“ዘፀዓት ለኢትዮጵያ”

“ዘፀዓት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ
ባህሩን ሚያሻግር አንድ ሙሴን ይዞ
ቅርብ ነው አይርቅም
የኢትዮጵያ ትንሳኤ
በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባኤ”

ሀገራችን በሁለት ተቃርኖ ውስጥ ያለች ይመስላል፤ በአንድ በኩል በአዲስ አመራር አዳዲስ ሀሳቦች እየተቀነቀኑ የሰላምና የአንድነት ንፋስ መንፈስ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ዕለት ጀምሮ እየተቀነቀነ ያለው የኢትዮጵያ አንድነትና ትልቅነት የነበረውን ውጥረት በማርገብ በኩል የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የተስፋ ንፋስ እየነፈሰ ባለበት በዚህ ሰዓት ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በምንም መንገድ የአዲሱ አመራር ፍላጎት ነው ብሎ ለመውስድ ያስቸግራል፡፡ ምክንያም ስለ ኢትዮጵያና ኢትጵያዊነት ሌት ከቀን በየመድረኩ የሚያስተጋባ አመራር ማንም ኢትዮጵያዊ በፈለገበትና በመረጠው ቦታ ሀብት አፍርቶ መኖር ይችላል የሚለው ህገ መንግስታዊ ድንጋጌን በተቃረነ መንገድ ዜጎችን ያፈናቅላል ተብሎ አይገመትም፡፡

ያለው እውነታ ግን ይህ ነው፤ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ከኦሮሚያ፤ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ከሶማሌ ክልል፤ የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ከኦሮሚያ፤ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ከአማራ፤ወዘተ መፈናቀል የዜጎችቻችን ዕጣ ፈንታ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘመናት የተቆራኘ ባህል ወግ እንዲሁም ሀይማኖታዊ ትውፊት ያላቸው የአማራና የትግራይ ህዝቦች መሀከል የተፈጠረው የሰላም መደፍረስና የጦር ቀረርቶ ማንም ጤናማ ዜጋን ሁሉ የሚያሳስብ ነው፡፡ ሀላፊነት በጎደላቸው በሁለቱም አጥር ውስጥ በሚገኙ አክቲቪስቶችና ሀላፊነት በጎደፈላቸው አመራሮች በሚሰነዘር አጥፊ እሳት ሳቢያ ለዘመናት የኖረውን የሄለቱን ታላላቅ ህዝቦች የሰላም ጥማት እየሸረሸረው ስለመሆኑ በአደባባይ እየታየ ነው፡፡

ሀገር ማለት ሰው ነው የሚል ርዕዮት የሚያቀነቀውን መንግስት እንደ ሩቅ እናያቸው የነበሩ እንደ ሶሪያ ያሉ ሀገራት በጦርነት ፈራርሰው ህዝቦቻቸውም እንጀራ ፍለጋ በአከተማችን መንገዶች ላይ እጃቸውን ዘርግተው ማየት ከጀመርን ውለን አድረናል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም  በአማራና በትግራይ ህዝቦች መሀከል ውስጥ ውስጡን እየተቀጣጠለ ለመላ ሀገሪቱ እንዲተርፍ የሚሰሩ አፍራሽ ወገኖችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ  ከወዲሁ አደብ ሊያስገዛ ካልቻለ የእነ ሲፊያ ዕጣ ፈንታ በምርጫ የሚመጣ እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የሁለቱን ህዝቦች አብሮ የመኖር እሴት የሚያውቁና የሚያከብሩ የሀገይማኖት አባቶችና የሀገር ሽምግሌዎች ጉዳዩን ለመንግስትና ለሁለቱ ክልል አመራሮች ብቻ ሳይተው አፋጣኝ ህዝባዊ የሰላም ኮንፍረንስ ሊያዘጋጁ ይገባል እንላለን፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe