ተፈናቃዮችን በግዳጅ ወደቀያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ጥረት እንዳሳሰበው አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ገለጸ።

ባለፈው ዓመት በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በግዳጅ ወደቀያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ጥረት እንዳሳሰበው ሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ ባወጣው ተፈናቃዮችን የተመለከተ ሪፖርት ላይ በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በጫና ወደቀያቸው እንዲመለሱ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን አመልክቷል።

“ይህ የመንግሥት እርምጃ፤ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ የበለጠ የከፋ ያደርገዋል” ሲሉ ባለፈው መስከረም ወር ወደ አካባቢ ተጉዘው የነበሩት የግብረሰናይ ድርጅቱ ባለሙያ ማርክ ያርኔል ተናግረዋል።

ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ አቅንቶ የነበረው የሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል ልኡክ እንዳለው የመንግሥት ባለሥልጣናት ተፈናቃዮቹ ወደመጡበት እንዲመለሱ ለማስገደድ ወደተጠለሉባቸው ካምፖች ድጋፍ እንዳይደርስ እንደሚደረግ አመልክቷል።

በተጨማሪም ወደቀያቸው ከተመለሱ እርዳታን እንደሚያገኙ ቢነገራቸውም ቤታቸው በግጭቱ መውደሙንና በአካባቢያቸውም አስተማማኝ የደህንነት ሁኔታ እንደሌለ ተገልጿል።

ቢሆንም ግን ባለፈው ወር በፌደራል መንግሥቱ የቀረበው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚመለከተው ዕቅድ ላይ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለሱ ሥራ “በፈቃደኝነታቸው ላይ የተመሰረተ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀና ዘላቂ ድጋፍን የሚያገኙበት” እንደሚሆን ተገልጾ ነበር ይላል ሪፖርቱ።

ሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል እንደሚለው መንግሥት በተቃራኒው ተፈናቃዮችን በማስገደድ እንዲመለሱ እየያደረገ ነው ይላል። አክሎም በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮቹ ተጠልለውባቸው የነበሩ ቦታዎችን በማፍረስ ጭምር ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን አሰታውቋል።

መንግሥት ስደተኞችን በተመለከተ እየወሰደ ባለው እርምጃ ከዓለም ዙሪያ እየተመሰገነ ባለበት በዚህ ወቅት፤ የራሱን ተፈናቃይ ዜጎችን የያዘበት መንገድ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ከሰብዓዊነት የራቀ ነው” ሲሉ ኮንነውታል። ያርኔል እንዳሉት “ይህ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው።”

ሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል አክሎም አሁን እየተካሄደ ያለው የመመለስ ጥረት በፈቃደኝነት፣ በዘላቂነትና ከተፈናቃዮቹ ጋር በመተባበር የሚደረግ እስከሚሆን ድረስ እንዲቆም እንዲደረግ ጥሪውን አቅርቧል።

ከሳምንት በፊት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም እንደተናገሩት በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደቀያቸው ለመመለስ መንግሥት ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተው 875 ሺህ የሚደርሱት መመለሳቸውን ገልጸው ነበር።

ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው በሚመለሱበት ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው አያያዝ ተግባራዊ እንደሚደረግና ደህንነታቸው ተጠብቆ የሚያስፈልጋቸው መሠረተ ልማት ተሟልቶ እንዲሆን መንግሥት ጥረት እንደሚያደርግ ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል።

ምንጭ፡ DW

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe