ኩዌስት – ዕውቁ የቢዝነስ ጋዜጠኛ

ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲጓዝ በገጠመው ድንገተኛ አደጋ መከስከሱንና በውስጡ የነበሩት 149 ተሳፋሪዎችና 8 የበረራ ሠራተኞች መሞታቸውን ተከትሎ ስለ አየር መንገዱ የድጋፍ አስተያየት ከሰጡት ዝነኛ ሰዎች አንዱ ሪቻርድ ኩዌስት ነው፡፡ በአየር መንገድና በአውሮፕላኖች ዙሪያ የተለየ ዕውቀት ያለው የሲኤንኤኑ ጋዜጠኛ ስለ አየር መንገዳችን እንዲህ ነበር ያለው፡፡ ‹‹ከጥሩ በላይ የሆነ የደህንነት ታሪክ አለው፡፡ አየር መንገዱ በመሪነት ከሚታወቁ የዓለማችን አየር መንገዶች አንዱ ነው፡፡ የሀገሪቱ መንግሥት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቁልፉን ሚና ከሚጫወቱት ዘርፎች መካከል (አየር መንገዱ) አንዱ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በሌሎች አየር መንገዶች የደህንነት ሥጋት ሲኖርብሽ የኢትዮጵያን አየር መንገድ እጠቀማለሁ ብለሽ የምትመርጪው ነው››

. . . እኛም በጎ አስተያየቱን መነሻ አድርገን የሰውየውን ማንነትና ስኬታማ የሥራ ሕይወት መቃኘት ወደናል፡፡ እነሆ!

ማን ነው? 

እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ሪቻርድ ኩዌስት በአሜሪካው ሲኤንኤን ኢንተርናሽናል ቴሌቪዥን ላይ በዘጋቢነትና በዜና አቅራቢነት የሚሠራ ዕውቅ ባለሙያ ነው፡፡ መኖሪያውን በኒውዮርክ ሲቲ ነው ያደረገው፡፡ ሪቻርድ የተወለደው እ.ኤ.አ መጋቢት 9 ቀን 1962 በእንግሊዟ ሊቨርፑል ከተማ መርሲሳይድ ተብላ በምትጠራ ስፍራ ነው፡፡ ቤተሰቦቹ አይሁዳውያን ናቸው፡፡ በሊድስ ከተማ በሚገኘው ስቴት ኮምፕሬሔንሲቭ ራውንዳይ ትምህርት ቤትና ኋርፌዳል የተባለ ኮሌጅ ውስጥ የተማረው ሪቻርድ ኩዌስት እ.ኤ.አ በ1983 ከሊድስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት ተመርቋል፡፡ በናሽቪል የሚገኘውን የቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የሬዲዮ ጣቢያ የዜና ኃላፊ ሆኖ በሚመራበት ወቅት የዜና ዘጋቢዎችን ቡድን በማደራጀት ተግባሩ ይታወቃል፡፡

1.88 ሜትር ቁመት ያለው የቢዝነስ ዘጋቢ ከ2002 ጀምሮ በቴሌቪዥን ጣቢያው ሲተላለፍ በቆየው ‹ቢዝነስ ትራቨለር› የተሰኘ ፕሮግራም ከሆቴሎች፣ ከአየር መንገዶችና በመላው ዓለም ከሚገኙ ከተሞች እያንዳንዷ የዓለማቀፍ ምጣኔ ሀብት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ የንግድ ርዕሠ ጉዳዮችን በድንቅ አቀራረብ በመተንተን ይታወቃል፡፡

በትላልቅ የንግድ ጉዳዮች ላይ ሙያዊ ትንታኔ የሚሰጥበት ‹ኩዌስት ሚንስ ቢዝነስ› የተሠኘ ፕሮግራሙም እጅግ ታዋቂ ነው፡፡ ዕውነተኛና የውሳኔ ሰው መሆኑ የሚነገርለት ኩዌስት የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያነት ጉዞውን የጀመረው እ.ኤ.አ በ1985 በብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ቢቢሲ) ሰልጣኝ ጋዜጠኛ ሆኖ በመቀጠር ነበር፡፡ በ1987 ደግሞ ትኩረቱን ወደ ገንዘብ ነክ የዘገባ ዘርፍ ካደረገ በኋላ በ1989 የተቋሙ የሰሜን አሜሪካ ወኪል ዘጋቢ ለመሆን ወደ ኒውዮርክ ከተማ ተዛወረ፡፡ በዚያም ገንዘብና ንግድ – ነክ ዘገባዎችና ትንታዎች ማቅረቡን ተያያዘው፡፡ በ2001 ሲኤንኤን ወደተባለው የዩናይትድ ስቴትስ ዓለማቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከተዘዋወረ በኋላ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጨምሮ በርካታ ዘገባዎች ሠርቷል፡፡

የአውሮፓ ሕብረት መገበያያ ገንዘብና ሳንቲሞች ሥራ ላይ ከዋሉበት የመጀመርያ ቀን ኮንኮርድ የተሠኘው የንግድ አውሮፕላን ሥራ እስካቆመበት ቀን ድረስ ያሉ ታላላቅ ዘገባዎችም ሠርቷል፡፡ በ2006 የአልጀዚራ እንግሊዘኛ የዜና ጣቢያ ሠራተኛ ሆኖ የሚቀጠርበት ዕድል የነበረው ቢሆንም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

የቢዝነስ ጋዜጠኛው

ከሲኤንኤን ታዋቂ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ኩዌስት ከዓለማቀፍ የንግድ ዘገባዎቹና ‹ኩዌስት ሚንስ ቢዝነስ› ከተሠኘ ፕሮግራሙ ባሻገር በወቅታዊ የገበያ ሁኔታዎችና ንግዶች ላይ በሚያተኩር የፕሮግራም ይዘት እንዲሁም ‹የኩዌስት አስደናቂ ዓለም› በተሠኘና አዳዲስ የጉዞ ታሪኮች በተከታታይነት በሚዳሰስበት ተወዳጅ ፕሮግራሙ ይታወቃል፡፡

ከቢዝነስ ፕሮግራሞች አዘጋጅና አቅራቢነቱ በተጨማሪ የሲኤንኤን ቢዝነስ ዘገባዎች ከፍተኛ የይዘት አርታኢ እንደመሆኑ ‹ማርኬትስ ናው› የተሠኘውን ገንዘብ ነክ ሾው የአርትኦት ሥራ ይሠራል፡፡

በተለይ ታዋቂ የሆነበት ‹ኩዌስት ሚንስ ቢዝነስ› የተሠኘ ፕሮግራሙ ጠንካራ ምጣኔ ሀብታዊ ወሬን በአዝናኝ መንገድ በማቅረብ የቢዝነስ ፕሮግራሞች አሰልቺ ናቸው የሚለውን የቆየ አስተሳሰብ ለመናድ የቻለ ነው፡፡ ከፍተኛ የንግድ ተቋማት ሥራ አስኪያጆችና የፋይናንሱ ዓለም ሚኒስትሮች በእንግድነት መቅረብ የቻሉበት ፕሮግራምም ነው፡፡ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን፣ የቼክ ሪፐብሊኩ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔትር ኔካስ፣ የዓለም ገንዘብ ፈንድ ኃላፊዋ ክርስቲን ላጋርድና ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ የንግድ ሰዎች በፕሮግራሙ ላይ ቀርበዋል፡፡

ተለዋዋጭና ልዩ የአቀራረብ ዘዬው በቢዝነስ ዘገባው ዘርፍ የተለየ ቀለም ያለው ጋዜጠኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የቡድን ሃያ ስብሰባዎችም ሆነ በየዓመቱ በስዊዘርላንዷ ዳቮስ የሚካሔደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ውይይት የዘገባው አንኳር ግብዓቶች ሲሆኑ የዓለም ንግድ ማዕከላት የሆኑት ዎል ስትሬት፣ ለንደን፣ ሳኦፖሎ፣ ቶኪዮና ሆንግ ኮንግም ለረጅም ዓመታት በዘገባው የተመላለሰባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡

ሁለገቡ ጋዜጠኛ

በሚሠራበት ሲኤንኤን ኢንተርናሽናል የቴሌቪዥን ጣቢያ ውስጥ የአየር መንገድ ዘርፍ ዘጋቢ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ በዚህም ታላላቅ የአየር መንገዶች ሥራ አስኪያጆችን በቃለ መጠይቁ አካቷል፡፡

ከዓመታት በፊት ደብዛው ጠፍቶ ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ በከፍተኛ ደረጃ ሲያነጋግር በቆየው ኤም ኤች 370 የማሌዥያ አውሮፕላን ላይ የሠራቸውን ልዩ ዘገባዎች ያካተተና ‹የበረራ ኤም ኤች 370 መጥፋት፤ የጠፋውን የማሌዥያ አውሮፕላን ፍለጋ የሚዳስስ እውነተኛ ታሪክ› (the Vanishing of Flight MH370: The True Story of the Hunt for the Missing Malaysian Plane) የሚል መጽሐፍ ጽፏል፡፡ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሠራቸውን ሥራዎች ዕውቅና በመስጠት የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት እ.ኤ.አ በ2013 የሕይወት ዘመን ስኬት ሽልማት አበርክቶለታል፡፡

ሲኤንኤን የተሠኘው ተቋሙ በብሪታኒያ የሚያዘጋጃቸውን ኹነቶች በመምራት ቀዳሚውን ሚና የሚጫወተው ሪቻርድ ኩዌስት ብሪታንያ ከአውሮፓ ሕብረት ለመውጣት እያደረገቻቸው ያሉትን እንቅስቃሴዎች በገበያና በንግድ ግንኙነቶቿ ላይ ከሚኖረው ተፅዕኖ ጋር አያይዞ ተከታታይ ዘገባዎች በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የብሪታንያ ንጉሣዊ ቤተሰብን ታሪክ ጠንቅቆ ማወቁ ደግሞ በ2018 በልዑል ሃሪ እና በሜጋን ማርክል የተደረገውን ጋብቻና የሠርግ ስነሥርዓት፣ በ2012 የተካሔዱትን የንግሥት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ የአልማዝ ኢዮቤልዩ አከባበር ሥነ ሥርዓቶች እንዲሁም በ2011 በልዑል ዊልያምና በኬት ሚድልተን መካከል የተካሔደውን የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች በመሪነት እንዲዘግብ ረድቶታል፡፡

ላለፉት ሃያ ዓመታት ተሳትፎ ካደረገባቸው ዘገባዎች መካከል አንዱ በነበረው ሠበር ዜናም ከቀድሞው የፍልስጤም መሪ ያሲር አራፋት እስከ ታላቁ የፖፕ ሙዚቃ ንጉሥ ማይክል ጃክሠን ህልፈተ ሕይወት ታላላቅ ዘገባዎችን ሸፍኗል፡፡ የ57 ዓመቱ ትውልደ እንግሊዛዊ የቢዝነስ ጋዜጠኛ በረጅም ዓመታት የሥራ ሕይወቱ ቃለ መጠይቅ ካደረገላቸው ታላላቅ ሰዎች መካከል የቲቤታውያን መንፈሳዊ መሪው ዳላይ ላማና ተዋናይት ጆአን ኮሊንስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe