ መርፌያቸው እየወጉን ሲጓዙ እንደ ክር አያሌዎች መድረሻቸውን ሳይጠይቁ ይከተሏቸዋል፡፡ ድረገጻቸውን የሚያነብላቸው ተከታታይና ደጋፊ ማብዛታቸውን እንጂ ሀገርና ሕዝብ ላይ እየተከሉ ያሉትን አደጋ፣ እየረጩት ያለውን መርዝ ሊያዩት አልቻሉም፡፡› ይላሉ፡፡

‹ባለፉት ጥቂት ወራት ሀገራችን ያስመዘገበቻቸውን የድል ስኬቶች በመዘርዘርና ከእርሱም ትይዩ የገባችበትን የፖለቲካ ቀውስ ለእናንተ በማስታወስ ጊዜአችሁን ማባከን ኣይገባም፡፡ አሁን ያለው ትልቁ ቁም ነገር ከዚህ ከገባንበት አሳሳቢ ቀውስ ራሳችንንም፣ ሀገራችንንም እንዴት እናውጣት የሚለው ነው፡፡› የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹ሁለት የገመድ ጽንፎችን ይዘው የቆሙ ኃያላን በሚያደርጉት ጉተታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አደገኛ ውጥረት ውስጥ የከተቱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ልበ ሥውር ሆኖ ግራና ቀኝን በጥሞና ማስተዋል በተሳነው ጽንፈኛ ቡድን የሀገራችን አየር ምድሯ ሰላምና ተስፋን ከመተንፈስ ይልቅ የስጋትና የውድመት ደመናን አርግዞ የመከራ ዶፉን ሊጥል ከአናታችን በላይ መጣሁ መጣሁ ይላል፡፡ መካረር እዚህም እዚያም በርትቷል፡፡ ተፈጥሮ ነውና የተወጠረና የተካረረ ጉዳይ ቆይቶ መበጠሱ አይቀርም፡፡› ብለዋል፡፡

‹የማን ቤት ጠፍቶ ፣የማን ሊበጅ ፣ ያውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ፣ የሚለው የሽፍቶች ፈሊጥ እንጂ የሰላማዊ ዜጎች መመሪያ አይደለም፡፡ በእውነት ኢትዮጵያዊነት የሚፈተንበት ወቅት እየመጣ ነው፡፡ ማንም ጣፋጭ ዘርና ፍሬ ነኝ ብሎ ሊኮራና ሊመጻደቅ የሚችለው የግንዱ ሥር እስካለ ብቻ ነው፡፡ የግንዱን ሥር ቆርጦና ነቅሎ በቅርንጫፉና በዘሩ መኩራት የሞኝ ጨዋታ ይሆናል፡፡› ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡

‹በውስጣችን አንጠፍጥፈን ያላወጣነው ዐቅም፣ ያልተጠቀምንበት ችሎታ ካለ፣ እርሱን ኢትዮጵያን ለማዳንና ለመገንባት እንጂ በማኅበራዊ ሚዲያ ዐውደ ውጊያ ሀገር ለማተራመስ ልናውለው አይገባንም ነበር፡፡› የሚሉት ዶ/ር አብይ ‹ሥልጣኔ ሕዝብን በዕውቀት መክበብ እንጂ በሐሰት መረጃ ማጨናነቅ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ኃላፊነታቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን መታደግ ነው፡፡ በጣም ጥቂት ለሆኑና ጊዚያዊ ጥቅም ለሚያስገኙ የፖለቲካ ቡድንተኞች አለበለዚያም የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታይና ደጋፊን ማስደሰትና ማስፈንደቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለኢትዮጵያ መሥራት፣ ኢትዮጵያን ማስደሰት እንጂ ኢትዮጵያን በሐሰት መረጃዎች ማሸበር አይደለም፡፡ ሊሆንም አይገባም፡፡

‹በዘመናት ውስጥ የሀገራችንን ህልውና የሚፈታተኑ አያሌ ፈተናዎች ገጥመውን ያውቃሉ፡፡ ነገራችን ቀጥኖ የሚበጠስ የሚመስልበትም ጊዜ ታልፏል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ምንም ብትቀጥን ጠጅ ናት በእንግዳ ደራሽ በውኃ ፈሳሽ የምትፈርስ አይደለችም፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ በጣም የበዙ የሐሰት መረጃዎች ይተላለፋሉ፡፡ ሐሰት ጮኾ ስለተነገረ፣ ጎልቶ ስለተጻፈ፣ በብዙ ሰዎች ስለ ተደገፈ ወይም በታዋቂ ሰዎች ስለተወራ እውነት አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ግን የዘላለም እውነት ነች፡፡ በሐሰት ዜናም ሆነ በአሉባልታ የማትፈርስ ጽኑዕ መሠረት ያላት እውነት ናት፡፡ ታሪክ ወለል አድርጎ እንደሚያረጋግጥልን ሐሳውያን እንጂ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከንቱ ሆነው አያውቁም፡፡

‹ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን እንጂ ለአንዱ እሥር ቤት ለሌላው ቤት አይደለችም፡፡ እገሌ የዚህ ወይም የዚያ ማኅበረሰብ አባል ስለሆነ በተለየ መልክ ተጠቃሚ ወይም ተጎጂ መሆን አለበት ብሎ የሚያስብ ካለ እርሱ የምናሳክመው እንጂ የምንከተለው አይደለም፡፡ የትም እንወለድ፣ የየትኛውም ብሔር አባል እንሁን፣ ኢትዮጵያ ሁላችንንም በእኩልነት ማገልገል አለባት፡፡ ይህ፣ አቋማችን ነበር፤ አሁንም በጽኑ እናምንበታለን፡፡› በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

በመሪዎቹ የተዘነጉት እውነቶች

ኢትዮጵያ የ107 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ ናት፡፡ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ህዝብ የሚኖርባት ሃገር መረጃ የምትለዋወጠው በጣት በሚቆጠሩ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ነው፡፡ እነዚያም ቢሆኑ እንደቦይ በአንድ በኩል የሚፈሱ ፕሮፓጋንዳን ብቻ የሚነዙ ሆነው ቆይተዋል፡፡፡ በዚህም ምክንያት ህዝቡ አንድ አይነት የስብከት ዜናዎችን ለማድመጥ ተገዷል፡፡ በተለያየ ጊዜ ብቅ የሚሉ የግል መገናኛ ብዙሃንም በታክስና በወረቀት ዋጋ መናር ከገበያው ሲወጡ እየታየ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ  ያልተረዱት እውነት ወይም እያወቁ እንዳላወቁ ያለፉት ጉዳይ ሰዎች ፊታቸውን ሙሉ ለሙሉ ወደማህበራዊ ድረገጽ አዙረው መረጃዎችን የሚለቃቅሙት መረጃ ከመንግስት ባለስልጣናት የሚያገኝና ገለልተኛ ሚዲያ በሃገሪቱ ውስጥ ስለሌለ ወይም እንዲፈጠር መንግስታቸው ድጋፍ እያደረገ ባለመሆኑ  ነው፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ

በቴክኖሎጂ በተሳሰረው በአሁኑ ዘመን፤ ማህበራዊ ሚዲያ በመላው አለም በተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ሰዎችን ግንኙነት በማመቻቸት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በተለይም ስማርት ስልኮች ከተፈጠሩ በኋላ ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጨምሯል፡፡ ከአፍሪካ ህዝብ 10 በመቶ የሚሆነው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በአገራችን ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ የዋለው ማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ሲሆን 97.84 በመቶ የሚሆነው የኢንተርኔት ተጠቃሚ የፌስቡክ ተጠቃሚም እንደሆነ ይነገራል፡፡ ፌስቡክ በአሜሪካዊው ማርክ ዙከርበርግ እና ጓደኞቹ አማካኝነት የካቲት 1996 ዓ.ም ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተቋቋመ ማህበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ከጅምሩ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበራዊ ግንኙነት ታስቦ የተዘጋጀ ቢሆንም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ግን እድሜው ከ13 በላይ ለሆነ ለማንኛውም የኢንተርኔትተጠቃሚ ክፍት ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ከ3.7 ሚሊዮን በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንደሚገኙ ይታመናል፡፡ ከፌስቡክ በተጨማሪ በኢትዮጵያ በርካታ ተጠቃሚ ያላቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች ዩቲዩብ እና ትዊተር ናቸው፡፡

ማህበራዊ ሚዲያ ጥቅምና ጉዳቱ

በተለያዩ ወገኖች የማኅበራዊ ሚዲያ ሉታዊ እና አዎንታዊ ፋይዳ ሁሌም ቢሆን የጦፈ ክርክር እንዳስነሳ ነው፡፡ “ታማኝ የመረጃ ምንጭ ሊሆን አይችልም፤ ሰዎችን ለማታለል ሊውል ይችላል፤ ሰዎች በአካል እንዳይገናኙ እንቅፋት በመፍጠር ላልተገባ የሥነ ልቡና ቀውስ ይዳርጋል” ወዘተ. በማለት ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያላቸውን ቅሬታ ከሚያሰሙት ጀምሮ አንድሪው ኪንን የመሳሰሉ ጸሐፊያን “The cult of the amateur writing” የሚል መጽሐፍ በማሳተም ማኅበራዊ ሚዲያውን በስፋት ተችተዋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያን የሚተቹ ወገኖች እንደ ማስረጃ ከሚያወሷቸው ነጥቦች አንዱ በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ይፋ የሆነውንና “ማኅበራዊ ሚዲያን አዘወትሮ ጠቀም ሱስ ያስይዛል፡፡” የሚለውን ግኝት መሠረት ያደረገው ጥናት ነው፡፡ በተለይ በተመራማሪዎቹ ስም የወጣለት “FOMO” (fear of missing out) /በአማርኛው የመረሳት ፍርሃት/ ጥናቱ በተካሔደባቸው ብዙ ተማሪዎች ላይ መታየቱ የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ጎን ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል፡፡

በአንጻሩ በርካቶች ማኅበራዊ ሚዲያን በእጅጉ በማወደስ የብዙ ለውጦች መንስኤ መሆኑን ያወሳሉ፡፡ “መድኃኒት አሉታዊ ጎኖች አሉት ተብሎ አልወስድም እንደማይባለው ሁሉ ማኅበራዊ ሚዲያም ከአጠቃቀም ጉድለት በሚያስከትለው ችግር ሳቢያ በደፈናው መወገዝ የለበትም፡፡” በማለት ይከራከራሉ፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር ተጠቃሚ ያለው ማኅበራዊ ሚዲያው “እልፍ” አዎንታዊ ፋይዳዎች ያሉት መሆኑን የተለያዩ ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡ ሰዎች በነጻነት ሐሳባቸውን ለመግለጽ፤ የተደራጀ እንቅስቃሴን በቀላሉ ለማስተባበር፤ የተለያዩ ዕውቀቶችን ለማግኘት፣ የሥራም ሆነ ሌሎች መልካም ዕድሎቻቸውን ለማሳደግና፣ በጣም ጠቃሚ መረጃዎችን በፍጥነት ለመለዋወጥ ማኅበራዊ ሚዲያው የላቀ ጥቅም እንደሚሰጥ የሐርቫርድ፣ ጆን ሆፕኪንስ፣ ኮሎምቢያ እና ስታንፎርድ የመሳሰሉ የአሜሪካ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች ምሁራንን አሳምኗል። ከዚህም ባሻገር ለተማሪዎቻቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ዘላቂ ጥቅምን ሊያገኙ የሚችሉበትን ልዩ ኮርስ አዘጋጅተው የ”ምርጥ ሶሻል ሚዲያ ተሞክሮ” ትምህርትን እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከአመታት በፊት በሄይቲ የደረሰው እጅግ ከፍተኛ የሆነ የመሬት መናወጽ ለ220,000 ሰዎች ሞት እና 30 ሺሕ ሕንፃዎች መደርመስ ምክንያት ሆኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በጊዜው የአሜሪካ ቀይ መስቀል ለዚህ ዘግናኝ አደጋ እርዳታ ለማሰባሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ፣በዋነኝነትም በትዊተር ባደረገው ቅስቀሳ በ24 ሰዓታት ብቻ ከ126 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማሰባሰብ በቅቷል፡፡ በግብጽ ለተከሰተው አብዮት ብሎም በዐረቡ ዓለም ለታየው መነሣሣትም ማኅበራዊ ሚዲያ በተለይ ፌስቡክና ትዊተር የላቀ ሚና መጫወታቸው ይታወሳል፡፡ በአሜሪካዋ ቦስተን ከተማ በቅርቡ የተካሔደውን የማራቶን ሩጫ መሠረት አድርጎ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት አድራሾች ማንነት ለመለየት ከምንም በላይ የላቀ ሚና የተጫወተው የፍሎሪዳው ነዋሪ ዴቪድ ግሪን በማኅበራዊ ሚዲያ ያሠራጨው የፍንዳታውን ክስተት የሚያሳይ የሞባይል ፎቶ ነበር፡፡ ኤፍ ቢ አይም በሶሻል ሚዲያ የተገኘውን ፎቶ ‘የቦንብ ጥቃቱን አድራሾች ለመለየት ያስቻለ ምርጥ መረጃ’ ሲል ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡ በዚህ መልኩ በመላው ዓለም ማኅበራዊ ሚዲያ በሰው ልጆች በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሆነ ሌሎች የሕይወት መስተጋብሮች ውስጥ አቻ የሌለው ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

ምን ይደረግ

በሃገሪቱ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ መገናኛ-ብዙሃኑ ህዝቡን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ በማስተማርም ሆነ መረጃ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችሉ ነበር፤ እንዲሁም የመከራከሪያ መድረክ በመሆን ሊያገለግሉም ይችሉ ነበር፤ ይሁን እንጂ መንግስት በሃገሪቱ ላለው ብቸኛ የበላይነት የግሉን መገናኛ-ብዙሃን ከመደገፍና ከማበረታተት ይልቅ ትኩረቱን በፌስቡክና በሌሎች ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ በማድረግ የገፅታ ግንባታውን ለማግኘት ሲጥር ዋናው መገናኛ ብዙሃን በአቅም ችግር ሳቢያ እየተዳከመ ይገኛል፡፡ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንም በገቢ እጥረት ሳቢያ ለጋዜጠኞቻቸው ደሞዝ መልክፈል እያቃታቸው ሲዘጉ እየታየ ነው፡፡ እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ላይ ሲሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞችም ፊታቸውን ብዙም ወጪ በማይጠይቀው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በማዞር በግልፀም በድብቅም የመሰላቸውን ሲፅፉ እየታየ ነው፡፡በመሆኑም መንግስት በሀላፊነት ስሜት  የሚሰሩ ሚዲያዎችን በመደገፍና በማበረታትታ የማህበራዊ ሚዲያውን ተፅእኖ መቀነስ ሲችል ጣትን ወደ ሌላ አካላት ላይ መቀሰሩ ብዙም የሚዋጣ አይመስልም፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe