ወላጆች በሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ላይ ላነሱት ቅሬታ የፈረንሣይ ኤምባሲ ምላሽ ሰጠ

በኮሮና ሳቢያ ችግር የገጠማቸው ወላጆች የዋጋ ጭማሪ አይመለከታቸውም ተብሏል

የሌሲ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን በመቃወም ወላጆች ያሰሙትን አቤቱታ አስመልክቶ ምላሽ የሰጠው የፈረንሣይ ኤምባሲ፣ በኮሮና ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁ ወላጆች የዋጋ ጭማሪው እንዲነሳላቸው እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ የፈረንሣይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦምቴስ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የተገደደው ባለፉት አራት ዓመታት ሲያስታምም የቆየው ኪሳራ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ ነው፡፡ አምባሳደሩ እንዳሉት በትምህርት ቤቱ ከሚማሩ መካከል ከ70 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በመሆኑም የ20 በመቶ የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ተደርሶባቸዋል፡፡ ይህ ጭማሪ በወላጆች ዘንድ ቅሬታ አስነስቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሆኖም እንደ አምባሳደሩ ማብራሪያ ጭማሪው የተደረገው፣ በአገሪቱ ላለፉት አራት ዓመታት በተከታታይ ሲከሰት በቆየው የዋጋ ግሽበትና በመንግሥት በተደረገው የምንዛሪ ለውጥ ሳቢያ ባጋጠመ የወጪ መናር ሳቢያ ነው፡፡ ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ከሚያስተምራቸው 3,000 ገደማ ተማሪዎች መካከል 20 በመቶ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ የልዩ ልዩ አገሮች ዜጎችና አሥር በመቶው ፈረንሣውያን ተማሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በመሆኑም 70 በመቶ በኢትዮጵያ ብር ቀሪውን በዩሮ ለትምህርት ክፍያ ቢያስከፍልም፣ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በተከሰቱ የምንዛሪ ለውጥና የዋጋ ግሽበት ችግሮች ሳቢያ፣ የአሥር በመቶ የትምህርት ክፍያ ኪሣራ ሲደርስበት መቆየቱ ተገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 የ25 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠመው የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ በዚህ ዓመትና ባለፈው ዓመት የ20 ሚሊዮን ብር፣ ዘንድሮ የ10 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠመው በማውሳት፣ የተደረገው ጭማሪ ቢያንስ በአሁኑ ወቅት 20 በመቶ ላይ የሚገኘውን የዋጋ ግሽበት ለማካካስ እንዲረዳ የተደረገ መሆኑን አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡ ከወላጆች ጋር በተደረገ ውይይት ይኸው የትምርህት ቤቱ ወቅታዊ ጉዳይ እንደተብራራላቸው ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ላይ የ20 በመቶ ጭማሪ የተደረገበት የመጪው ዓመት የትምህርት ክፍያ ወደ 116 ሺሕ ብር አሻቅቧል፡፡ ይህ ክፍያ የዓመቱን መመዝገቢያ 3,800 ብር ሳይጨምር ሲሆን፣ ለመጀመርያ ጊዜ ልጆቻቸውን የሚያስመዘግቡ ወላጆችም የ55 ሺሕ ብር የመመዝገቢያ ክፍያ ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህም ጭማሪው ይመለከታቸዋል፡፡ በፈረንሣውያን ተማሪዎችም ላይ የ40 በመቶው ጭማሪ በፊት ከነበረበት ወደ 4,600 ዩሮ ከፍ የተደረገ ሲሆን፣ የመመዝገቢያ 118 ዩሮ፣ እንዲሁም ለመጀመርያ ጊዜ ልጆቻቸውን የሚያስመዘግቡ ወላጆች ከ1,700 ዩሮ በላይ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡

መንግሥት ትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ፣ እንዲያውም እስካሁን ሲያስከፍሉ ከነበረው ላይ ከ50 እስ 75 በመቶ እንዲያስከፍሉ ማድረጉን በማስመልከት ወላጆች፣ የሌሲ ጭማሪ አግባብ እንዳልሆነ ቅሬታ አቅርበው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርት ሚኒስቴር ስለጉዳዩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ጭማሪ እንዳይደረግ እንደሚያደርግ ቢገልጽም፣ ሊሴ ገብረ ማርያም ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም የኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶች ዋጋ በመጨመር ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ወላጆች በትምህርት ቤቱ ላይ ከሚያቀርቧቸው ሌሎች በርካታ ቅሬታዎች መካከል በውጭ ኦዲተሮች ሒሳቡ ተመርምሮ እንደማይታወቅ የሚጠቁመው አንዱ ነው፡፡ ይህን የወላጆች ቅሬታ የሚጋሩት አምባሳደሩ፣ በቅርቡ በገለልተኛ የውጭ ኦዲተር ሒሳቡ ተሠርቶ ሁሉም ለወላጆች ግልጽ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እ.ኤ.አ. በ1947 በኢትዮጵያ መመሥረቱ የሚነገረው ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት፣ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ዕድሳት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሆነና እስከ አሥር ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን አምባሳደር ቦምቴስ አስታውቀዋል፡፡

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካይነት ከማዘጋጃ እስከ መስቀል አደባባይ ባለው መንገድ ላይ በሚካሄደው የማስፋፊያና የከተማ ማደስ ሥራ ምክንያት አጥሩን ጨምሮ ጥቂት ይዞታዎቹ የሚፈርሱበት ትምህርት ቤቱ በምትኩ ተጨማሪ ቦታ ሊሰጠው ከአስተዳደሩ ቃል እንደተገባለት አስታውቋል፡፡ የሚሰጠው ምትክ ቦታም ለመኪና ማቆሚያ እንደሚያውለውና በዚህም መውጫና በመግቢያ ሰዓት የሚከሰተውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እንደሚያስተነፍስለት አስታውቋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1947 ተመሥርቶ እ.ኤ.አ. በ1966 በፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ቻርልስ ደ ጎልና በአፄ ኃይለ ሥላሴ መካከል በተፈረመ የ50 ዓመታት ስምምነት ለኢትዮጵያውን፣ ለፈረንሣውያንና ለሌሎች አገሮች ተማሪዎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ይህ የትምህርት ተቋም፣ ለትርፍ ባልተቋቋሙ የፈረንሣይ ተቋማት ባለቤትነት የሚተዳደር ነው፡፡ ተጠሪነቱም ለፈረንሣይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ የሆነ የፈረንሣይ የውጭ ትምህርት ኤጀንሲ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግለት ይታወቃል፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe