አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ
የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እየተጠናቀቀ ባለው 2011 ዓ.ም ከፍተኛ አነጋገሪ ሰው ነበሩ፡፡ ከእስር ቤት እንደወጡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ለ3 ሰዓታት ያህል በቤተመንግስት መነጋገራቸውን የሚናገሩት አቶ አንዳርጋቸው በየመድረኩ የሚያደርጓቸው ንግግሮች የለውጥ ሀይሉንና ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ተገፋን የሚሉ ወገኖችን ማነታረኩ ቀጥሏል፡፡ ያመኑትን ነገር ፊት ለፊት በመናገር የሚታወቁትና ለከንቱ የውዳሴና የፖለቲካ ፍጆታ ጊዜያቸውን አያጠፉም የሚባልላቸው አቶ አንዳርጋቸው በ2011 ዓ.ም ለህትመት ከበቃው ‹ትውልድ እንዳይደናገር ፤ እኛም እንናገር› የተሰኘ መፅሀፍቸውን መውጣት ተከትሎ በየቦታው እየተገኙ ንግግር ማድረጋቸው አሉ የተባሉ የፖለቲካ ልዩነቶችንና ለውጦችን ይፋ ለማድረግ ተጠቅመውበታ ፤
አቶ አንዳርጋቸው እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት አጋማሽ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን የብሔር ተኮር ፖለቲካና የጽንፈኞች አካሄድ በተመለከተ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ‹ለውጡ እየተቀለበሰ ነው› ብለው ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን የተናሩ ሲሆን ወደ አትላንታ ባመሩበት ወቅትም ‹ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ፍኖተ ካርታውን ሰርቼ የሰጠኋቸው እኔ ነኝ› በማለት መናገራቸው የወቅቱ አነጋጋሪ አጀንዳ ነበር፡፡ እንደሳቸው አባባል የለውጥ ሀይሉ ሀገሪቱን ለመምራት በቂ ዝግጅትና ልምድ ስለሌለው ወደፊት የሀገሪቱን ህዝቦች በአንድነትና በጋራ ለማስቀጠል የድንበር ኮሚሽንና የእርቀ ሰላም ኮሚሽን መቋቋም እንዳለበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት እሳቸው ናቸው፡፡
ሌላው አነጋጋሪው የአቶ አንዳርጋቸው ንግግር በቅርቡ በካናዳ ቶሮንቶ ያደረጉት ንግግር ነው፡፡ባለፈው ሐምሌ 12,2011 በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ ውስጥ የኢዜማ የድጋፍ ሰጪ በጠራው ስብሰባ ላይ የተገኙት ግንቦት ሰባትን ከመሰረቱ አንዱ የሆኑት እና በዋና ጸሐፊነት የገለገሉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለተሰብሳቢዎቹ ባሰሙት ንግግር ላይ ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ “ለግንቦት ሰባት ቁልፍ መረጃዎችን በመስጠት አንገታቸውን ለካራ ፣ግንባራቸውን ለጥይት ፣ቤተሰቦቻቸውን ለስደት ሰጥተው እንደ ነበር እጫውተውኛል “ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ በስብሰባው ላይ ከታደሙት መካከል እንዱ የነበረው የዋሊያ ኢንፎርሜሽን ጋዜጠኛ ኤልያስ አወቀ ሰሞኑን እንደ ዘገበው እና የስብሰባውን ድባብም በተመለከተ ለህብር ራዲዬም በስልክ እንዳረጋገጠው ለሰላሳ አራት ደቂቃዎች ንግግር ያደረጉት አቶ አንዳርጋቸው ከአራት አመታት የእስራት ቆይታ በወጡ ማግስት ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድን በጽ/ቤታቸው ሲያነጋግሯቸው” አንተ ለአራት አመታት ታስረሃል፣ እኔ ደግሞ ለስድስት አመታት በመታሰሬ አንተ የሁለት አመት እዳ አለብህ አሉኝ፣እኔም እንዴት?ስል ዶ/ር አብይን ጠየኳቸው”ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው አውስተዋል።
ከጠ/ሚ/ር አብይ ጋር ለሁለት ሰዐታት የዘለቀ ንግግር ማድረጋቸውን ለታዳሚዎቹ የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው”እኔ ለእናንተ መረጃ ለማቀበል ስል አንገቴን ለካራ፣ግንባሬን ለጥይት ፣ቤተሰቦቼን ለስደት ዳርጌ የአጃ ቂጣ እንዲበሉ ፈርጄባቸው ፣በህይወቴ ላይ ቁማር ተጫውቼበት ነበር።የዚያ መረጃ ምንጩ እኔ መሆኑ ቢታወቅ ኖሮ ጨካኙቹ ወያኔዎች ስጋዬን ይዘለዝሉት ነበር ሲሉ ዶ/ር አጫውተውኛል። “በማለት አቶ አንዳርጋቸው ስለ ምስጢራዊ ውይይታቸው ለተሰብሳቢዎቹ በግርድፉ ገልጸዋል። የመረጃው ይዘት ፣እንዴት እና መቼ ከወያኔ እጅ ሾልኮ ለግንቦት ሰባት እንደተሰጠ ከመዘርዘርም አቶ አንዳርጋቸው ተቆጥበዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ከፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለውን እርቅ እሳቸው እንዳከናወኑት ከዚህ በፊት ተናግረው የነበረ ሲሆን በሁንም በድጋሚ ማረጋገጫ ሰጥተውበታል፡፡እንደ አቶ አንዳርጋቸው የቶሮንቶው የኢዜማ ስብሰባ ገለጻ ከሆነ በኤርትራው ፕ/ት በአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እና በ ጠ/ሚ/ር አብይ መካከል የተደረገውን ስምምነት መንገድን የጠረጉት እርሳቸው መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን ” ከፕ/ት ኢሳያስ/ከሻቢያ ጋር ለመታረቅ በፕሬዜዳንቶች፣ በንጉሶች ፣በኤሚሮች፣በሼኮች ሞክሪያለሁ። አሁን ግን ልታስታርቁን የምትችሉት እናንተ ግንቦት ሰባቶች በተለይ አንተ ነህ፣ ቀልቤም ቢሆን አንትን ብሎኛል እና እባክህን አስታርቀን ሲሉ ተማጸኑኝ ።እኔም እስቲ የተቻለኝን ልሞክር ብዬ በቀጥታ ወደ ኤርትራ በማምራት አቶ ኢሳያስ አፈወርቅን ስለጉዳዩ አነጋገርኳቸው።ፕ/ቱም ‘ይሔ በወያኔ ስር ያደገ፣ ግልገል ወያኔን እንዴት ታምነዋለህ?’ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገለጹልኝ።እኔም በመቀጠል አይ ሰውየውንስ አምናቸዋለሁ አልኳቸው።ፕ/ት ኢሳያስም ‘ምን የሚያሳምንህ ምክንያት አለህ?’ሲሉኝ ተከታይ ጥያቄ አቀረቡልኝ።እኔም አንተ የምታውቀው አንዱን ምስጢር ጨምሮ እነዚያ ስለ ሻቢያ የተነገሩት እና ከወያኔ አፈትልከው የወጡት አራቱ ምስጢሮችን እንድናገኛቸው የርዳን ዶ/ር አብይ እኮ ነው አልኳቸው። አቶ ኢሳያስም ሳያንገራግሩ ‘ይሄንን ያደረገው እርሱ ከሆነማ ጉዳዩን ለእኔ ትውልኝ በማለት የፖለቲካ ጉዳዬች ሐላፊ እና አማካሪያቸው የሆኑት አቶ የማነ ገ/አብን ወደ አ/አ በአስቸኳይ እንደሚልኳቸው ቃል ገቡልኝ።ውሎ ሳያድርም የእርቀ ሰላሙ ስምምነት ተፈረመ” በማለት አቶ አንዳርጋቸው በኢትዬ-ኤርትራ ስምምነት ላይ የእርሳቸው ስውር እጆች እንዳሉበት ለቶሮንቶ የኢዜማ ደጋፊዎች ተናግረዋል ። ስለ አራቱ ምስጢሮች ምንነት በተመለከት ግን ለማብራራት አልፈለጉም ፣
የአቶ አንዳርጋቸቸው ሌላው አነጋጋሪ ንግግር ስለሰኔ 15ቱ የባለስልጣናት ግድያ ቅድሚያ ትንበያ ስለማድረጋቸው የተናገሩትን ይመለከታል፡፡የዶ/ር አብይ አሕመድ ኢትዬጵያ ውስጥ ከሚታየው የፖለቲካ ትኩሳት አኳያ ምን ማደረግ እንዳለበት እና የተያያዘውን የሽግግር ወቅትን እንዲያሳካ ከተሞክሯቸው አኳያ ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) ቀርጸው ለጠ/ሚ/ሩ እና ለባለስልጣናቱ መስጠታቸውን እና የአክራሪ ብሔርተኝነት በአገሪቱ መንሰራፋቱን በቶሮንቶው ስብሰባ ላይ የጠቀሱት አቶ አንዳርጋቸው ባለፈው ሰኔ 15 ,2011 ዓም በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የክልሉ ፕ/ት የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተገደሉበትን አሳዛኝ ክስተት በተመለከተ”ማ ማንን እንደሚገድል ስም ዝርዝራቸውን ሳይቀር ጽፌ በቅድሚያ ሰጥቼው ነበር(ለጠ/ሚ/ሩ?)”ሲሉ መናገራቸው ይፋ ሆኗል፡፡
ኢትዬጵያ ከተደቀነባት የጎሳ ፖለቲካ ቁርቋሶ የተነሳ” 80%የመበታተን እድል አላት” ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “ኢትዬጵያን ከመበታተን ለመታደግ ከተፈለገ በቀሪው 20% ላይ ትኩረት አድርገን ዶ/ር አብን ከመደገፍ ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፣ዶ/ር አብይ ከስልጣን ቢወርዱ መከላከያውን የሚቆጣጠር ፣የስልጣን ክፍተቱን የሚሞላ አንዳችም የፖለቲካ ሀይል በአሁኑ ሰአት አይኖርም ” በማለት ለታዳሚዎቹ አቋማቸውን እና ስጋታቸውን አካፍለዋል።
“ከማንም መንግስት ጋር በፍቅር አድሬ አላውቅም ፣ተወዳጅቼም አላውቅም ፣አደርባይም ሆኜ አላውቅም።” ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ስለ ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ ስብእና በተመለከተ ሲናገሩ ” ዶ/ር አብይን በተመለከተ ልናገር የምችለው አንድ ትልቅ ነገር ቢኖር እርሱ ውስጥ ያለውን ኢትዬጵያዊነት ስሜት ማንም የአንድነት ሀይል ነኝ ብሎ ከሚዘምረው ፣ በየአደባባዩ ከሚለፍፈው እና ከሚጮኸው ቡድን ሆነ ግለሰብ መካከል ከዶ/ር አብይ አሕመድ ጋር በጭራሽ የሚስተካከል የለም ” ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው በዶ/ር አብይ አሕመድ ላይ ያላቸው ጽኑ እምነትን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዬጵያ ውስጥ የተወሰኑ ክልሎች በተለይ ደግሞ የኦሮሚያ፣የትግራይ እና የአማራ ክልሎች ከፌደራሉ መንግስት ያልተናነሰ ሚሊሻዎችን ማሰልጠናቸው እና የጦር መሳሪያዎችን ማጋበሳቸውን የመከላከያ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በአደባባይ ሲናገሩ ተደምጠዋል።እንደ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የቶሮንቶ ኢዜማ ስብሰባ ገለጻ ግን የትግራይ ክልላዊ መንግስት “የሚሳየል ባለቤት ነው፣ የጦር መሳሪያው የተገዛውም ከመንግስት ካዝና ሳይሆን ህወሃት የሚያስተዳድራቸው በእነ ኤፈርት አማካኝነት ከሕዝቡ እጅግ ብዙ ገንዘብ ስለዘረፈ የሚሳየሉ ግዢ የዚያ ውጤት ነው” ማለታቸውን እና ወደፊትም ቢሆን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አዳዲስ መረጃዎችን በስፋት ይዘው እንደሚመጡ ቃል መግባታቸው ታውቋል።
የአቶ አንዳርጋቸውን የዚህ አይነት ንግግር የሰሙ ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሀገር ክህደት ሊስጠይቃቸው የሚችል ሚስጥር ማውጣቸውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ሀገሪቱ እንደ ሀገር ጠላት ብላ ከፈረጀችው የኤርትራ መንግስትና አሸባሪ ብላ ከፈረጀችው ግንቦት 7 ጋር ይሰሩ እንደነበር መገለፁ ጠቅላይ ሚኒስተሩን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
በሌላ በኩል ወቅቱ የትግል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ሀይሎች በወቅቱ የነበረውን አምባገነን መንግስት ለመጣል ከማንም ጋር ቢሰሩ እንደ ሀገር ክህደት ሊያስጠይቃቸው አይገባም ሲሉ ይከራከሩላቸዋል፡፡
በሌላ በኩል የዚህ አይነት ንግግር በየመድረኩ የሚያደርጉት አቶ አንዳርጋቸው ሀገሪቱ ገና ተረጋግታ ወደ ሰላማዊ መንገድ ባልገባችበት ወቅት የዚህ አይነት ትላልቅ ሚስጥሮችን በአደባባይ መዘርገፋቸው የጤንነታቸውን ሁኔታ የሚጠራጠሩ አሉ፡፡ አንዳንዶች እንደውም ለረዥም ዓመታት በእስር ቤት የቆየ ሰው ከእስር ቤት ሲወጣ ከፍተኛ የስነልቦና ቀውስ ሊያጋጥመው ስለሚችል የባለሙያ እርዳታ ሳያገኙ ወደ ፖለቲካው የመቀላቀላቸው ምክንያት አድርገው የሚወስዱ ወገኖች አሉ፡፡ ያም ሆኖ አቶ አንዳገርጋቸው በሰጧቸው መግለጫዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ፖርቲያቸው የሰጡት ማስተባባያም ሆነ ማረጋገጫ የለም፡፡