እናት ባንክ ሴቶች በቀላሉ ሥራ እንዲያገኙና የፋይናንስ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ሥምምነት ተፈራረመ

እናት ባንክ ሴቶች በቀላሉ ሥራ እንዲያገኙናገቢያቸው እንዲጨምር የፋይናንስ ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ሥምምነት ከሜርሲ ኮርፕስ እና ኤዚቲ የመረጃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግል/ማህበር ጋር በዛሬው ዕለት ተፈራርሟል።

ሥምምነቱ ኤዚቲ የመረጃ አገልግሎት ኃ/የተ/የግል/ማ የሥራ ገበያ ክፍተት ለመሙላት ታስክሞቢ የሚባል ቴክኖሎጂን በመፍጠር የቤት ለቤት አገልግሎት ሰጭዎች እና ከአገልግሎቱ ፈላጊዎች ጋር ያለ ድካም የሚያገነኙበት የሞባይል መተግበሪያ መጠቀም የሚያስችል ሲሆን፤ ይህንም መተግበሪያ የሠራተኞችን የዋስትና እጦት ችግር መቀርፍ እንዲያስችል ሆኖ ተሰራ መሆኑ ተነግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ሥምምነቱ በአገር ውስጥ የሥራ እድል በመፍጠር ወደ አረብ አገር ሄዶ የመስራትን አመለካከት ለመቀየር እንደሚያስችል ተገልጿል።

እንደሚታወቀው በአገራችን በየዓመቱ በርካታ ወጣቶች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አስፈላጊውን የእውቀትና የክህሎች ሥልጠና ወስደው፤ በተለያየ የሙያ ደረጃዎች ሠልጥነው ቢመረቁም ሥራ ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይም ሴቶች የዚህ ችግር ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ናቸው፡፡

እናት ባንክም ይህንን ችግር ለመቅረፍና ለተለያዩ የሥራ ቅጥሮች ዋስ በማጣት ምክንያት ሥራ ሊያጡ የሚችሉ ሴቶችን ለመደገፍ ይህን ሥምምነት መፈፀሙን፤ የእናት ባንክ የኮርፖሬት ሰርቪስ ምክትል ዳይሬክተር ገነት ሀጎስ  ገልፀዋል።

“በርካታ እህቶቻችን የሥራ ዕድሉ ተመቻችቶላቸው ነገር ግን ዋስ/ተያዥ ባለማኘታችው ብቻ የዕድሉ ተጠቃሚ ሳይሆኑ ይቀራሉ ያሉት ገነት፤ ይህንንም ችግር ለመፍታት እንዲያስችል በእያንዳንዳቸው ሥም በዝግ የባንክ አካውንት የ3 ሺህ ብር እንዲቀመጥ የሚያደርግ መሆኑም ተናግረዋል።

በዚህም በመጀመርያ ዙር 300 ሴቶች ዘላቂ ገቢ እንዲፈጥሩ የሚያስችል የፋይናንሺያል ዋስትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን የገለፁት ምክትል ዳይሬክተሯ፤ የዚህም የዋስትና አገልግሎት ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን በሚሰጡበት ጊዜ ከጥንቃቄ ጉድለት በደንበኛው ንብረት ወይም እቃ ላይ የመሰበር ወይም የእምነት ማጉድል ችግሮች ቢፈጥሩ የህግ አካሄድን ተክትሎ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኤዚቲ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ምሥጋናው ዓለሙ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው አገልግሎት ሰጪዎችን የመመልመል፣ የማሰልጠን እና ሥራ የማሰማራት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ፣ እንዲሁም ከአገልግሎት ተጠቃሚዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን እንደሚያስተናግድ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ከአገልግሎት ሰጨዎችም ሆነ ቀጣሪዎች ጥያቄዎች ሲቀርቡ በእናት ባንክና የኤዚቲ የመረጃ አገልግሎት ተወካዮች በተገኙበት ህጋዊ በሆነ መንገድ የሚያስተናገድበትን መንገድ እንደሚያመቻችም ምሥጋናው ጨምረው ተናግረዋል።

Taskmoby የተሰኘው የሞባይል መተግበሪያ ኹለት አይነት ሥራዎችን እንደሚሰራ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህም ለአገልግሎት ሰጢው እና ለአገልግሎት ተጠቃሚው የሚያገለግል ነው። በዚህም ኹለቱም አካላት አስፈላጊ መረጃዎችን በመተግበሪያው እንዲያሟሉ የሚያስገድድ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት ሠራተኛው እና አሰሪው የሚገናኙበትን ምቹ መንገድ ይፈጥራል ተብሏል።

ከሞባይል መተግበሪያው በተጨማሪም በ8191 የኤስ ኤም ኤስ የፅሁፍ መልዕክት አሰሪዎችም ሆነ ሠራተኞች መመዝገብ እንደሚችሉ የተገለፀ ሲሆን፤ ለዚህም ራሱን የቻለ የጥሪ ማዕከል መዘጋጀቱም በሥምምነት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

እናት ባንክ በ 11 ባለራዕይ ሴቶች ሀሳብ አመንጪነት በሰፊ የህዝብ መሠረት ተቋቁሞ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የተሟላ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ባንክ ነው ፡፡ እናት ባንክ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የባንክ አገልግሎት በመስጠትና በተለይም ሴቶችን በኢኮኖሚ የማብቃት ተልዕኮ ይዞ የተቋቋመ ባንክ ሲሆን  ለተልዕኮ መሳካት በተለየ አካሄድ የሚሰራ ባንክ ነው ፡፡

 

ባንኩ ከሚለይባቸው አካሄዶች እንደ ማሳያ ለማንሳት   ፤

  • የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳካት በመምሪያ ደረጃ የተቋቋመ የሴቶች የባንክ አገልግሎት መምሪያ ያለው ፤
  • ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ብድር የሚያገኙበትን አሰራር አመቻችቷል፤
  • በተለያዩ ዘርፍ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሴት እናቶቻችንና እህቶቻችን ያበረከቱትን አስተዋፅኦ እውቅና ለመስጠት እና ለተተኪ ትውልድ አርአያ እንዲሆኑ በማሰብ በአዲስ አበባ የሚከፈቱ ቅርንጫፎቹን በእነዚሁ ሴት የሀገር ባለውለታዎች ስም በመሰየም እና
  • በተለያየ መልኩ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች የማቆያና ድጋፍ ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር ትብብር በመፍጠር በባንኩ ውስጥ የሥራ እድል እንዲያገኙ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነት በመተግባር መንቀሳቀሱ እንደ ማሳያ የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡

እናት ባንክ ከላይ የተገለፁትን የተለዩ አስራሮች ጨምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ፍላጎት በሚያሟላ ፣ የሴቶችን የፋይናንስ አካታችነት በሚያጎለብት አሰራርና  የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን ጨምሮ የተለያዩ ምቹና በርካታ  አገልግሎቶችን  በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ይህንኑ የባንክ አገልግሎት ለሁሉም ማህበረሰብ በማድረስ ረገድ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከማብዛት ጎን ለጎን ሰራቸው ከባንኩ ተልዕኮ ጋር ተዛማጅነት ካላቸው ተቋማት ጋር  በትብብር በመስራት ላይ ይገኛል ፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe