የኤርትራው ፕሬዚዳንት ‹‹እጃቸው የት ይደርሳል?››
ከሰሞኑ የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ከመንግስታቸው መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ብዙ ነገሮችን አንስተዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነትና ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ሰፊ ሃሳቦችን አንስተዋል፡፡
የምፅዋና የአሰብ ወደቦች፣ ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኙ መንገዶች፣ የህወሃትን ጉዳይ እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያን በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከቱ ጉዳዮች በቃለ ምልልሳቸው ላይ ተነስተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታም አንስተዋል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ስምምነት ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ማንኛውም ፖለቲካዊ ለውጥ ኤርትራን እንደጎረቤት ሳይሆን ራሷን በቀጥታ ስለሚጎዳት “እጃችንን አጣምረን ቁጭ አንልም” ብለዋል። ጥያቄው ታዲያ ‹‹የሚዘረጋው እጃቸው አስከምን ድረስ ይረዝማል?›› የሚል ነው፡፡
የአሰብ ነገር
የአሰብና ምጽዋ ወደቦችን አገልግሎት ውጤታማነት ለመጨመር የማደስ፣ የማስፋትና የማሳደግ ስራዎች ለማከናወን እቅድ መያዙን በቃለ ምልልሳቸው ያነሱት ፕሬዚዳንቱ “ወደቦቹን ስናሻሽል ኢትዮጵያን ብቻ እያሰብን አይደለም፤ ዋነኛ ትኩረታችን ቀይባሕር በቀጠናው ላይ ያላትን ቦታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰፋ ያለ አገልግሎት እንዲሰጡ ያለመ እቅድ ነው” ብለዋል፡፡
“ከተጋገዝን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ስለምንችል በአካባቢው ኢኮኖሚያዊ ውህደት መፍጠር አንዱ የመንግስታችን ዓላማ ነው›› ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከወደቦች በተጨማሪ ከመንገድ ግንባታ ጋር የተያዙ እቅዶችም ላይ መረጃ የሰጡ ሲሆን፤ በዚህም ኢትዮጵያንና ኤርትራን የሚያገናኙ መንገዶችም የሚያስፈልጋቸውን ጥገናም ሆነ ግንባታ ለመስራት መንግሥታቸው ማቀዱን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ከአሰብ በደባየሲማ ኢትዮጵያን የሚያገናኘውን መንገድ የማስፋት፤ ከምጽዋ በደቀመኃሪ አድርጎ ዛላምበሳ የሚያገናኙት የአስፋልት መንገዶች ደግሞ የማሻሻል ስራዎች በዚህ አመት እንደሚጀመሩና፤ የተጀመሩትም እንደሚጠናቀቁ ገልፀዋል።
ሰባት የመርከብ መቆሚያዎች ያሉት የአሰብ ወደብ ኢትዮጵያ ከምትገለገልበት ጅቡቲም ይሁን ሽርክና ከገባችበት በርበራ በተሻለ ቅርበት ላይ ቢገኝም ለሁለት አስርት አመታት ሥራ ፈቶ ቆይቷል። ከ6-20 ቶን ማንቀሳቀስ የሚችሉ 18 ቋሚና ሰባት ተንቀሳቃሽ የዕቃ መጫኛና ማውረጃ ክሬኖች፣ 280 ሺህ ቶን ዕቃ ማስቀመጥ የሚችል ቦታም አለው።
በደቡባዊ ኤርትራ ከጅቡቲ ድንበር በ55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አሰብ እንዲህ እንደዛሬ ጊዜ ሳይጥለው ሥራ ከሚበዛባቸው የአፍሪቃ ቀንድ ወደቦች መካከል አንዱ ነበር። በወታደራዊ እና የስለላ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሰራው ግሎባል ሰኪዩሪቲ የተባለ ተቋም በድረ-ገፁ እንዳሰፈረው በጎርጎሮሳዊው 1988 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሰባ በመቶ የገቢ እና ወጪ ንግዷን የከወነችው በአሰብ ወደብ በኩል ነበር። በጎርጎሮሳዊው 1986/87 የበጀት አመት መጨረሻ ከ2.8 ሚሊዮን ቶን በላይ የደረቅ ጭነት በአሰብ በኩል ተንቀሳቅሷል። ከዚህ ውስጥ 66 በመቶው ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ሸቀጥ 792 ሺሕ ቶን ደግሞ በወደቡ ለሚገኝ ማጣሪያ የታለመ ድፍድፍ ነዳጅ እንደነበር ይኸው ድረ-ገፅ ያትታል።
ኤርትራ እንደ አገር ስትቆም ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን ያለ ክፍያ እና ያለ ገደብ እንድትጠቀም ሁለቱ መንግሥታት ስምምነት ነበራቸው። የዓለም አቀፍ ወቅታዊ ጉዳዮች ጥናት ማዕከል (The Institute of Current World Affairs) ተመራማሪው ማርክ ሚካኤልሰን እንደፃፉት በወቅቱ ከወደቡ ሥራ 95 በመቶው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ አሊያም ከኢትዮጵያ የሚወጡ ሸቀጦችን ማስተናገድ ነበር። የጨው አምራች እና የነዳጅ ማጣሪያ ሰራተኞች ኅልውናም መቶ በመቶ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ጥገኛ ነበር።
የጭነት ማመላለሻ መኪኖች አሽከርካሪዎች፣ የመርከብ ሰራተኞች፣ እና ነጋዴዎች የሚያዘወትሯት አሰብ ሞቅ ደመቅ ያለች ነበረች። ግንቦት 1990 ዓ.ም ደርሶ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወዳጅነት ሲቀዛቀዝ ግን አሰብም ወደ ሥራ ፈትነት አዘነበለ። ወይም የወደብ እንቅስቃሴው እጅጉን ተዳከመ።
ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን ብትገልጽም በትክክል መቼ እንደሁ ግን የሚታወቅ ነገር የለም። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የምፅዋ ወደብን በጎበኙ ወቅት መቐለ የሚል መጠሪያ የተሰጣት የኢትዮጵያ እቃ ጫኝ መርከብ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ የኤርትራን ሸቀጥ ለመጫን ከምፅዋ ወደብ ደርሳለች። መርከቧ ምፅዋ የደረሰችው ቢሻ ተብሎ ከሚታወቀው የኤርትራ የማዕድን ማውጫ ሥፍራ የተመረተ ዚንክ ወደ ቻይና ለማድረስ ነበር።
ከጅቡቲ የወደብ ጥገኝነት ለመላቀቅ በበርበራ የወደብ ልማት ሽርክና ለገባችው ኢትዮጵያ አሰብ የተሻለ ቅርበት አለው። የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት መሥሪያ ቤት ያዘጋጀው ሰነድ እንደሚጠቁመው የአሰብ ወደብ ሰባት የመርከብ መቆሚያዎች አሉት። ወደቡ ከስድስት እስከ 20 ቶን ማንቀሳቀስ የሚችሉ 18 ቋሚ እና ሰባት ተንቀሳቃሽ የዕቃ መጫኛ እና ማውረጃ ክሬኖች፣ 280 ሺህ ቶን ዕቃ ማስቀመጥ የሚችል ቦታም ተዘጋጅቶለታል።
ሁለቱ ሃገራት አሁን ያላቸው ግንኙነት በህግና በፍቅር ጸንቶ መዝለቅ ከቻለ ኢትዮጵያም ሆነ ኤርትራ በአሰብ ወደብ የሚያገኙት ጥቅም ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
የባድመ ነገር
“የኤርትራ ሉዓላዊ መሬት ያልተመለሰው በህወሓት እምቢታ ነው” ይላሉ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የባድመን ጉዳይ በማንሳት፡፡
ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ ላይ በተለይ ኤርትራ ከኢትዮጵያና ሌሎች ጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት አስመልክተው ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህ ንግግራቸው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መበላሸት ምክንያት ስለሆነው የድንበር ጥያቄ አንስተው በተለይ በባድመ ጉዳይ ስምምነቱ እንዳይፈጸም ህወሓት እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰዋል።
“በወረራ የተያዘው የኤርትራ ሉዓላዊ መሬት ያልተመለሰው ህወሓት እምቢ በማለቱ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ።
ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የተደረገው የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት እልባት ይሰጣል የተባለውን የድንበር ጉዳይ በማስመልከት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ በሰጡት ማብራሪያ ህወሓት በድንበሩ ጉዳይ የወሰደውን አቋም ተችተዋል።
“ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የተናገሩት የስምምነት ሃሳብ ሳይተገበር የባድመ የድንበር ሁኔታ እንደምናየው ድሮ ከነበረበት ደረጃም በላይ በከፋ ሁኔታ ነው ያለው። ሕጋዊ ውሳኔ ተሰጥቷል፤ በዚሁ መሰረት ውሳኔው ተከብሮ የተወረረው ሉዓላዊ መሬት ወደ ኤርትራ መካለል ነበረበት። አሁን ግን አልተቻለም። ለምን አልተመለሰም ያልን እንደሆነ፤ የከሰረው ስብስብ (ህወሓት) የድንበርን ጉዳይ በአንድ በኩል እንደ ማስፈራሪያና በሌላ በኩል ደግሞ እንደ መቋመሪያ ስለያዘው በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በባድመ ጉዳይ ምን ሰራን ካልን፤ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ሳንገባ በአጭሩ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል” ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅትም ለጦርነቱ መነሻ በነበረችው ባድመ መሬት እየተሸነሸነ እየታደለ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ደግሞ የድንበሩን ጉዳይ እልባት ላለመስጠት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። “ለኤርትራ በተወሰነው መሬት ላይ መሬት ለማን እየታደለ እንደሆነ መረጃ አለን” ሲሉም አክለዋል፡፡
በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የተወሰነውን የድንበር ጉዳይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እንደሚቀበሉ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚንስትሩ ውሳኔውን እንደሚቀበሉ ካሳወቁ ከአንድ ዓመት በኋላ የድንበሩን ጉዳይ ለመፍታት የተሰራ የሚታይ ነገር እስካሁን የለም። ለኤርትራ የተወሰነው የባድመ መሬት አሁንም በኢትዮጵያ እጅ ነው የሚገኘው። ይህም ጉዳይ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወዴት እንደሚወስደው ገና አልለየለትም፡፡
በኢትዮጵያ ጉዳይ
ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክተው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “በባድመ ድንበር ብቻ ሳንታጠር፤ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ በሁሉም አቅማችን እንደግፋለን” ብለዋል።
“ሰላም ሰርተህ የምታመጣው እንጂ እንደመና ከሰማይ የሚወርድ አይደለም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመሩትን የሰላም ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ስምምነት ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን በመጠቆም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ፖለቲካዊ ለውጥም ኤርትራን እንደጎረቤት ሳይሆን ራሷን በቀጥታ ስለሚጎዳት “እጃችንን አጣምረን ቁጭ አንልም” ብለዋል። እጃቸውን የት ድረስ እንደሚያስረዝሙ ግን አልገለጹም፡፡
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለሦስት ትውልድ የተደረገው ጦርነት “ትርጉም አልባ ነበር” በማለት ጦርነቱም የውጭ ኃይሎች ጉዳዩን ስላወሳሰቡት የመጣ ጣጣ እንደነበር ገልጸዋል ፕሬዚዳንቱ።
የሁለቱ ሀገራት ፈተናዎች
ከአንድ ዓመት በፊት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የተመራውን የልኡካን ቡድን እራት በጋበዙበት ምሽት ባለፉት 25 አመታት የተፈጠሩ ሰላም የማስፈን እድሎች በሁለቱ አገራት መሪዎች እምቢተኝነት ምክንያት ለፍሬ አለመብቃታቸውን ገልፀው ያለፈው ጊዜ እንዳይደገም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አብረው ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድም “የዜጎችን ተጠቃሚነት እንዳናረጋግጥ የተጋረጠብንን የመለያየት ግድግዳ አፍርሰን፣ ላለፉት 20 አመታት ከባድ ኪሳራ ያደረሰብንን ሞት አልባ ጦርነት ቋጭተን፣ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር የጀመርነዉ ጉዞ እንደሚሳካ አልጠራጠርም” ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ «የአስመራ መግለጫ» የተባለዉን ውል የፈረሙት ዐቢይ አስመራን በረገጡ በነጋታዉ ነበር። የአስመራና የአዲስ አበባ መንግሥታት ጦራቸዉን ካዋሳኝ ድንበሮች ማንሳት፣ የየብስና የአየር መስመሮችን መክፈት፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን መቀጠልን ጨምሮ ስር የሰደደዉን ጠብ ለማስወገድ የሚረዱ በርካታ እርምጃዎችን ወስደዋል። ብሪታንያዊቱ የኤርትራ ጉዳይ ከፍተኛ አጥኚና ደራሲ ሚሻኤላ ሮንግ እንደሚሉት ግን የሁለቱ ሐገራት ግንኙነት አጀማማሩ ላይ የነበረዉ ዓይነት ተስፋ አልቀጠለም። «ድንበርን የማካለል ምልክት እስካሁን የለም። ነገሮች ተስፋ እንዳደረግነዉ አይደሉም። በጣም አሳሳቢዉ ኤርትራዉያን ወጣቶች ለብሔራዊ ውትድርና መመልመላቸዉ ነዉ። ነገሮችም በተፈለጉበት እና ተስፋ በተጣለባቸዉ መንገድ አልተሻሻሉም። ዋናዉ ነገር በኤርትራ አሁንም የብሔራዊ ውትድርናዉ ተጠናክሮ ቀጥሎአል። በዚህም ዋናዉ እና አሳሳቢው ነገር ኤርትራዉያን ሃገራቸዉን እየጣሉ መሰደዳቸዉ ነዉ» ይላሉ ሚሻኤላ፡፡
ሃገራቱ ለዓመታቶች ዘግተዉ የቆዩትን ድንበር ከፍተዉ መልሰዉ የዘጉበት ምክንያት ምን እንደሆን በግልፅ የታወቀ ነገር የለም ያሉት ብሪታንያዊቱ የኤርትራ ጉዳይ ከፍተኛ አጥኚ ሚሻኤላ ሮንግ ፤ የኤርትራ መንግሥት ለምን እንደዘጋ በግል ይፋ ያደረገዉ ነገር የለም የአስመራዉ መንግሥት ግልፅ እንዳልሆነ ይታወቃል ሲሉ ገልፀዋል። እንድያም ሆኖ በሁለቱ ሃገራት መካከል የንግድ እና የመገበያያ ገንዘብ ጉዳይ በሁለቱም መንግሥታት ስላልተቋጨ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።
«እንደምገምተዉ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ከኢትዮጵያ ሸቀጦቻቸዉን ይዘዉ ወደ ኤርትራ መግባታቸዉና አብዛኛዉ ኤርትራዉያ ሸቀጡን መግዛት ባለመቻላቸዉ ይመስለኛል። በርካታ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ኤርትራ ዉስጥ ንግድ መጀመራቸዉ ለሀገሪቱ የንግድ ባለሥልጣንም አላመቸ ይሆናል። የድንበር መዘጋቱ ምክንያት ይህን እና የመሳሰሉት ነገሮችን ለመቆጣጠር ያደረጉት ርምጃ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ሃገራቱ የመገበያያ ገንዘብን በተመለከተ ምንም የተስማሙበት ነገር የላቸዉም። የብር ዋጋዉ ምን ያህል ነዉ? የኤርትራዉ ናቅፋስ ምን ያህል ዋጋ አለዉ? የሚለዉ ጥያቄ መቋጫ አልተሰጠዉም። የኤርትራ መንግሥት ግን ስለድንበር መዘጋትም ሆነ በአጠቃላይ ምንም በግልፅ የሚናገረዉ ጉዳይ የለም። ግልፅነት ይጎድለዋል።»
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸዉ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የማውቀው ነገር የለም ሲሉ የተናገሩት ሚሻኤላ ሮንግ፤ አዲስ አበባ የሚገኘው መንግሥት በአሁኑ ወቅት ስለ ኤርትራ የሚያነሳበት ጊዜ ሳይሆን በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩትን ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት ቅድምያ ለሀገር ውስጥ ጉዳይ መስጠቱ ግልፅ ነዉ።
«በርግጥ ስለሁለቱ ሃገራት ወቅታዊ ግንኙነት ምንም የማዉቀዉ ነገር የለም። እንደሚመስለኝ ግን አዲስ አበባ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን የሚያሳስበዉ አይመስለኝም በአማራ ክልል ተደረገ ስለተባለዉ መፈንቅለ መንግሥት ጉዳይና ስለተገደሉት የባለስልጣን ሁኔታ ነዉ። ሃገሪቱን በማረጋጋት ፤ በዉስጥ ፖለቲካዊ ጉዳይ ስለተጠመደ በወቅቱ የኤርትራ ጉዳይ እጅግም አሳሳቢ አይመስለኝም። ቢያንስ አሁን ስለኤርትራ የሚያነሳበት ጊዜ አይደለም ብዬ አስባለሁ» ይላሉ ሴትዮዋ፡፡
ሮንግ ኤርትራን በተመለከተ በውትድርና የሰለጠኑ ወጣቶች ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ ይኖርባቸዋል ያሉ ሲሆን ሁለቱ አጎራባች ሃገራት ደግሞ የድንበር ኮሚሽኑ የወሰነዉን የድንበር መስመር ማካለል ጉዳይ መፍትሔ መስጠት አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ፡፡
በመጨረሻም
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያዉ የመጀመሪያ ጉብኝታቸዉን ሲያደርጉ ባሰሙት ንግግር «ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት ሕዝቦች ናቸዉ ብሎ የሚያስብ ሃቁን የማያዉቅ ነዉ፤ እኛ አንድ ነን» ማለታቸው አይዘነጋም።
ይህ ንግግራቸው እርግጥ ከውስጣቸው የፈለቀ ነው ወይስ ለፖለቲካዊ ፍጆታ የተናገሩት ብሎ መመርመር ደግ ነው፡፡ በእርግጥ እውነቱን የሚያውቁት እሳቸው ብቻ ናቸው፡፡ ግን ከአንጀትም ተናገሩት ከአንገት የሁለቱን ሀገራት ዘላቂ ግንኙነት በህግና በስርዓት መስመር ማስያዝ አስፈላጊ ነው፡፡ ያ ካልሆነ ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ መንከባለል እጣፋንታቸው ሆኖ ይቀጥላል፡፡ መንግስት መጥቶ ሲሄድ፣ ዘመን አልፎ ሌላ ዘመን ሲተካ ሁሉም ነገር እንደአዲስ እየተጀመረ የሚፈርስ ይሆናል፡፡
ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ፖለቲካ
