የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ተሳታፊ የሆኑ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፡፡

በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞንና ጃዊ አካባቢ የነበረው የፀጥታ ችግር ወደ መረጋጋት መመለሱ ተገለፀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2011ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ ዛሬ ለሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙኃን በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞንና በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ ከሚያዝያ 17 ቀን ጀምሮ የነበረው የፀጥታ መደፍረስና በአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በግለሰቦች የተነሳ ግጭ አድጎ ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉንና የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት በጋራ በመሥራታቸው አንጻራዊ ሠላም መስፈኑን ተናግረዋል፡፡
የግጭቱን ዝርዝር ሁኔታ ለማጣራት የሁለቱ ክልል መንግሥታት በጋራ እየሠሩ እንደሆኑና ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት በሁለቱም ወገን የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ አካል መጉደሉን፣ ንብረት መውደሙን አስታውቀዋል፤ ድርጊቱ በክልሉ መንግሥት በጥብቅ የሚወገዝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአማራና ቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥታት በጋራ እየሠሩ መሆኑን ተከትሎ በአካባቢዎቹ አሁን ላይ አንጻራዊ መረጋጋት መፈጠሩንም ነው ለመገናኛ ብዙኃን ያስረዱት፡፡
ከኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከኅብረተሰቡ ጋር የሁለቱ ክልሎች የፖለቲካ አመራሮች ቦታው ድረስ በመገኘት የማጣራትና የማረጋጋት ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በግጭቱ ዙሪያ ሕዝቡን ከእውነታው የሚያርቅ ሀሰተኛ ዘገባ የሚያሠራጩ የሚሠሩ ሰዎችና ተቋማት እንዳሉ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ‹‹ከድርጊታቸው ሊታረሙ ይገባል፡፡ እነዚህ አካላት የአማራ መደራጀትና መጠንከር የማይዋጥላቸው ናቸው›› ብለዋል፡፡
ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በተመለከተም በአስተባባሪነት፣ በተባባሪነት፣በተሳተፊነትና አሳታፊነት በድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው እንዳለበት የሚጠረጠሩ አካላትን በሕግ ቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ በጋራ እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ ተሳታፊ የሆኑ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
‹‹የአጣሪ ቡድኑ የሟቾችንና ተጎጂዎችን እንዲሁም ሌሎች የጉዳት መጠኖችን አጣርቶ እንደደረሰ ለሕዝብ እናሳውቀለን›› ያሉት አቶ አሰማኸን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የሚገለጹ ቁጥሮች የተሳሳቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልልን በተመለከተም ከደኅንነት አንጻር ስጋቶች እንዳሉ በሕዝብ እንደሚነሳ ተጠይቀው ‹‹አሁንላይ በክልሉ አንጻራዊ የሰላምና ደኅንነት መሻሻል አለ፡፡ ክልሉን በተለያዩ አጀንዳዎች ወጥሮ ስትራቴጂክ የሆኑ ሥራዎችን እንዳንሠራ የሚሠሩ ኃይሎች ግን ከድርጊታቸው ሊታረሙ ይገባል›› ብለዋል፡፡ በጎንደር፣ ከሚሴ፣ አጣዬና ማጀቴ አካባቢ አጋጥመው የነበሩ ችግሮች ከሕዝብ ጋር ሆኖ በተሠራው ሥራ ወደ ሠላምና መረጋጋት እየተመለሡ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
ትናንት በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችን በተመለከተም ከጋዜጠኞች ተጠይቀው ምላሽ ሰትተዋል፡፡ ‹‹ሠላማዊ ሰልፎቹ በሰላም ተጠናቅቀዋል፤ ሕዝቡም ስሜቱን የገለጸባቸው ነበሩ፡፡ የክልሉ መንግሥትም በሰልፉ የተላለፉ መልዕክቶችን ይዞ ከሕዝቡ ጋር በመሆን በጋራ ይሠራል›› ነው ያሉት፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe