ቡና ባንክ  ከግብር በፊት 937 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

ከ16 ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ቡና ባንክ አ.ማ ዓመታዊውን የባለአክሲዮኖች 12ኛ መደበኛ እና 5ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ እሁድ ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም አካሂዷል።

በጎልፍ ክለብ ግቢ ውስጥ በተካሄደውና በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖች በታደሙበት በዚሁ ጉባኤ ላይ የቡና ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ሰውአለ አባተ የባንኩን የ2020/21 ዓመታዊ ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች በንባብ አቅርበዋል።

ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው ባንኩ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከግብር በፊት 937 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ከ20 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ ችሏል።

በቀረበው ሪፖርት ላይ ይፋ እንደተደረገው ባንኩ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2021 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ6.58 ቢሊዮን ብር ማሳደግ የቻለ ሲሆን ይህም የባንኩን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ47.5% በማሳደግ 20.46 ቢሊዮን ብር እንዳደረሰው ተነግሯል። ከዚህ ውስጥ የቁጠባ ሂሳብ 78.6 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ ድርሻ ይዟል።

ዶክተር ሰውአለ በንግግራቸው እንዳሰመሩበት ከሆነ የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ሌሎችም ችግሮች በአገር አቀፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደሩትን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ተቋቁሞ አትራፊነቱን ማስቀጠል የቻለው ቡና ባንክ በአጠቃላይ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት በላቀ ደረጃ ላይ መገኘት መቻሉ የሚያበረታታ ውጤት ነው ብለዋል።

በቦርድ ሊቀመንበሩ የቀረበው ሪፖርት የባንኩን የብድር አፈጻጸምም አብራርቶታል። በዚህ መሰረት ባንኩ በዓመቱ ውስጥ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በአጠቃላይ 6.73 ቢሊዮን ብር ማበደሩ የተገለጸ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያበደረው የገንዘብ መጠን በ58 በመቶ አሳድጎ 18.29 ቢሊዮን ብር ያደረሰው መሆኑም ተጠቁሟል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለምአቀፍና ሃገር አቀፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ባሳደረው ተጽእኖ ሳቢያ ከውጭ ሃገር የሚላክ ሀዋላ መቀነሱ እንዲሁም የኤክስፖርት ስራ መቀዛቀዙ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል የባንኩን አፈፃፀም በተጠበቀው መልኩ እንዳይከናወን አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ያብራራው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሪፖርት ባንኩ በዓመቱ ካገኘው 164 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ውስጥ የወጪ ንግድ 61.8 በመቶ የሚሆነውን በመሸፈን ቀዳሚ መሆኑን አመልክቷል።

ባንኩ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ቁጥራቸው ከአስር የውጭ ሃገራት ባንኮች ጋር የቀጥታ ግንኙት መስርቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ሪፖርቱ አብራርቷል።

በቦርዱ ሊቀመንበር ዶክተር ሰውአለ አባተ ሪፖርት ውስጥ ከተካተተው አንዱ የባንኩን ጠቅላላ ሃብት የተመለከተ መረጃ ሲሆን እንደሪፖርቱ የባንኩ ጠቅላላ ሃብት በበጀት ዓመቱ የ7.08 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቶ 25.96 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

የባንኩን ካፒታል በተመለከተ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት እንዳብራራው በበጀት አመቱ የብር 706.2 ሚሊዮን ብር እድገት አሳይቷል። ይህም የባንኩን አጠቃላይ የካፒታል መጠን 3.81 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡

እንደሪፖርቱ ቡና ባንክ ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ብሎም የተቀማጭ ማሰባሰቡን ሥራ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል በበጀት ዓመቱ 43 ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ይህም ባንኩ የበጀት አመቱ እስካለቀበት ሰኔ 2020 መጨረሻ ድረስ የከፈታቸውን ቅርንጫፎች መጠን 285 አድርሶታል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምቹ የባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብና አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት ረገድ ባንኩ ባደረገው እንቅስቃሴ በበጀት ዓመቱ የተቀማጭ ሂሳብ ደንበኞቹን ቁጥር ከ576ሺህ በላይ ከፍ በማድረግ የ71.5 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። ይህም አፈጻጸም የባንኩን አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር በዓመቱ መጨረሻ ወደ 1 ሚሊዮን 388 ሺህ 519 ከፍ አድርጎታል።

ከዚህ በተጨማሪም በበጀት አመቱ ባንኩ በሰጠው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በዋዲያና ቀርድ ከወለድ ነጻ ሂሳቦች በበጀት ዓመቱ ብቻ 45,672 ደንበኞችን በማፍራት አጠቃላይ የደንበኞቹን ቁጥር ከ576ሺህ በላይ አድርሷል ብለዋል። በዓመቱ ውስጥ 400 ሚሊዮን ብር ከወለድ ነጻ ተቀማጭ ገንዘብ በመሰብሰብ አጠቃላይ የወለድ ነጻ ተቀማጭ ገንዘብ 576ሺህ 026 ማድረሱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል።

ሪፖርቱ በዋናነት ካካተታቸው አብይ ተግባራት መካከል የባንኩን የማህበራዊ ሃላፊነት የተመለከተው ሪፖርት ይገኝበታል። ቡና ባንክ በሃገር ግንባታ እና የህዝብን ህይወት ለመለወጥና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በመንግስት በሚካሄዱ ጥረቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለቀረበለት ጥሪ በሰጠው ምላሽ በበጀት አመቱ በድምሩ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የማህበራዊ ሃላፊነት ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe