ከቀዳማዊ ሀይለስላሴ ጀርባ እነማን ነበሩ?

ከእዝራ እጅጉ /ተወዳጅ ሚድያና     ኮሚኒኬሽን

እንደ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ሳስብ አፍሪካ፣ የአፍሪካ አንድነት ባለውለታዎቿን ዘርዝራና በወጉ ሰንዳ አልያዘችም፡፡ ስለ ክዋሜ ንክሩማህ ሲነሳ ማን ረዳው? ከጀርባው ማን እገዛ ሰጠው? የተጻፈ ነገር ብዙም አናገኝም፡፡ የተሰነዱ መጽሀፎችንም በብዛት ማግኘት ይከብዳል፡፡ በሀገራችንም በተመሳሳይ የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ስም ጎልቶ ሲወጣ የሌሎች ባለውለታዎች ሚና እንደ ቀላል ይዘነጋል፡፡ ይህ ሀሳብ በውስጤ እያለ ነበር ከቀዳማዊ ሀይለስሳሴ ሀውልት ሊቆም መሆኑን የሰማሁት፡፡ በዚህ መነሻነት ከጃንሆይ ጀርባ ማን ነበር? ስል እጠይቃለሁ፡፡

እነሆ አፍሪካ አንድ ሆና ከተባበረች ግንቦት 18  ሲመጣ  56 አመት ይሞላታል፡፡  በእነዚህ  አመታት አህጉሪቱ በበርካታ ውጣ ውረዶች አልፋ ዛሬ መጭው ጊዜ ብሩህ ነው እያለች ትገኛለች፡፡ ከሰሞኑም ለአፍሪካ አንድነት የደከሙ በሚል ለግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ሀውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ይህ ደስ የሚያሰኝና በሀገር ልጅ መኩራት ምን ማለት እንደሆነ ያሳየ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የድካሟን ፍሬ በሚገባ ያየችበት አጋጣሚ ይመስለኛል፡፡

ያኔ የአፍሪካ አንድነት የተመሰረተ ሰሞን ብዙዎቹ  የአፍሪካ ሀገራት ነጻ እየወጡ ነበር፡፡ ፍጹም ነጻነት ያላገኙ ሀገራትም ነበሩበት፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ ሀሳቡ ተቀባይነት አገኘና  የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት  ነጻዎቹ  የአፍሪካ መንግስታት  ተስማሙ፡፡ ነገር ግን ማን አስተባብሮ ድርጅቱን ይመስርት? ቻርተሩንስ ማን ያሰናዳው? የድርጅቱስ መቀመጫ የት ይሁን? የሚሉት መልስ የሚፈልጉ ዋና ጥያቄዎች ነበሩ፡፡

በዚህ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ ‹‹እኔ ሀላፊነቱን እወጣለሁ›› ስትል በቀዳማዊ ሀይለስላሴ መሪነት ሀገራቱን አንድ ለማድረግ ተነሳች፡፡ አንድ ማድረግ ሲባልም የመጀመሪያውን የምስረታ ስብሰባ ለማዘጋጀት መነሳሳት ማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ‹‹አንድ እንሁን›› የሚለውን ጥያቄ እንዳነሳች ከየአካባቢው ተቃውሞው ተነሳ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ  የመሰብሰቢያ  አዳራሽ መንገድና ሆቴል  የላትም፡፡ ንጽህና የላትም፡፡  ስብሰባውን ለማድረግ ሌጎስ ፣  ናይሮቢና ካይሮ ይሻላሉ›› የሚል ሀሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ነገር ግን ቀዳማዊ ሀይለስላሴ  በነበራቸው ፖለቲካዊ ብስለት አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባኤን እንድታዘጋጅ ከውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡ ከወሰኑም በኋላ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን ሰብስበው ጉዳዩን ዘርዘር አድርገው አስረዱ፡፡‹‹…….ጊዜው እየሄደ ነው፡፡ያሉን 12 ወራቶች ብቻ ናቸው፡፡ መሪዎች ሲመጡ የሚያርፉበት ሆቴል የለም፡፡ ጎበዝ እንዴት ይህን ሃላፊነት እንወጣ?›› በማለት ጃንሆይ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በጊዜው ለዝግጅት የተሰጠው ጊዜ በጣም አጭር ነበር፡፡ ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም እንዳሉት ‹‹……. ይህን ስብሰባ የማዘጋጀቱ እድል ሊያመልጠን አይገባም፡፡ ገንዘቡ ከተፈቀደልኝ  በተባለው ጊዜ  ውስጥ እንዲያውም ከዛ ቀደም ብዬ በ10ወር ውስጥ የአውሮፕላን  ማረፊያ ስራውን አስረክባለሁ፡፡ ›› በማለት ቃል ገቡ፡፡ ቁርጠኛ አመራር ማለት እንዲህ ነው፡፡

ንጉሱም ልኡል ራስ መንገሻ የተግባር ሰው መሆናቸውን ስለሚያውቁ መንገሻ አደርገዋለሁ ካለ ያደርገዋል በማለት በሀሳባቸው ተስማሙ፡፡ ወዲያውም የቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ፣ የአፍሪካ አዳራሽና የግዬን ሆቴል ተሰርተው ስላለቁ በጊዜው ጉድ ተባለ፡፡ በንጉሱ ዙሪያ የነበሩት  በሳል ዲፕሎማቶችም ጥልቅ እውቀት የነበራቸው ነበሩ፡፡ ካቢኔው በዛን ወቅት ይመራ የነበረው  በአክሊሉ ሀብተወልድ ነበር፡፡ በዛን ወቅት ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ ክቡር ዶክተር ተስፋዬ ገብረእግዚ  የማስታወቂያ ሚኒስትር ፣ክቡር ዶክተር ምናሴ ሀይሌ እና ክቡር አቶ ሰይፉ ማህተመ ስላሴ የተባሉ ሚኒስትሮች ወደተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እየሄዱ ፣ ሲያስተባብሩና  ሲያግባቡ ነበር፡፡በዛን ወቅት ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው የግብጹ መሪ ገማል አብድል ናስር ነበሩ፡፡እርሳቸውን ለማግባባት ትልቅ የዲፕሎማሲ ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ የማግባባት ስራ  በወጉ ተከናውኖ ስብሰባው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ  ሲወሰን ለእንግዶቹ አዳራሽና ሆቴል አልነበረም፡፡በወቅቱ አዲስ አበባ አስፈላጊ የሚባሉትን  ጉዳዮች ካላሟላች የመቀመጫነቱ እድል ለሌላ ይተላለፍ ይሆን? የሚል ስጋትም ነበር፡፡

መቼም ከቀዳማዊ ሀይለስላሴ ሀውልት እንዲቆምላቸው መደረጉ በጎ ነገር ሁኖ ከእርሳቸው ስር የነበሩ ሰዎችን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም፡፡ ለዋቢነት አቶ ከተማ ይፍሩን ብንጠቅስ የበርካታ  የአፍሪካ መሪዎችን እንዲሁም የነጻነት ታጋዮችን በማሳመን ለስብሰባ አዲስ አበባ እንዲመጡ አድርገዋል፡፡ መሪዎቹ ከመጡ በኋላም በቂ የሚባለውን የዲፕሎማሲ ስራ ያከናወኑ ናቸው አቶ ከተማ፡፡

በ1955 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተ ሰሞን  ግዬን ፣ኢትዮጵያ፣ ራስ ሆቴል፣ ጣይቱ ፤ ገነት እና  ሂልተን ሆቴሎች ነበሩ፡፡  መሪዎች ሲመጡ የት ይረፉ? ሲባል  በግዮን ሆቴል 32 መሪዎችን የሚያስተናግድ 2 ቅጥያ ፎቅ የተሰራው በዛን ጊዜ ነበር፡፡ ከተማውን የማሳመሩ ዝግጅት በሚገባ ከተጠናቀቀ በኋላ መሪዎቹ የሚመጡበት ቀን ግንቦት 1955 እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ይህን መሰናዶ በመምራቱ በኩል ትልቁን ሃላፊነት የወሰዱት አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ፡፡ በዛን ወቅት መሪዎቹ ሲመጡ ሀይለኛ ዝናብ በአዲስ አበባ ይዘንብ ስለነበር ጃንሆይ መሪዎቹን በጃንጥላ ነበር የተቀበሏቸው፡፡ ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎም  ፖሊስ ባንድ ማርሽ  እያሰማ ለመሪዎቹ ክብር 21 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ፡፡

መሪዎቹና የልኡካን ቡድኑ አባላት አዲስ አበባ መግባት የጀመሩት ከግንቦት 13 በኋላ ሲሆን  ሁሉም ተጠቃልለው የገቡት ደግሞ ግንቦት 15 ነበር፡፡ ግንቦት 16 ምሽት ጃንሆይ በታላቁ ቤተ-መንግስት  ለዲፕሎማቶች፣ለጋዜጠኞች ፣ለሌሎችም ታላቅ የራት ግብዣ አደረጉ፡፡

ተጋባዦቹ ወደ አዳራሾቹ ከመግባታቸው በፊት ቤተ- መንግስት ሜዳ ላይ ርችቶች ተተኩሰዋል፡፡ አዳራሹ በተለያዩ ታሪካዊ ስእሎች አሸበረቀ፡፡ ማሪያ ማኬባም  በዚህ እለት የዶክተር ጥላሁንን ዜማ ስታዜም  ጭብጨባው ቀለጠ፡፡

ኢትዮዽያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ብቻዋን በአፍሪካ አህጉር ካሉ ሀገራት  ከአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት  ቀንበር ውጪ ሆና ቆይታለች፡፡ በቅኝ ግዛት ሥርም የነበሩ ህዝቦች ከታገሉ በኃላ ነጻነት ማግኘት ጀመሩ፡፡

ነጻነቱ ከተገኘ በኃላም አፍሪካ አንድ ሆና የተባበረ ክንዷን የምታሳይበት ቀን ተቃረበ፡፡  የአፍሪካ  አንድ መሆን ትልቁ ጥቅም ለራሷ ለአፍሪካ ነበርና አህጉሪቱን አንድ ለማድረግ ንቅናቄው በስፋት ተጠናክሮ ቀጥሎ ግንቦት 18 1955 የአፍሪካ አንድነት ቻርተር ሊፈረም  ቻለ፡፡

ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዋና ተሰሚነት የነበራቸው መሪ ነበሩና አፍሪካን አንድ ለማድረግ ንቅናቄው እንዲጀመር ኃላፊነት በመስጠት የጀመሩ ጉዞ ከብዙ ጥረት በኋላ ሊሳካ ችሏል፡፡ ይህን ሃላፊነት የወሰዱት  የወቅቱ የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ፡፡  ያኔ ገና የ36 ዓመት ወጣት የነበሩት አቶ ከተማ አፍሪካ አንድ ልትሆን ሰሞን ቢቢሲ ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ድርጅቱን ለመመስረት በዝርዝር የታለፈበትን ሂደት ተናግረዋል፡፡

ቻርተሩ በተፈረመ ዕለት ብዙ ኢትዮዽያውያን በተለይ ለዚህ ድል የተጉ በደስታ መፈንደቅ ያዙ፡፡ አቶ ከተማ ይፍሩን ጨምሮ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ይሰሩ የነበሩ ወጣት ኢትዮዽያውያን ሳይቀሩ የዚህ ታሪክ ተሳታፊ መሆናቸው ትልቅ ደስታ አመጣላቸው፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ አቶ ከተማ ይፍሩንና ሌሎችንም አሰማርተው የአፍሪካ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ሲያደርጉ በባለሙያዎቻቸው  በጣም ይተማመኑ ነበር፡፡ ውጭ ሀገር ተምረው የመጡት የጊዜው የሀገራችን ወጣት ምሁራን ይህን ታሪክ ለማስፈጸም ብቃታቸውንም አሳይተው ነበር፡፡ ዛሬ ለቀዳማዊ ሀይለስላሴ  ሀውልት ሲሰራ ከስር የነበሩ ሰዎችም ስራቸው በጉልህ እየተነገ ሊወጣ ይገባል፡፡ ለዋቢነት የህግ ባለሙያው አቶ ተሾመ ገብረማሪያምን ብንጠቅስ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር እንዲረቀቅ የህግ እውቀታቸውን አዋጥተዋል፡፡ እንዲያውም 32ቱ መሪዎች የፊርማ ስነ-ስርአቱን ሲያካሂዱ አቶ ተሾመ በጉልህ ይታዩ ነበር፡፡ አቶ ተሾመ በህይወት ሳሉ አነጋግሬአቸው ስለነበር ብዙ ትዝታ እንዳላቸው አውርተውኛል፡፡ በተለይ ከህግ ማርቀቅ  ጋር በተገናኘ ሙያዊ የሆኑ ጉዳዮች ተፍታተው እንዲቀርቡ አቶ ተሾመ የተቻላቸውን ማድረጋቸው አልቀረም፡፡

እንደ ዶክተር ተስፋዮ ገብረእግዚ ፤ አቶ ክፍሌ ወዳጆ ፤ ወይዘሮ ሂሩት በፍቃዱ እንዲሁም እንደ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ያሉ ሰዎች አፍሪካ  አንድ የሆነች ሰሞን እንቅልፍ አጥተው የደከሙ ናቸው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ መሪዎቿን ስታመሰግን ከመሪዎቹ ጀርባ ቆመው ቀን ከሌት የለፉትንም ሰዎች ማሰብና ታሪካቸውንም ማሰባሰብ አለባት፡፡ አፍሪካም ሆነ ኢትዮጵያ ሊቆሙ የሚችሉት ሁሉንም አሰባስበው በጋራ ከተረደዱ ብቻ ነው፡፡ ከዛሬ 55 አመት በፊትም ኢትዮጵያውያን ተጋግዘው  ለአፍሪካ እዚህ መድረስ አንዳች ሚና ማበርከታቸው በጉልህ መጻፍ አለበት፡፡

ማስታወሻ : የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እዝራ እጅጉ ሙላት  ለ19 አመት በጋዜጠኝነት ያገለገለ ሲሆን የ 13 ሰዎችን ግለ- ታሪክ በዲቪዲና በኦድዮ ሲቲ ያሳተመ ነው፡፡ በዚህ 3 ወር ውስጥ ተጨማሪ 5 ታሪኮችን በዲቪዲና በኦድዮ ሲዲ እንደሚያሳትም ይጠበቃል፡፡ እዝራ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን የተሰኘ የራሱን ድርጅት የመሰረተ ነው፡፡   

                                      Gmail .tewedajemedia@gmail.com

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe