ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም እና የካራማራ ድል

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ራሳቸው በፃፉት “ትግላችን” መፅሐፍ ላይ በሶማሌ ወረራ ጉዳይ የነበሩበትን ጭንቀት አልገለፁም። ነገር ግን ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ” እኛና አብዮቱ” በተሰኘው መፅሐፋቸው ሊቀ መንበሩ ስለነበሩበት ሁኔታ እንዲህ ያስቀምጡታል.(ነፍስ ይማር)..
“… በወቅቱ በሶማሊያ መሪ ዚያድ ባሬ የተጠናከረ የኢትዮጵያ ጦር እንዳይገጥመው የሻዕቢያ፣ የህወሃት፣ የኦነግ እና የሲዳማ ነፃ አውጭ ድርጅት መሪዎችን በሞቃዲሾ ሰብስቦ መመሪያ ከሰጠ በኋላ በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘራቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት ክፉኛ ተመታ። … የኢህአፓ አባላትም ” የሶማሊያ ጦር ኃያል ነው። የታጠቀውም መሣሪያ ሁላችንንም ሙሉ በሙሉ በአንድ ግዜ መደምሰስ የሚችል በመሆኑ ነፍሳችንን እናድን” በማለት ሽብር ነዙ። ከዚህም አልፈው በግርግርና በተኩሱ መሃል መሪዎችን ከጀርባቸው እየተኮሱ ገደሉ። ጦሩን መሪ አሳጡት። በዚህ የተነሳ ሠራዊቱ እግሩን ነቀለ። ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ሆነ።
… በሽሽት እየገሰገሰ የመጣውን ጦር ጂጅጋ ላይ ለማስቆም ተሞከረ። ግን አልተሳካም። ይህ አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትል የሚችለውን አሳፋሪ የጦር መፍረስ የተመለከቱት ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አነስተኛ ኃይል ያለው የጦር ክፍል ይዘው ካራ ማራ አካባቢ እየተጣደፉ ደረሱ። ቅጥ በሌለው አኳኋን ፊቱን አዙሮ ወደ ሐረር በመጓዝ ከነበረው ሠራዊት ጋር ተገናኙ። ቆራጥ እርምጃ ወስደው በመሳሪያ ኃይል ቆሬ ላይ እንዲቆም አደረጉት። ሠራዊቱን የገቱት እንዲህ ብለው ነበረ ” አገርህን ለማን ጥለህ ነው የምተሸሸው?”
ለሠራዊቱም በቂ ኃይል አሰልጥነንና አደራጅተን አገራችን የወረረውን የሶማሊያ ጦር ረግጠን እስክናባርር ድረስ በካራ ማራ አካባቢ መሽጋችሁ እንድትከላከሉ ብለው ትዕዛዝ ሰጡ። ጦሩም ትእዛዙን ተቀብሎ ምሽጉን በማጠናከር በመከላከል ጦርነት ተጠመደ።… በዚህም ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃየረለ ማርያም ኢትዮጵያን ከውድቀት አድነዋል።
… ከዛ በኋላ በነበረው አጠቃላይ ውስብስብ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህልውና ከምን ጊዜውም ይበልጥ አደጋ ውስጥ ወደቀ።… ብዙዎቻችን የቋሚ ኮሚቴ አባላት የምናደርገው ጠፍቶን በጨለማ የተዋጥን መሰለን። ተስፋ ወደ መቁረጡም ተቃረበን። በዚህም ምናልባት ለመዘጋጀት እንዲረዳን ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ለምን የተኩስ ስምምነት አናደርግም? የሚል ሃሳብ እስከመሰንዘር ደረስን። ሊቀመንበሩ ግን ሃሳቡን አጥብቀው ተቃወሙ።
” ከፊል ሃገራችን በጠላት ተይዞ የተኩስ ማቆም ስምምነት ማድረግ ማለት መሬታችን አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል። በመሆኑም ይህን የመሰለውን ሃሳብ ማስተናገድ የለብንም። የፈለገውን ያህል መስዋእትነት ቢጠይቀንም የሕዝብ ድጋፍ እስካለን ድረስ በመጨረሻ አሸናፊ ሆነን እንወጣዋለን። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በቅርቡ ለየት ያለ ስልት ቀይሼ ለውሳኔ አቀርባለሁ።” ብለው እየደከመ የመጣውን መንፈሳችንን አነቃቁት።….
እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው ለህዝቡ ሀገር መወረሯን በግልፅ ይፋ አድርገው፣ በ3 ወር ግዜ ውስጥ ታጠቅ የጦር ማሰልጠኛ ሰፈርን መስርተው፣ ሰራዊት አሰልጥነውና የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲሆን ታላቅ የጦር ሰልፍ አካሂደው እንደቃላቸው ሶማሊያን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው የሀገር ዳር ድንበር እንዲከበርና የወገን ክብር እንዲመለስ ያደረጉት!
ይህ ቃል የማይገልፀው ጀግንነት ነውና ክብር ይገባዋል! ክብር ይሁን!
ስለ ድሉ ራሳቸው በፃፉት ትግላችን መፅሐፍ ላይ እንዲህ ይላሉ
“ሶማሊያዎች … እነርሱን ቀርቶ እጅግ ገናና እና ኃይለኛ የነበሩ የአካባቢውን ኃይሎችና የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን የወረራ ሙከራ እየመከተ አሳፍሮ በመመለስ በታሪኩ ለዘለቄታው ተሸንፎ ክብርና ነፃነቱን ያላስገፈፈ ብቸኛ ጥቁር ሕዝብ ለመሆን ያስቻለውን የታሪክ፣ የመንፈስና የሥነ ልቦና አቋሙን ለማስተዋል አልሞከሩም።….”

ክብር ለዚህ ድል መገኘት ድርሻ ላላችሁ ሁሉ…

#ተወልደ በየነ(ተቦርነ)

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe