ከተማ ይፍሩ፡ ያልተነገረላቸው የአፍሪካ አንድነት ባለ ራዕይ

በፊውዳሉ ስርዓት ሹመት በደም ትስስር፤ በዘርና አጥንት ተቆጥሮ በሚሰጥበት ወቅት ስሟ ብዙ ከማትታወቀው የሐረርጌ ግዛቷ ጋራ ሙለታ ከደሃ ገበሬዎች ቤተሰብ የተገኘውና በ30ዎቹ ዕድሜ የነበረው ወጣት ከተማ ይፍሩ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ግንኙት አድራጊ፣ ፈጣሪ እንዲሁም የአፄ ኃይለሥላሴ ዋና ልዩ አማካሪ (ቺፍ ኦፍ ስታፍ) ይሆናል ብሎ ያለመ አልነበረም።

ነገር ግን የማይታሰበው እውን ሆኖ ከተማ ከዚህም አልፎ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ አሻራውን መጣል ችሏል።

የታሪክ መዛግብትም ሆነ በቅርብ የሚያውቋቸው ተራማጅ ብለው የሚጠሯቸው ከተማ ኢትዮጵያ ቅኝ ባለመገዛቷ ከአህጉሩ የተለየችና ኢትዮጵያውያንም ልዩ ነን የሚል እሳቤ በአብዛኛው ዘንድ ቢንሸራሸርም ለሳቸው ግን የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ከሌሎች አፍሪካውያን የተለየ አይደለም ፤ መተባበር ካለባትም ከአፍሪካውያን ጋር ነው የሚል ቁርጠኛ አቋም ነበራቸው።

ገና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ ሊግ ኦፍ ኔሽን ኢትዮጵያን አንቅሮ የተፋበት ሁኔታ ቁጭት እንደፈጠረባቸው በአሁኑ ሰዓት የህይወት ታሪካቸውን እየፃፈ ያለው ልጃቸው መኮንን ከተማ ይናገራል።

የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ በጣልያን ስትወረር አባል የሆነችበት የሊግ ኦፍ ኔሽን ይተባበረኛል የሚል እምነት ነበራት ። ነገር ግን ያልተጠበቀው ሆኖ አፄ ኃይለሥላሴ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት በመዘባበት፣ በጩኸትና በፉጨት ንግግራቸው ተቋረጠ።

ይህም ሁኔታ ታዳጊው ከተማን ከማስከፋት አልፎ ለተጨቆኑ ህዝቦች እንዲቆም ፤ ለፍትህና ለእኩልነት እንዲታገል መሰረት እንደሆነው የቅርብ ጓደኞቻቸው ምስክር ናቸው።

በአንድ ወቅት የቀድሞው የጣልያንና ጂቡቲ አምባሳደር ዶ/ር ፍትጉ ታደሰ ስለ ከተማ ተጠይቀው ሲመልሱ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካውያን ሁኔታ ስለሚያሳስባቸውም “እኛ ነፃነት አግኝተን፤ እነርሱ በባርነት ቀንበር እንዴት ይሰቃያሉ” የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው ብለዋል።

ለዚያም ነበር ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር በነበራት ትግል የረዳቻት እንግሊዝን እንኳ ለመተቸት ቅንጣት ወደ ኋላ ያላሉት። እንግሊዝ በአፓርታይድ ጭቆና ስር ለነበረችው ደቡብ አፍሪካ የጦር መሳሪያ መሸጧንም በከፍተኛ ሁኔታ ተችተዋል።

ከመተቸት ባለፈም ነፃ ያልወጡ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ እንዲወጡ ከፍተኛ ርብርብና ለነፃ አውጭዎቿም ድጋፍ አድርገዋል። ከዚህም ውስጥ የሚጠቀሰው ለማንዴላ በኢትዮጵያ ፓስፖርት እንዲዘዋወሩ ማድረጋቸው ነው።

ማንዴላ በአፓርታይድ መንግሥት በቁጥጥር ስር ሲውሉ የከተማ ፎቶ በኪሳቸው ውስጥ እንደተገኘ የከተማ ልጅ መኮንን ይናገራል።

ፎቶው ላይ ለነፃነት ታጋዩ የሚል ፅሁፍ የነበረበት ሲሆን ፎቶው በማንዴላ እስር ወቅት እንደ ማስረጃ ሰነድ ቀርቦ እንደነበር በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ቪትዝ ዩኒቨርስቲ ሙዝየም ማስረጃ ተቀምጧል::

ከተማና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ

1950ዎቹ ለአፍሪካውያን የተለየ ተስፋ ይዞ የመጣ ጊዜ ነበር። የነበሩበት የቅኝ ግዛት፣ ጭቆና፣ ባርነትን በመሰባበር ነፃነት የተፈነጠቀበት ጊዜ ነበር።

በዛን ጊዜም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚህ ቀደም ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወጣቱ ፓን አፍሪካኒስት ከተማ የአፍሪካ አህጉራዊ ድርጅት መፈጠር አለበት የሚል ንግግር ተናገሩ።

ነፃ በወጡት አፍሪካ ሀገራት መካከል የአህጉሯ ህብረት ቢፈለግም ድርጅትን ሳይሆን ሀገራቱ ተዋህደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል የሚል እሳቤዎች የጎሉበት ጊዜ ነበር።

በአንድ ወገን ዋናና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሀገራቱ በፍጥነት ተዋህደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል የሚለው የካዛብላንካ ቡድን፤እንዲሁም አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል የሚለው የሞኖሮቪያ ቡድኖች ነበሩ።

ኢትዮጵያም በወቅቱ የሞኖሮቪያን ቡድን ተቀላቅላ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተማ ኢትዮጵያ ሁለቱን አንጃዎች የማስማማት ስራ መስራት እንዳለባት ለንጉሱ አጥብቆ ተናገሩ።

ምንም እንኳን በወቅቱ ወግ አጥባቂ የነበሩት ሹማምንቱና መኳንንቱ “እንምከርበት” የሚል ኃሳብ ቢያነሱም አፄ ኃይለሥላሴ ግን “ታምንበታለህ” የሚል ጥያቄ ብቻ እንዳቀረቡላቸውና ሂደቱን ብቻ እንዲያሳውቃቸው እንደነገራቸው መኮንን ይናገራል።

ሁለቱም ቡድኖች ስብሰባቸው ላይ እንዲገኙ ጥሪ ሲያቀርቡ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ በማሰብ አጀንዳቸውን ይዘው ሄዱ።

የሚኒስትሩ ዋነኛ አጀንዳ የነበረው ከ20 በላይ አባላት የነበሩትን የሞኖሮቪያን ቡድንና ስድስት ብቻ አባላት የነበሩትን የካዛብላንካን አንጃ አሳምኖ አዲስ አበባ ጉባኤ ማካሄድ ነበር።

ኢትዮጵያ ሁለቱን ቡድኖች አንድ ላይ ለማምጣት የመሪነት ቦታውን በመያዝ የሞኖሮቪያን ቡድን ስብሰባ ለመሳተፍ አቶ ከተማ ወደ ሌጎስ አመሩ።

አመራሮቹን አዲስ አበባ በሚካሄደው ጉባኤ እንዲመጡ ፤ በኋላም ንጉሱንም አሳምነው ለመሪዎቹ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያደረጉ ሲሆን ንጉሱም ” እኛ ከሞኖሮቪያም ሆነ ከካዛብላንካ አይደለንም። ከአፍሪካ ጋር ነን የሚል” ታሪካዊ ንግግራቸውን አደረጉ።

በተለይም በወቅቱ የሀሳቡ አመንጪና ከረር ያለ አቋም የነበራቸውን የ ጋናውን መሪ የነንክሩማህን ቡድን ማምጣት ቀላል እንዳልነበር ከተማ ይናገሩ እንደነበር መኮንን ይገልፃል ።

በተለይም ጉዳዩን አወዛጋቢ ያደረገው በወቅቱ የሞኖሮቪያ አባል የነበሩት የቶጎው መሪ መገደል ያኛውን ቡድን መወንጀልና ሁኔታዎችም መካረር ጀመረ። ነገሮችንም ለማለሳለስ ብዙ ጥረት ተደረገ።

ከዚህም ውስጥ ሌላኛውን የካዛብላንካ ቡድን አባል የነበሩትንም የጊኒውን መሪ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬንም ወደ አስመራ በመጋበዝ ከንጉሱ ጋር እንዲነጋገሩ ተደረገ። ኢትዮጵያና ጊኒ በመከፋፈል አያምኑም የሚል መግለጫም በጋራ አወጡ።

መሪዎቹን አስማምቶ ማምጣት በጣም የከበደ ስራ እንደነበር የሚናገረው መኮንን በብዙ አጋጣሚዎችም አባቱ ከተማ የዲፕሎማሲ ክህሎታቸውን በመጠቀም ነገሮችን እንዳሳኩ ይናገራል።

ከተማ በየሃገራቱ ሲዞሩ “ሀገር አልለቅም፤ ንጉሱ አያስገቡኝም” የሚሉ ማባበያዎችን ይጠቀሙ እንደነበር የሚናገረው መኮንን ከተማ የቱኒዝያውን ፕሬዚዳንት ያግባቡበትን መንገድ ለይቶ ይጠቅሳል። ፕሬዚዳንቱ የሁለቱ ቡድኖች የጋራ አቋም ሳይኖር እንዴት አንድ ላይ እንሰበሰባለን የሚል የእምቢታ ምላሽ ሲሰጧቸው በምላሹም “አፄ ኃይለሥላሴ ያለርሰዎ ይህ ስብሰባ አይካሄድም” እንዳሏቸው መኮንን ይናገራል።

በወቅቱ አፄ ኃይለሥላሴ የነበራቸው ቦታ ከፍተኛ ስለነበርም የቱኒዚያው ፕሬዝዳንት እሺ ብለው መጡ። ያ ታሪካዊ ስብሰባ ሊደረግም በቃ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ተበሰረ።

ነገር ግን ሁሉ ቀላል አልነበረም። ሁለት የተለያዩ እሳቤዎችን ይዘው የመጡ ቡድኖችን አንድ ላይ መምጣት ቀላል አልነበረም፤ የተወሰኑ ግጭቶች ቢፈጠሩም የነበረው የስሜት ድባብ በጣም የተለየ እንደነበር አቶ ከተማ ለልጃቸው ለመኮንን ነግረውታል።

“እንዲህ አይነት ስሜት አፍሪካ ውስጥ ተፈጥሮ አያውቅም” ብለው አባቱ አጋጣሚውን ገልፀውለታል።

አዲስ አበባን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፅህፈት ቤት የማድረግ ትግል

በመቀጠልም የአፍሪካ ፖሊሲዎችን ማርቀቅ፣ የድርጅቱ ፀሐፊ እንዲሁም ዋና ፅህፈት ቤት የት ይሁኑ የሚሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ነበሩ።

በከተማ አመራርነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለቱን አንጃዎች ፖሊሲና ሌሎች ሀሳቦችን ጨምረው አቀረቡ፤ ፖሊሲዎቹ ላይ አንዳንድ አለመስማማቶች ቢፈጠሩም ሰነዱ ተፈረመ።

ከተማ ስራቸው አላለቀም ለኢትዮጵያ የነበረው ጥሩ ስሜት እያለ ኢትዮጵያ የድርጅቱ ፅህፈት ቤት መቀመጫ ትሁን የሚል ሀሳብ አቀረቡ። በፍጥነት ከአመራሩ “አይቻልም” የሚል ምላሽ ተሰጣቸው። ምክንያቱ ደግሞ “ከተማ የራሱን ስም ለማበልፀግ” እየሰራ ነው ብለው ንጉሱን የሚመክሩ ስለነበሩ እንደሆነ መኮንን ይናገራል።

የተፈራው አልቀረም ትንሽ ቆይቶም ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገራት የድርጅቱ መቀመጫ ዳካር እንድትሆን መስማማታቸው ተሰማ። ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመመስረት ይህንን ያህል ለፍታ አመድ አፋሽ መሆኗ ንጉሱን አስደነገጣቸው።

ከሴኔጋል ሌላም ናይጀሪያ ያላትን ትልቅነት ተጠቅማ እዚህ መሆን አለበት የሚል ክርክርም ጀምራ ነበር። የሃገራቱ እሰጣገባ ብቻ ሳይሆን “ኢትዮጵያን አትምረጡ” የሚል ቴሌግራም እንደተሰራጨም እንደነበር የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለከተማ አሳዩዋቸው።

“ኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ግጭት እያለ ሚኒስትሩ ያንን ማድረጋቸው ለአባቴ በህይወቱ ሙሉ የሚያስደንቀው ጉዳይ ነበር። ቢጋጩም የሶማሊያ ድጋፏ ለኢትዮጵያ ነበር” ይላል መኮንን

በመቀጠልም ኢትዮጵያ እንድትመረጥ የማግባባቱ ስራ/ ዘመቻ/ ተጀመረ። በተለይም ለጊኒ እናንተ ኢትዮጵያን መቀመጫ ካደረጋችሁ የፀሀፊውን ቦታ እንሰጣችኋለን የሚል ሃሳብን እንዳቀረበ መኮንን ይናገራል።

በመጨረሻም ከናይጀሪያ በስተቀር ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ፅህፈት ቤት መቀመጫ እንድትሆን አገራቱ ድምፃቸውን ሰጡ።

“ብዙዎች እንደሚሉት አፄ ኃይለሥላሴ ስለነበሩ አዲስ አበባ ተመረጠች የሚለው ሳይሆን ከብዙ ማግባባት፣ ክርክርና ፍጭቶች በኋላ ነው የድርጅቱ ፅህፈት ቤት አዲስ አበባ ሊሆን የቻለችው።” በማለት መኮንን ያስረዳል።

ከጋራ ሙለታ ቦስተን ዩኒቨርስቲ

ለዘመናት በተለያዩ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያን የወከሉት አቶ ከተማ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በተለያዩ ኃላፊነት አገልግለዋል።

የትምህርት ጉዟቸው ሀ ብሎ የተጀመረው ኬንያ ነበር። ምክንያቱም ጣልያን ኢትዮጵያን ሲቆጣጣር በሰባት አመታቸው ወደ ጂቡቲ ለመሰደድ ተገደዱ።

ትንሽ ጊዜ ጅቡቲ ቆይተውም ጉዟቸውን ከአጎታቸው ጋር ወደ ኬንያ አደረጉ። በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችው ኬንያም ስደተኞች ከአገሬው ተማሪ ጋር አብሮ መማር ስለማይቻል ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተብሎ በተከፈተውና በቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ህይወት ኃላፊነት በሚመራው ትምህርት ቤት ጀመሩ።

ኢትዮጵያ ነፃነቷን ስትቀዳጅ ደግሞ ወደ ጋራ ሙለታ ተመለሱ። ያኔም ትምህርታቸውን የመቀጠል ፅኑ ፍላጎት እንደነበራቸው መኮንን ይናገራል። ለዚህ ደግሞ የአጋጣሚ በር ተከፈተላቸው።

ንጉሱ የተለያዩ አካባቢዎችን በሚጎበኙበት ወቅት ጋራ ሙለታን ሲጎበኙ በአካባቤው ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች አሉ ምን ይደረግ? ብለው ሲጠየቁ አዲስ አበባ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምጣት እንደሚችሉ ምላሽ ተሰጣቸው።

መኮንን እንደሚናገረው አዲስ አበባ ሄደው ወዲያው ትምህርት ቤት የሚገቡ መስሏቸው የነበረ ቢሆንም ሲደርሱ አናስገባም የሚል ምላሽ ተሰጣቸው። የሚያድሩበትም ሆነ የሚበሉት አልነበራቸውም፤ በጊዜው “ሰው ለሰው አዛኝ በመሆኑ” ይላል በአካባቢው የነበሩ ወታደሮች መጠጊያ ሆኗቸው። ስራም እየሰሩ ትንሽ ከቆዩ በኋላ ነገሩ በወቅቱ የጦር ሰራዊት ኃላፊ ለነበሩት ጄኔራል መርዕድ መንገሻ በመነገሩ በሳቸው ምክንያት ትምህርታቸውን ሊጀምር እንደቻሉ ይናገራል።

የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የመኳንንትና የሹማምንት ልጆች በመሆናቸው ከፍተኛ ልዩነት ይታይበት የነበረ ሲሆን አባቱ የነገሩትንም መኮንን እንዲህ ያስታውሰዋል።

“ንጉሱ በየጊዜው እየመጡ ተማሪዎቹን ይጎበኛሉ። መምህሩም ስም በሚጠራበት ወቅት ከስማቸው ፊት ደጃዝማች፣ ልዑል እንዲሁም ሌሎች ሹመቶች ነበሩ። ጃንሆይም ልጆቹ በእኩልነትና ያለምንም ተፅእኖ ትምህርታቸውን እንዲማሩ ቅጥያው እንዲሰረዝ አዘዙ” ይላል።

በመቀጠልም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ሚቺጋን ሆፕ ኮሌጅ ፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ለማጥናት ያቀኑ ሲሆን፤ የማስተርስ ዲግሪያቸውንም በቦስተን ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ ትምህርት ተመርቀዋል።

አሜሪካ ሲደርሱ ከፍተኛ ዘረኝነት ያጋጠማቸው ሲሆን፤ “ውሾችና ጥቁሮች አይፈቀድም” የሚሉ መልእክቶች እንዲሁም የነበረው የዘረኝነት ሁኔታ አፍሪካዊነታቸውን ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካዊነት ፅንሰ ሀሳባቸውንም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደገው ነገር እንደሆነ መኮንን ይናገራል።

ምንም እንኳን የፒኤችዲ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ቢጠየቁም ቤተሰቤን እረዳለሁ ብለው ተመለሱ። ትልቅ ህልም የነበራቸው አቶ ከተማ በውጭ ጉዳይ በተለያዩ ዘርፎች በኃላፊነት ቢያገለግሉም ከደሃ ቤተሰብ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ ሹመቶች ያመለጧቸው ነበር።

የሹማምንት ልጆች በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ሲቀመጡ እሳቸው ዝም ተባሉ። ይህንንም ጉዳይ በጊዜው ውጭ ጉዳይ ለነበሩት ለፀሀፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተወልድ አጫወቷቸው ነበር።

ሚኒስትሩም ጉዳያቸውን ለንጉሱ እንዲያቀርብ መከሯቸው። “ደፋርና በግልፅ ተናጋሪ ነበር” የሚለው መኮንን ለንጉሱ የጠየቀበትን መንገድ ይገልፃል ” እኔ ወደ ኋላ የቀረሁት በማንነቴ ነው” ብሎ በመናገሩ ንጉሱ ተቆጥተው ውጣ አሉት።

ቢሆንም የደመወዝ ጭማሪ ተደረገላቸው፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ቢሆን ደግሞ ሹመቱ ተሰጣቸው። ለሹመቱም ጄኔራል መርዕድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሲሆን ብዙ ተቃውሞም ገጥሟቸዋል። የውጭ ጉዳይ ኃላፊ መሆን ግን አልጋ ባልጋ አልሆነላቸውም።

“ይህ ሁኔታ በጣም አስደንጋጭ ነበር። ብዙዎች በመቃወም ተከራክረዋል። ምንም እንኳን ሹመቱ ጥሩ ቢሆንም። ብዙ ጠላቶችንም ማፍራት ቻለ” በማለት መኮንን ይናገራል።

ንጉሱን በድፍረት በመናገር ታሪክ የሚያስታውሳቸው ከተማ የንጉሱም ዋና ልዩ ፀሀፊም ለመሆን ችለው ነበር።

ምንም እንኳን ከአፍሪካውያን ጋር ህብረት መመስረትና ሌሎች አማራጮችን በድፍረት መናገሩ ብዙዎችን ቢያስደንቅም ለመኮንን “ንጉሱ እሱን መስማታቸውና የሚመክራቸውንም ጉዳይ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ያደንቃል” ሌላው ሰው የማይጠይቃቸውን ነገሮች ከተማ በድፍረት ይጠይቁ እንደነበርም መኮንን ይናገራል።

ለምሳሌ አባቱ ካጨወቱት መካከል አፄ ኃይለስላሴን ንጉስ ባይሆኑ ምን ይሆኑ ነበር? ብለው ጠይቀው ነበር። እርሳቸውም በምላሹ “ዶክተር” ብለው መልሰውለታል።

ተራማጁ በንጉሳዊ አገዛዝ ስርአት ውስጥ

ብዙ እሳቤዎቻቸው ከጊዜው የቀደመ ነው የሚባልላቸው ከተማ አፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሰረት ከማስያዝ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ገለልተኛ አቋም እንዲኖረው ብዙ ጥረዋል።

ከዚያም በተጨማሪ ንጉሱን ስልጣን ለልጃቸው እንዲያጋሩ፤ ህገ መንግሥታዊ የዘውዳዊ ስርዓት እንዲመሰረት የሚሉና ሌሎች ኃሳቦችን አካተው ምክር አዘል ደብዳቤም ፅፈውላቸው ነበር።

ከተማ ይፍሩ ለአፄ ኃይለሥላሴ የፃፉት ደብዳቤ

“በዚች አነስተኛ ማስታወሻ ላሳስብ የምወደው ግርማዊነትዎ ከፈለጉ የመሸጋገሪያውን ድልድይ ለመዘርጋትና የኢትዮጵያ ህዝብ ወደፊት ከሞግዚትነት ወጥቶ የራሱን እድል በራሱ ለመወሰን የሚያስችለውን ለማድረግ ስለሚችሉ ሳይውል ሳያድር አስበውበት አንድ የተፋጠነና የተወሰነ እርምጃ እንዲወስዱ ነው” ከደብዳቤው የተቀነጨበ

በድፍረት የመናገሩ ጉዳይ ገደብ እንዳለው ያልተረዱት አቶ ከተማ በተለይም በስልጣናቸው ላይ መምጣቱ በንጉሱ ዘንድ ቅሬታን አሳደረ።

ደብዳቤውን በፃፉ በማግስቱ ከውጭ ጉዳይ አውጥተው ወደ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ሚኒስትር ቀየሯቸው። አባቱ በሁኔታው ብዙ ደስተኛ እንዳልነበሩና እንደከፋቸውም መኮንን ይናገራል።

ከሶስት አመታት በኋላም ከተማ የተነበዩት አልቀረም ንጉሱ ከስልጣን ወረዱ። “ምክሩን ሰምተው ቢሆን ኖሮ ያ መጥፎ ስርአት ላይመጣ ይችል ነበር፤ ይስተካከልም ነበር” ይላል መኮንን

የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ፅንሰ ሃሳብ ከመመስረት ጀምሮ፣ የአፍሪካ ፖሊሲዎችን ማርቀቅ፣ ካዛብላንካንና ሞኖሮቪያን አስማምቶ አንድ ላይ ማምጣትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፅህፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን ማድረግ ከሚጠቀሱ ስራዎቻቸው የተወሰኑት ቢሆንም ታሪክም ሆነ ታሪክ ፀሀፊዎች ዘንግተዋቸዋል። በስማቸውም የተቀመጠ ሀውልት ወይም ሌላ ማስታወሻ የላቸውም። ለምን? መኮንን መልስ አለው

“አንድ ህዝብ ታሪኩን ሳያውቅ ሲቀር ይህ ነው የሚሆነው፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዴት ተመሰረተ የሚለውን በአንድ አረፍተ ነገር መናገር እንችላለን፤ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሁለቱን ቡድኖች አስታረቁ ማለት እንችላለን። ዝርዝሩን ግን ምን ያህል እናውቃለን፥ መንግሥት በተለወጠ ቁጥር ታሪክ የሚጀምረው በኔ ነው ይልና ያኛውን ያፈርሰዋል። የሚያውቁት ደግሞ እኔ ለሳቸው ተገዢ ነኝ የሚል አስተሳሰብ አለ። የአቶ ከተማ ይፍሩ ስም ከተነሳ ድንገት የሳቸውን ሊሸፍነው ይችላል የሚልም ነገር ይኖራል። አይሸፍንም እሳቸው መሪ ናቸው ተገቢውን ክብር ማግኘት አለባቸው። ነገር ግን ገና ለገና የሳቸውን ስም ይሸፍናል በሚል የግለሰቦች አስተዋፅኦ ሊደበቅ አይገባም። በዛ ላይ ከእንደዚህ አይነት ደሃ ቤተሰብ ከመጣ ሰው ይህንን ሁሉ ታሪክ ከሰራ በኋላ፤ ላገሩ ካበረተ በኋላ ለሌሎች ምሳሌ ይሆናል እንጂ ይሄንንማ መደበቅ አንችልም”

ያ ተስፋን የሰነቀ ድርጅት ብዙም አልቀጠለም በአባላቱ ሃገራት መፈንቅለ መንግሥቶች፣ ግድያዎች ቀጠሉ። በተለይም ከተማ በደርግ ጊዜ ከዘጠኝ አመት የእስር ቆይታ በኋላ ምሬታቸውና ኃዘናቸው ከፍተኛ እንደነበር መኮንን ይናገራል።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በተመሰረተበት በመጀመሪያዎቹ ሶስት አመታት ችግሮቻቸውን በአህጉራዊ ድርጅቱ ይፈቱ ነበር እንደ ምሳሌም የሚነሱት አልጀሪያና ሞሮኮ ሲዋጉ ኢትዮጵያ አንዷ አሸማጋይ ነበረች።

እሳቸውም በአንድ ወቅት በአሜሪካ ድምፅ ተጠይቀው እንደተናገሩት “ሀገራቱ ስልጣን የሚተካኩበት ስርዓት ማምጣት ስላልቻሉ መፈንቅለ መንግሥቶች መከታተል ጀመሩ” ብለዋል።

አፍሪካውያን በአንድነት አህጉሯ በአለም አቀፍ ደረጃ የመደራደር አቅምን እንዲሁም ተሰሚነት እንድታገኝ የተጀመረው ጉዞ ወደ ኋሊት ሆኖ ወታደሮች በተለያዩ ቦታዎች ስልጣንን መያዝ ጀመሩ። ይህም ሁኔታ በጣም ያሳዝናቸው ነበር ቢልም እሳቸው ካበረከቱት አንፃር ከአንድ ሰው ከሚጠበቀው በላይ እንዳደረጉ የሰሯቸው ስራዎች ምስክር ናቸው ይላል።

ከባለቤታቸው ራሔል ስነ ጊዮርጊስ አራት ልጆች አፍርተዋል። ከእስር ሲፈቱ የአስራ አምስት አመት ልጅ የነበረው መኮንን ደግ፣ ቀላልና የሰው ሃሳብ የሚሰሙ ሰው እንደነበሩ ይናገራል። አቶ ከተማ ራሳቸውንስ እንዴት ይገልፁ ይሆን መኮንን እንደሚለው ወጣ ያለ አስተሳሰብ (ሬብል) ነኝ ይሉ ነበር ብሏል።

Sourceቢቢሲ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe