ቢጂአይ ኢትዮጵያ የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ለመግዛት ከስምምነት መድረሱ ተነገረ

ቢጂአይ ኢትዮጵያ የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ከዲያጆ ኩባንያ ለመግዛት ስምምነቱን ማጠናቀቁና የግዢ ስምምነቱን ወደተግባር ለመቀየር የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣንን ይሁንታ  በመጠባበቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ።

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ግዢውን ከፈጸመ በኋላ በዘርፉ የካበተ እውቀትና ልምዱን በመጠቀም በብዙሃን ዘንድ ታዋቂና ተወዳጅ የሆነውን የሜታ ብራንድ ከነ ሙሉ ክብሩ ለማስቀጠል፥ የሜታ ሠራተኞችን ፍቅርና የስራ ተነሳሽነትም ከፍ ለማድረግ እቅድ መያዙን ነው በግዢው ዙሪያ የወጣ መረጃ የሚጠቁመው።

ቢጂአይ እንዲህ ዓይነት ግዢ ሲፈጽም የዋና ዋና ባለድርሻዎችን ፍላጎትና ስጋት ተገንዝቦና የያንዳንዱንም ጥቅም መጠበቁን አረጋግጦ ሲሆን የገዛውን ድርጅት ከራሱ ጋር  አዋሕዶ በብቃትና የበለጠ ውጤት ሊሰጥ በሚችል መልክ መምራትም የተካነበት ተግባር ነው ይላሉ የኩባንያው ምንጮች።

እንደመረጃዎቹ ማብራሪያ ቢጂአይ በተለይ ሜታ ቢራ ፋብሪካን ዚገዛ የፋብሪካውን  ሠራተኞች እና በሰበታ የሚገኘውን ማህበረሰብ ጥቅሞች ሁሉ እንደተጠበቁ ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን በበለጠ እና በተጠናከረ መልኩ ለማሳደግ የሚያስችል ማሻሻያም ያደርጋል ተብሏል።

ቢጂአይ ሜታ አቦን መግዛቱ እንደቀደመ አሰራሩ የቢራ ፋብሪካዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎችና ከዚያም ባሻገር በሚኖሩ ዜጎች ሕይወት ላይ የኩባንያውን አዎንታዊ አሻራ ለማሳረፍ ነድፎ ከሚተገብረውና በብዙዎች ዘንድ መልካም ስም ካተረፈበት የማኅበራዊ ኃላፊነት ፕሮግራሙ ጋር የተስማማ መሆኑም ተገልጿል።

የቢጂአይ ግዢ ለሜታ ብራንድ፣ ለሠራተኞች እና አከፋፋዮች እንዲሁም ለሰፊው የሰበታ ማህበረሰብ መልካም የምስራች ሊሰኝ የሚችል ነው ያለው መረጃው ግዥው ለብራንዱ፣ ለሰራተኛውና ለሰበታ ማህበረሰብ አዳዲስ የዕድል በሮችን እንደሚከፍትም ነው የተነገረው።

ቢጂአይ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣንን ይሁንታ እንዳገኘ ግዢውን በተመለከተ የገባውን ስምምነት በማጠናቀቅ በፍጥነት የኢንቨስትመንት ማስፋፋት እና ከላይ የተዘረዘሩትን የማኅበራዊ ኃላፊነት ተግባራቱን ለመወጣት ማቀዱ ተገልጾ ይህንኑ ወደተግባር ለማስገባትም በጉጉት የሚጠባበቀው የባለስልጣኑን ይሁንታ ብቻ መሆኑም ተገልጿል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe