‹ካርታ ›የሚሻው ፍኖተ ካርታ?

‹‹እንክርዳድ ዘርቶ እንክርዳድ ያጨደው›› የ20 ዓመታት ስህተት የኢትዮጵያ ትምህርትፖሊሲ?

መነሻ
በዩኤስ አሜሪካ አዮዋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ማሃርሺ የተባለ የማኔጅመንት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የምትማር አንድ ወዳጄ ያጫወተችኝ ጉዳይ የእኛን ሀገር የትምህርት ስርዓት ይበልጥ እንድታዘበው አድርጎኛል፡፡ ወዳጄ እንደነገረችኝ ምንም እንኳን ለመማር የተመዘገበችበት ት/ት ክፍል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሆንም በመጀመሪያ ሲሰጣት የነበረው ስልጠና ግን በቀጥታ ከትምህርቱ ጋር የሚገናኝ አልነበረም፡፡
ስልጠናው ትኩረቱን ያደረገው የህይወት ክህሎት ላይ ነበር፡፡ አላማው የተማሪዎቹን አዕምሯዊ ንቃት በማሳደግ ለመደበኛው ትምህርት ማዘጋጀት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃዎችን ስፈልግ በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች የተለመደ አሰራር መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ በእኛ ሀገር ግን ይህን አይነት መንገድ የለም፡፡ ወደዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች በቀጥታ ነው ወደመደበኛው ትምህርት የሚገቡት፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ወጣቶች ለሚያሳዩት አስነዋሪ ባህርይ ምክንያቱ ምናልባትም ይህ ባለመደረጉ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ መንገድ ልጀምር ነው ብሏል፡፡
ከሰሞኑ ከነበረው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ስህተትና እሱን ተከትሎ በወላጆችና በተማሪዎች ሲቀርብ ከነበረው ቅሬታ ባሻገር ሌላም አዲስ ነገር ሰምተናል፡፡ ላለፉት ረዘም ያሉ ዓመታት ለሶስት ዓመታት ብቻ ሲሰጥ የነበረው የዩኒቨርሲቲ የዲግሪ መርሀ ግብር ቆይታ ወደ አራት አመት ከፍ እንዲል ተወስኗል፡፡
በ2012 ዓ.ም ወደ መንግሥትም ሆነ የግል ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ አዲስ (የመጀመሪያ ዓመት) ተማሪዎች ትምህርት የሚጀምሩት በ15 አዳዲስ ትምህርቶች መሆኑንም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አስታውቋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የሚሰጡት የትምህር ዓይነቶች ለሁሉም የትምህርት ክፍሎች የጋራ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡
ትምህርቶቹም ተማሪዎች በአስተሳሰብ ምጡቅ እንዲሆኑ፣ ብዝሀነትን፣ የሀገርን ባህል፣ ሀገር በቀል ዕውቀቶችንና ታሪክን እንዲያውቁ የሚያደርጉ ናቸው ብሏል ኤጀንሲው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት፣ ስነምግባር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት የሀገሪቱ የትምህርት ስርዓት እንዴት ይቃኝ? በሚል ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በምሁራን ሰፊ ጥናት ሲደረግና ሕዝብም ሲወያይበት መቆየቱን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱአለም አድማሴ ገልጸዋል፡፡ በዚሁ መሰረትም በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች ተቋማቱ አዳዲስ የትምህርት ዓይነቶችን መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ላይ ተደርሶ ለዚሁ ዝግጅት መደረጉን፣ አሁን ያለው ሁኔታም ትምህርቱን ለመጀመር የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አዲስ መንገድ?
የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የለውጥ ስራዎች ማስጀመሪያ መድረክ ባሳለፍነው ሳምንት ተካሂዷል፡፡ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው መድረክ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በ2012 የትምህርት ዘመን የሚተገበሩ አሠራሮችን እና በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲኖር ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል። የተለያዩ መነሻ ፅሁፎች ቀርበው የጋለ ውይይት ተስተናግዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፥ በኢትዮጵያ የምርምር ተቋም ሊሆን የሚችል ዩኒቨርሲቲ እንደሌለ አመላክተዋል። እሳቸው እንዳሉት በአለም አቀፍ መስፈርት መሰረት 50 በመቶ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አባላት ፕሮፌሰሮች ሊሆኑ ይገባል።
በዚህ መስፈርት ከታየም በኢትዮጵያ ይህንን የሚያሟላ ዩኒቨርሲቲ ባለመኖሩ የምርምር ተቋም ሊሆን የሚችል ዩኒቨርሲቲ እንደሌለ ተናግረዋል። እናም የዩኒቨርሲዎችን አቅም መገንባት በቀጣይ በትኩረት የሚሰራበት እንደሚሆንም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓት ለማሻሻል የተዘጋጀው የ15 ዓመታት የትምህርት ፍኖተ ካርታም ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በፍኖተ ካርታው ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉት ደረጃዎች ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን፥ የምክክር መድረኩም የማሻሻያዎቹ አካል ነው ተብሏል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይህን የመጀመሪያውን የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ከሶስት ዓመታት በላይ ከፈጀ የዝግጅት ምዕራፍ በኃላ ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ይህ ፍኖተ ካርታ አጥኚ ቡድን ተቋቁሞ የትምህርትና ስልጠና ስርዓቱ ያለበትን ሁኔታ ከፈተሸ ወዲያ የደረሰባቸውን ችግሮች ሊቀርፉ የሚችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች የተካተቱበት ነው፡፡ ፍኖተ ካርታው እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ የሚተገበር ሲሆን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያው የትግበራ ዓመት ይሆናል፡፡ ፍኖተ ካርታው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ችግሮችን ለይቶ መፍትሔዎችን አስቀምጧል፡፡ በፍኖተ ካርታ ዝግጅት ወቅት የተለዩት ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ የሥርዓተ ትምህርት አዘገጃጀት ይዘትና ትግበራ ችግር፣ የዩኒቨርስቲዎችዎች በተልዕኮ አለመለየት፣ የትምህርት አደረጃጀት ችግር፣ የህጎች፣ የአሠራሮችና ስታንደርዶች አለመኖርና አለመናበብ፣ በቂና ብቁ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ ግብዓቶች ከትምህርት መስፋፋቱ ጋር አለመጣጣም፣ ዩኒቨርስቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዝቅተኛ መሆን/አለመኖር፣ የሲቪል ሰርቪሱ አለመዘመን – ሥልጠና መስክና የሥራ ገበያ አለመጣጠም ሲሆኑ በዚህ ምክንያት የመጡ ችግሮችም ተለይተው ቀርበዋል፡፡
የስነምግባር እና የሞራል ውድቀት፣ ስርዓት አልበኝነትና ምክንያታዊ ያለመሆን፣ የስራ ጠባቂነትና ጥገኝነት፣ የወቅታዊ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ያለማወቅና ያለመረዳት፣ የተግባቦትና የመረዳዳት ችግር፣ ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ይዞ አለመገኘት ናቸው፡፡
በፍኖተ ካርታው እነዚህን ችግሮች ከስር መሰረታቸው ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመፍትሄ ምክረ-ሃሳቦች ተቀምጠዋል፡፡ ዋና ዋናዎቹም የአንደኛ አመት ተማሪዎችን የታሪክ፣ የጂኦግራፊና አንትሮፖሎጂ፣የኮምፒዩቴሽናል ክህሎት፣ የስነምግባር፣ የቋንቋ፣ የስነተግባቦት፣ ምክንያታዊነት፣ ፣የቴክኖሊጂ እና ዓለም ዓቀፋዊ ዕዉቀት ሊያስጨብጡ የሚችሉ ኮርሶችን መስጠት፣ ዩኒቨርስቲዎች እንደተልኳቸው ትኩረት ማደራጀት፤ የምርምር፣ የአኘላይድ ሳይንስ፣ የቴክኒካል ዩኒቨርስቲ ሆነው እንዲደራጁ ማድረግ፣ የዩኒቨርስቲ ትምህርት ቆይታ 4 አመት እንዲሆን (ለኢንጂነሪንግ 5፤ ለሜዲሲን 6)፣ 2 አመት ለMasters, 4 ዓመት ለPh.D እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
በፍኖተ ካርታው መሰረት ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ለሁሉም ተማሪዎች በመጀመሪያ ዓመት የሚሰጡ 15 የትምህርት አይነቶች የተለዩ ሲሆኑ እነዚህም፡- 1. Critical Thinking 2. General Psychology 3. Global Trends 4. Economics 5. Communicative English Language Skills I 6. Geography Of Ethiopia And The Horn 7. Mathematics (For Natural Science/ For Social Sciences) 8. Introduction To Emerging Technology 9. Anthropology 10. Entrepreneurship 11. History Of Ethiopia And The Horn 12. Communicative English Language II 13. Moral And Civics Education 14. Inclusiveness 15. Physical Fitness ናቸው፡፡
ዩኒቨርስቲዎችን በተልዕኮ የመለየት ስራዎችም ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ በተልዕኮ መለየት ሲባል ለምሳሌ በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ኢንጂነሪንግ ትምህርቶች የሚሰጡ ከሆነ በቀጣይ የተሻለ ልምድና የማስተማሪያ ግብዓቶች ያሟላው ዩኒቨርስቲ ብቻ እንዲያስተምረው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይሄ ስራ ጊዜ የሚፈልግ ስለሆነ በአንድ ጊዜ ሊገባበት ባይችልም ዩኒቨርስቲዎቹ ያሉበትን ደረጃ በመፈተሸ የትኛው ተልዕኮ እንደሚሰጣቸው የማሳወቅ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በሂደት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ወደተሰጣቸው ተልዕኮ ብቻ አተኩረው ይሰራሉ ተብሏል፡፡ ይሔም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አንዱ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
የ20 ዓመት ስህተት?
ባለፈው ጊዜ የትምህርት ፖሊሲውን ለማሻሻል ያለመ ምክክር ተደርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ መንግሥት እንዳስታወቀው ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ገቢራዊ ሆኖ ሲሰራበት የቆየው የትምህርት ፖሊሲ በርካታ ውስብስብ ችግሮች የነበሩበት ነው:: ከአገር በቀል ዕሴቶች እና ዕውቀቶች ይልቅ ለምዕራባውያን አመለካከት እና ፍልሥፍና ትኩረት ሰቶ መቆየቱም ሃገሪቱ በቂ የተማረ እና ለውጥ የሚያመጣ ትውልድን በመቅረጽ ረገድ ያደረገችውን ጥረት በእጅጉ ጎድቶታል ተብሏል:: አጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱን የትምሕርት ተቋማቱን አደረጃጀት እና የትምሕርት ፕሮግራሞች ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት የሚያጠና ገለልተኛ ተቋም አለመቋቋሙ እንዲሁም የመምህራኑ ምልመላ እና ክህሎት ከትምህርት አሰጣጡ ጉድለት ጋር ተደማምሮ የተማሪዎች ውጤት እንዲያሽቆለቁል እና የተፈለገው ውጤት እንዳይገኝ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረጉንም መንግሥት ገልጿል::
የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ዘርፉም በሁሉም አካባቢ የፍትሃዊነት እና የተደራሽነትን ጥያቄ ሊፈታ በሚችል መንገድ ትኩረት ተሰቶት ዳግም እንዲጠና ተጠይቋል:: አዲሱ የትምሕርት እና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ረቂቅ ሰነድ ይህንን ለ20 ዓመታት የዘለቀ ስህተት ለማረም የመጣ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የትምሕርት ፖሊሲውን ለማሳለጥ ሲባልም የሃገሪቱን የትምሕርት ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስት ክፍሎች እንዲደራጁ አድርጓል::
መንግሥት ከ 20 ዓመታት በላይ በተግባር ተፈትኖ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻለም ያለውን የሃገሪቱን የትምሕርት ፖሊሲ ለማሻሻል አሁን ያቀረበው አዲስ ሰነድ የአጠቃላይ ትምህርት የቴክኒክ እና ሙያ የከፍተኛ ትምሕርትን እና የትምሕርት ዘርፍ አስተዳድሩን ለመለወጥ እና ለማሻሻል የሚረዳ ነው ተብሏል::
የትምህት ጥራት ማሽቆልቆል
ባለፈው ዓመት በወጣው የአዲስ አበባ የትምህርት ተቋማት ደረጃ መሥፈርት አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች እንደሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉራቶሪ ኤጀንሲ አስታወቆ ነበር። ችግሩ በትምህርት ጥራት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተገልጿል።
በወጣው የትምህርት ተቋማት ደረጃ መሥፈርት በአዲስ አበባ ከተማ ከ1,407 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1,106 ከደረጃ በታች እንደሆኑ የከተማዋ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉራቶሪ ኤጀንሲ አስታወቋል። ኤጀንሲው በከተማዋ ውስጥ ካሉት 2,072 የትምህርት ተቋማት ውስጥ በ1,407 ተቋማት የውጭ ኤክስቴንሽን ጥናት ማድረጉን ገልጿል። በጥናቱ መሠረትም የትምህርት ቤቶቹን የጥራት ደረጃ በአራት አስቀምጧል። በደረጃ አንድ ላይ የሚገኙት የጥራት ደረጃ ያላሟሉ 57 ተቋማት ናቸው ተብሏል። ጥራቱን በማሻሻል ላይ የሚገኙ በሚል ደግሞ 1,049 ተቋማት በደረጃ ሁለት ሰፍረዋል። ደረጃ ሦስት የተሰጠው ደግሞ የጥራት ደረጃ መስፈርቱን ያሟሉ በሚል ለ299 የትምህርት ተቋማት ነው። ደረጃ አራት በከፍተኛ ደረጃ ያሟሉ ቢሆንም በዚህ ደረጃ ግን አንዳችም ተቋም እንደሌለ ተነግሯል።
በጥራት ደረጃ ምደባ መስፈርቱ የመምህራን ብቃት፣ የትምህርት ማበልጸጊያ መሣሪያዎች፣ ንጽህና አጠባበቅ፣ የተቋማቱ ሁኔታና መሰል ጥናቱን ሊያግዙ የሚችሉ መመዘኛዎች ተቀምጠው ነበር።
ከትምህርትና ስልጠና ዘርፉ የሚመነጩ ችግሮችን ከመሠረቱ በመፍታት ሥራ የሚወድ ፣ ሌብነትን የሚጠየፍና ለህዝብና ለአገር የሚሰራ ባለሙያና አመራር በመፍጠር የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት የመጀመሪያ የህዝብ ውይይት መድረክን በንግግር በከፈቱበት ወቅት ነበር ይህን ያሉት፡፡ የዴሞክራሲ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ብልጽግና መሠረት የሆነው ትምህርትና ስልጠና የሁሉንም አካል ትኩረት ይሻል ያሉት ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ለትምህርት ሽፋንና ተደራሽነት የሰጠውን ትኩረት ያህል ለፍትሀዊነትና ለትምህርት ጥራት በሚዛናዊነት ትኩረት ባለማድረጉ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል መራመድና የሚፈለግበትን ውጤት ማስመዝገብ እንዳልቻለ አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም ዛሬ በአገሪቱ በምህድስናና በኮንስትራክሽን ዘርፉ ፣ በፍትህ ሥርዓቱ ፣ በህክምና፣ በቴክኖሎጂ ፣በሀብት ቁጥጥር ፣ በአገልጋይነት መጓደልና በሌሎችም ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮች ከትምህርትና ስልጠና ዘርፉ የሚመነጩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ችግሩን ከመሠረቱ መፍታት የሚቻለውም የውጪ ተሞክሮን ሙሉ በሙሉ በመተግበር ሳይሆን ከራሳችን ሀገር በቀል በቀል እውቀት እና ቴክኖሎጂ ጋር በመጠቀም ጭምር ሊሆን እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
‹የዘሩትን ማጨድ››
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ዕድሜው አጭር ከመሆኑ ባለፈ የተደራሽነት (Access)፣ የተገቢነት (Relevance) እና የጥራት (Quality) ችግሮች አሉበት። በተለይ የትምህርት ጥራት መጓደል የትምህርት ዘርፉንም ሆነ ከዘርፉ የሚገኙትን ግብዓቶች በስፋት በሚጠቀሙ ተቋማት ውስጥ እየተስተዋለ ነው። የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ጥናት መድረክ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ላይ የየዘርፉ ምሁራን አስተያየትና ትንተናዎችን በማሰባሰብ ባሳተመው መጽሐፍ ላይ አምዲሳ ተሾመ የተባሉ ምሁር በትምህርት ፖሊሲው ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ላይ ዳሰሳ አድርገዋል። አቶ አምዲሳ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚታየው የጥራት መጓደል የሁሉም መንግሥታት የረጅም ዓመታት ችግር ነው። ለምሳሌ ብንጠቅስ በኃይለሥላሴ ዘመን በ1963 ዓ.ም. የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያ መተግበር የጀመረ ሲሆን፤ መሠረታዊ ትምህርት ለሁሉም፣ ትኩረት ለሣይንስ፣ ትምህርትና ልማት፣ የትምህርት ጥራትና የተሟላ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚሉ ዓላማዎችን ማሳካት የማሻሻያው ግቦች ነበሩ። ይሁን እንጂ የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያው፣ በመሠረታዊ መልኩ የትምህርት ሥርዓቱን ችግሮች አይፈታም የሚል ተቃውሞ ከመምህራኑ ተነስቶ እንደነበር የታሪክ ድርሣናት አስፍረዋል።
የደርግ ሥርዓትም ትምህርት የፖለቲካ ዓላማዎቹን እንደሚያሳካለት በመረዳቱ፣ በአሥር ዓመት ውስጥ ቀድሞ የነበሩ የትምህርት ተቋማትን መቶ በመቶ ለማሳደግ ችሏል። የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ በማካሄድ ከዩኔስኮ ”International Reading Association literary prize” የተባለ ሽልማት በ1972 ዓ.ም ለማግኘት በቅቷል። አዳዲስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲገነቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የድኅረ-ምረቃ ትምህርት መሰጠት ተጀምሯል። ይሁን እንጂ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ በኮታ መሆኑና በአብዛኛው የስኮላርሺፕ ተጠቃሚ የሚሆኑ ምሁራን የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለምን ከሚከተሉት ሶቭየት ሕብረት፣ ጀርመን፣ ኩባና መሰል ሀገራት በመሆኑ ምሩቃኑ አመለካከታቸው የሚቃኘው በሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም ላይ ነው።
የደርግ ሥርዓተ ትምህርት በሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የተገነቡት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶችም ደረጃቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑና መምህራኑም በቂ ሥልጠና ያላገኙ እንደነበር ይጠቀሳል።
ደርግን በማስወገድ መንበረ ሥልጣኑን የተቆናጠጠው በኢህአዴግ የሚመራው የሽግግር መንግሥቱ በ1987 ዓ.ም የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። ይህ ፖሊሲ ለትምህርት መስፋፋት፣ ለተለያዩ የትምህርት ተቋማት መገንባትና ለግሉ ዘርፍ ተሣትፎ በር ከፍቷል። ነገር ግን የፖሊሲው ግቦች እንደ እኩልነት፣ ነፃነት፣ ፍትሐዊነት፣ እውነት፣ የሰብዓዊ መብት መከበርን የመሳሰሉ ዲሞክራሲን ማስረጽ የሚል ሲሆን፤ ዓላማዎቹ በዝርዝር ሲታዩ ተማሪዎችን በቀለም ትምህርት ከማብቃት ይልቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው።
በዘርፉ ብቃት ያላቸውና ለሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች የማይመጥኑ መምህራን፣ አንድም ከትምህርት ቤት በቀጥታ የተመረጡ፣ አንድም ከየወረዳው በፖለቲካዊ ብቃታቸው የተመለመሉ መሆናቸው የጥራቱን ጉዳይ ከመግደሉም በላይ ከታሰበው ግብ ለመድረስ የማይቻል ነው ማለት በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው በርካታ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች እየተገነቡ ሥራ ጀምረዋል። ይሁን እንጂ እንኳን አዳዲሶቹ፤ ነባሮቹ ዩኒቨርስቲዎችም ውስጣዊ አደረጃጀታቸው የተሟላ አይደለም።
ሌላው ለትምህርት ጥራት መጓደል መንስዔ ሊሆኑ ከሚችሉት ጉዳዮች መካከል፣ የትምህርት ፖሊሲው መንግሥት በተለወጠ ቁጥር ለሥርዓቶቹ እንዲመች ተደርጎ መለዋወጡ ነው። በአብዮቱ ዋዜማ የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያ (Educational Sector Review) የተደረገ ሲሆን፣ በደርግ ዘመንና አሁን ባለው በኢህአዴግ ዘመን የተለያዩ የፖሊሲ ለውጦች ተደርገዋል። ይህ ሲሆን ታዲያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የተማሪዎች ችሎታና ተፈጥሮዓዊ ክህሎትን ግምት ውስጥ ያስገባ ጥራት ያለው ትምህርት የመስጠቱ ጉዳይ ነበር። ግን አልሆነም፡፡
የቀደመው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው የተቀረፀበትን ግብ ለመምታት እንዲያስችል በሚል ስትራቴጂዎችና ዝርዝር ፕሮግራሞች ተነድፈዋል። ስትራቴጂው ሁሉንም የትምህርት ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ካሪኩለም መንደፍ፣ አዲስ የትምህርት አሰጣጥ መዋቅር የማስተዋወቅ፣ (የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ከ6-8 ውስጥ እንዲጠናቀቅ፣ የመማሪያ ክፍሎች ከ1-4፣ የመጀመሪያ ሳይክል ከ5-8ኛ፣ ሁለተኛ ሳይክል ሁለተኛ ደረጃ ከ9-10፣ የመሰናዶ ትምህርት ከ11-12፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና (TVET) ያካተተ ሲሆን፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ምርምርን መሠረት ባደረገ ሥልጠና የዲፕሎማ፣ የዲግሪና የድኅረ-ምረቃ ትምህርት እንደሚሰጥ ይጠቅሳል)። ስትራቴጂው ከ1-3ኛ ክፍል ተማሪዎች ያለ ምንም ምዘና በ(automatic promotion) እንዲያልፉ የሚያደርግ ሲሆን፣ መንግሥት የደጋሚና የትምህርት አቋራጭ ተማሪዎችን ቁጥር መቀነስ ላይ ትኩረት ያደረገ ይመስላል።
መንግሥት ከሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሚመስሉትን ስትራቴጂዎችን ለማሳካት፣ በስፋት ይንቀሳቀስ እንጂ በኢትዮጵያ የት/ቤቶች የውስጥ ድርጅት ያለመሟላታቸውና ሥርጭታቸውም ፍትሐዊ ያለመሆኑ፣ በሁሉም ደረጃ የቅበላ መጠኑን ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት አላስቻለም። ለምሣሌ የመጀመሪያው የትምህርት ልማት ፕሮግራም በተተገበረባቸው ዓመታት የአ/አ የቅበላ መጠን 83% ሲደርስ፣ የአፋር 8% ላይ ተገድቦ መቅረቱ፣ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ሴቶች እንደተለመደው ወደ ት/ቤት አለመግባታቸው በዕቅዱ ላይ የታዩ ችግሮች ነበሩ። ከሁሉ በላይ የትምህርት ጥራት የማሽቆልቆሉ ነገር እንዲሁ በዋዛ የሚታይ አልሆነም። መምህራን በቂ ሥልጠና ሳያገኙ፣ የመማሪያ መጽሐፍትና የትምህርት ቁሳቁስ ሳያሟሉ፣ ተገቢ የፈተና (የምዘና) ሥርዓት ሳይዘረጋ ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ ትምህርት እንዲከታተሉ መደረጉ፣ ለትምህርት ጥራቱ መጓደል በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል።
በዚህ መንገድ ዛሬ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሃሳብ የሚሞግቱ ምክንያታዊ ዜጎች ሳይሆን ዱላ ይዘው በሀይል ሌሎች ወገኖቻቸው ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ ሆነዋል፡፡ ምክንያቱም እንክርዳድን የዘራ ስንዴ አያገኝም፡፡
በመጨረሻም
የትምህርት ጥራት መጓደል በእያንዳንዱ የሥራ መስክ የሚፈለገው ሥነ ምግባር ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት እንዲከሰት የሚያደርግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ የምርት መጠን፣ ሥራ አጥነት፣ ጤናማ ትርፍ ማግኘት ቀርቶ ኮርፖሬሽኖች/ኢንዱስትሪዎች የገንዘብ/መዋለ ንዋይ እጥረት እንዲገጥማቸው እያደረገ ነው፡፡ ከሥራ አጦች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ለማኅበራዊ ደኅንነት ጥበቃ ከፍተኛ ወጪ ይወጣል፣ እንዲሁም ከግብር የሚገኝ ገቢ ይቀንሳል፡፡ ችግሩ በጣም ብዙ ነው፡፡
የትምህርት ጥራት ሲጓደል ትምህርት/ሥልጠና የባህሪ ለውጥ ሊያመጣ ስለማይችል ከፍተኛ የሆኑ ምስቅልቅልሎች ይከሰታሉ፡፡ ለምሳሌ ሙስና እንዲህ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው ትምህርት የባህሪ ለውጥ ሊያመጣ ባለመቻሉ ነው፡፡ ወጣቱ የውጭ ባህል አራማጅ የሆነውና የተለያዩ ሱሶች ተጠቂ ለመሆንና ለወንጀል መበራከት የትምህርት ጥራት መጓደል አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ለእሴቶቻችን መሸርሸር ዋናው መነሻ ምክንያት የትምህርት ጥራት መጓደል ነው፡፡
በተለያዩ ጥናቶች እንደተረጋገጠው የተዘረዘሩት ችግሮች ምክንያቶች በርካታ ናቸው። የዕውቀትና ክህሎት ማነስ፣ የሚሠሩትን ሥራ ወዶ በፍቅር አለመሥራት፣ ጤናማ ያልሆነ የሀብት ማግኘት ፉክክር፣ ቸልተኝነት በዋና ምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ትምህርት ከሞተ ሁሉም ሞተ ስለሆነ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጦት የሚከተሉት ምክረ ሐሳቦች ጊዜ ሳይሰጣቸው ተግባራዊ እንዲሆኑ አሁኑኑ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe