የዓለም ባንክ የንግድ ሥራና ኢንቨስትመንት ምቹነትን በሚለካበት መመዘኛ ኢትዮጵያ ከ100 አገሮች ተርታ ለመሠለፍ አቅዳለች

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራ ኮሚቴ በየወሩ መሰብሰብ ከጀመረ አምስት ወራት አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከሕግና ፍትሕ እስከ ንግድ አሠራርና ምዘገባ እንዲሁም ከብድር አሰጣጥ እስከ ግንባታ ፈቃድ ያሉትን ጨምሮ ዋና ዋና በተባሉና የዓለም ባንክ የአገሮችን የንግድ ሥራና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምቹነትና ቅልጥፍና በሚለካበት መመዘኛ መሠረት ኢትዮጵያ የምትገኝበትን 159ኛ ደረጃ ወደ 100ዎቹ አገሮች ተርታ እንድትቀላቀል ለማሻሻል እንቅስቃሴ ነው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የሚመራውን ይህንን የለውጥ እንቅስቃሴ የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሲሆን፣ ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹትም በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን የተሻለ ምቹ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ እንዲኖራት የሚደረግበት ሥራ ነው፡፡

ከአራት እስከ አምስት ወራት ውስጥ በነበረው የማሻሻያ ሥራ፣ ‹‹ኢዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ›› የተሰኘውን የዓለም ባንክ መመዘኛ በኢትዮጵያ ሁኔታ በአጭር፣ መካከለኛና ረዥም ጊዜ ሒደት ውስጥ ከሚጠበቁ የሪፎርም ዕርምጃዎች መካከል በየተቋማቱ የተካሄዱ የለውጥ ዕርምጃዎች በከፍተኛ ባለሥልጣናቱ አማካይነት ለንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና የንብረት ምዝገባ ተቋማት የቀረቡት ይጠቀሳሉ፡፡

ብሔራዊ ባንክ በተለይ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የንግድና የኢንቨስትመንት ምቹነትን ለማስፈን ይረዳሉ በማለት ከወሰዳቸው የለውጥ ዕርምጃዎች መካከል ሁለት ዓበይት የሚባሉትን የባንኩ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አቅርበዋል፡፡ አንደኛው በብድር አሰጣጥ ሒደት የመረጃ አሰባሰብ ሥራን ማካሄድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ተቀንቀሳቃሽ ንብረቶችን ለብድር ዋስትና ማዋል የሚቻልበት ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን የተመለከተው ነው፡፡

እንደ ብሔራዊ ባንኩ ገዥ ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ከደረሱ ሰዎች ውስጥ እስካሁን የባንክ ብድር ማግኘት የቻሉት ወይም በብሔራዊ ባንክ የመረጃ ቋት ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ከስድስት በመቶ አይበልጡም፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከባንኮች ከ222 ሺሕ የማይለጡ ናቸው፡፡ በሊዝ ካፒታል የብድር አሰጣጥ መሠረት 3,000 ተበዳሪዎች መመዝገባቸው ሲገለጽ፣ ከአነስተኛ ብድር አቅራቢ ተቋማት ብድር ከወሰዱ 5.3 ሚሊዮን ደንበኞች ውስጥም በብሔራዊ ባንክ መረጃቸው እንደተመዘገበ ገዥው አስታውቀዋል፡፡ ይህ በመሆኑም ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ባንክ ውስጥ የነበረውን የ0.4 በመቶ የነበረውን የተበዳሪዎች መረጃ ወደ ስድስት በመቶ ከፍ አደርጎታል፡፡

ይህም ሆኖ በአገሪቱ ካለው ተበዳሪ ውስጥ ይህ ቁጥር ብቻ ተመዝግቦ መገኘቱና ብድር የሚያገኘው ሕዝብ ቁጥርም እጅጉን አነስተኛ በመሆኑ ይህንን ለማሻሻል የሚያግዙ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ሲገለጽ፣ የብድር ተደራሽነትን ለማሳደግ ይረዳል የተባለውና ከቋሚ ንብረት ባሻገር ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በብድር ማስያዣነት ማዋል የሚፈቅደው ሕግ ከወዲሁ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ እንደ ገዥ ይናገር ከሆነ፣ በተንቀሳቃሽ ንብረቶች የብድር ዋስትና ማስያዣነት ገበሬዎች፣ ከፊል አብርብቶ አደሮች፣ የአዕምሯዊ ንብረትና የፈጠራ ባለመብቶችና ሌሎችም በርካታ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ያሏቸው የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሕግ ተዘጋጅቶ ለተወካዮች ምክር ቤት መላኩን አስታውቀዋል፡፡ ምንም እንኳ ከንግድና ኢንቨስትመንት ቅልጥፍናና ማሻሻያ ዕርምጃዎች ጋር በቀጥታ ባይገናኝም፣ ተያያዥ ነው በማለት የጠቀሱት የብድር ክፍያ ማራዘሚያ ላይ የተደረገው ማሻሻያን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር መሠረት ባንኮች ብድር ማራዘሚያ እስከ ሦስት ዙር የሚፈቅዱበት አሠራር ይከተሉ ነበር፡፡ ይህ በአሁኑ ወቅት እስከ ስድስት ጊዜ የብድር ማራዘሚያ በባንኮች ሥልጣን አማካይነት እንዲፈቀድ የተደረገበት ማሻሻያ ለተበዳሪዎች ትልቅ ዕርምጃ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እሸቴ አስፋው ያቀረቡት የንግድ ፈቃድና ምዝገባ አዋጅ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ነው፡፡ የንግድ ፈቃድ ለማግኘትም ሆነ የንግድ ኩባንያን ለማስመዝገብ ከዚህ ቀደም የነበረውን ውጣውረድ በማጣቀስ፣ ከዚህ ቀደም  ለንግድ ፈቃድ ለማውጣት ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተረጋግጦ እንዲቀርብ የሚጠየው የቋሚ አድርሻ ማረጋገጫ የኪራይ ወይም የሊዝ ውል እንዲሁም ለግል ይዞታ የሚጠየቀው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታና ደብተር እንዲቀርብ የሚጠይቀው አሠራር እንዲቀር ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም የንግድ ስያሜን በጋዜጣ ማሳወጅ፣ የንግድ ማኅበራት ሲደራጁም በሕግ የተደገፈና ተቀባይነት ያገኘ የመመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ማቅረብ ብሎም፣ የታክስ ከፋይነት መለያ ቁጥር፣ ከታክስ ዕዳ ነፃ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ማቅረብ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚቀርቡበት አሠራር እንዲቀር መደረጉን አቶ እሸቴ አብራርተዋል፡፡ ይልቁንም ወደፊት የንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ ማደስና የንግድ ስያሜ ማስመዝገብ በኦንላይ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡ ከ1,500 በላይ የነበሩት የንግድ ሥራ ማካሄጃ መደቦችም ወደ 500 ዝቅ እንዲሉ መደረጋቸውንም አውስተዋል፡፡ 3/4ኛ ካፒታላቸውን ኪሳራ ያስመዘገቡ ኩባንያዎች በአዲሱ ሕግ ወደ 1/4ኛ ተሻሽሎላቸዋል ብለዋል፡፡

እንዲህ ያሉ የፋይንናንስና የንግድ ምዝገባ ማሻሻያዎችን ጨምሮ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ፣ በንብረት ምዝገባ፣ በግብር ክፍያ፣ በድንበር ተሻጋሪ ንግድ፣ የአነስተኛ ባለአክሲዮኖችን መብት በማስጠበቅ፣ በንብረት ማስመዝገብ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና በውል ማስፈጸም በመሳሰሉት መስኮች የዓለም ባንክ ያስቀመጣቸውን መመዘኛዎች ለማሟላት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን በሚኒስትሮችና በሚመለከታቸው ባለሥልጣናት አማካይነት ማብራሪያ ቀርቦበታል፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽሩ አቶ አበባው እንዳሉት እንዲህ ያሉት ማሻሻያዎችን በማስፈጸም፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ደረጃ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ይህ ዓይነቱ የማሻሻያ እንቅስቃሴ ግን ከዚህ በፊት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አስተዳደር ወቅትም ይካሄድ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እንደውም በዚያን ወቅት ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ የ‹‹ኢዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ›› መለኪያዎች እስከ 50 ያሉትን ደረጃዎች ለማግኘት አልማ ትንቀሳቀሳለች ሲባል ነበር፡፡ እንደ አቶ አበበ ምልከታ ይህ ከእውነታው የራቀ ዕቅድ ነበር፡፡ እንደውም ከአምስትና ከስድስት ዓመታት በፊት በነበረው ሁኔታ የንግድና ኢንቨስትመንት ምቹነት የሚለካበት የዓለም ባንክ መመዘኛ ሚና እንደ ‹‹ቁንጅና ውድድር›› እንጂ የአገር ጉዳይ ሆኖ እንደማይታይ አስታውሰዋል፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe