የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ‹ብላክ ቦክስ› የት ነው?

 ‹ኦሮሚያ በፊንፌኔ ላይ ያላትን የባለቤትነት መብት ለማስከበር እንሰራለን›

መነሻ

መጋቢት 1 ቀን 2011 ማለዳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 -800 ማክስ አውሮፕላን በረራ ከጀመረ በስድስት ደቂቃ ውስጥ ተከስክሶ 157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወቃል፡፡አውሮፕላኑ ለመከስከስ ያበቃውን ምክንያት ለማወቅ የሚደረገው ምርመራ ውስብስብና አስቸጋሪ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ምርመራው ከኢትዮጵያ ባሻገር የቦይንግ ኩባንያ፤ የአሜሪካ የበረራ አስተዳደር ባለሥልጣን እና የፈረንሳይ መንግሥትን እያሳተፈ ነው።

እሁድ ማለዳ ከቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ መረጃ መቅጃ መሳሪያ (ብላክ ቦክስ) የተገኘው በቀጣዩ ቀን ሰኞ እለት ነበር። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ የዲጂታል የበረራ መረጃ መቅረጫ እና የአብራሪዎች ክፍል የድምፅ መቅጃ መሳሪያ መገኘታቸውን አረጋግጧል።

ካፒቴን አማረ ገብረሃና እንደሚሉት የበረራ መረጃ የሰነደው መሳሪያ “የአውሮፕላኑ ፍጥነት፤ በምን አይነት ኹኔታ እንደነበረ፤ በውስጡ የነበሩ እንቅስቃሴዎችን መዝግቦ የሚይዝ” መሳሪያ ነው። የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ካፔቴን አማረ የአብራሪዎች ክፍል የድምፅ መቅጃ መሳሪያ “በበረራ ሰራተኞች መካከል የነበረውን ንግግር፤ ከመቆጣጠሪያ ማማ ጋር የነበረውን ግንኙነት፤ በተለይ ደግሞ አብራሪው እና ምክትል አብራሪው እርስ በርሳቸው ሲያደርጉ የነበረውን ግንኙነት” ይይዛል። በተለይ ለአደጋ ምርመራ ወሳኝ የሆነ መሳሪያ በመሆኑ መገኘቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ካፒቴን አማረ አስረድተዋል።

ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 -800 ማክስ አውሮፕላን የተከሰከሰው ከቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር። ኢትዮጵያ አውሮፕላኑን ከአምራቹ ቦይንግ ኩባንያ የተረከበችው ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም ነበር።

ንብረትነቱ ላየን ኢየር የተባለው የኢንዶኔዥያ አየር መንገድ ተመሳሳይ አውሮፕላን ጥቅምት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ተከስክሶ 189 ሰዎች ሞተዋል።

ይህን ተከትሎ በቦይንግ አዲሱ ምርት ላይ ጥርጣሬዎች በዝተዋል፡፡ ብዙዎቹ አየር መንገዶችም አውሮፕላኑን ለጊዜውም ቢሆን ከመሬት እንዳይነሳ አድርገዋል፡፡ ጥርጣሬዎቹን ለመፍታትም ሆነ የአደጋዎቹን እውነተኛ መንስኤ ለማጣራት ብላክ ቦክስ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡  ብላክ ቦክሱ ወደ ፈረንሳይ ተወስዶም ውስጡ ያለው መረጃ በተሳካ ሁኔታ ወደ ኮምፒዩተር መገልበጡ ተገልፃል፡፡

ብላክ ቦክስ ምንድነው?

በተለምዶ ብላክ ቦክስ ወይም ጥቁር ሳጥን እያልን የምንጠራው የመረጃ ሳጥን እንደስሙ ጥቁር አይደለም፤ የሳጥን ቅርፅም የለውም። ቅርፁ እንደ ሲሊንደር ነው። ቀለሙ ብርቱካናማ። ለምን ጥቁር ተባለ ለሚለው አንድም ቆዬት ባሉት ጊዜያት በድህረ-አደጋ ወቅት የመሳሪያውን ፋይዳ ለመግለፅ ጋዜጠኞች “wonderful blackbox” ሲሉ ከገለፁት በኌላ ነው ሲባል፤ በተጨማሪም የበፊቶቹ ብላክ ቦክሶች የውስጥ ክፍል ጥቁር ስለነበር የሚሉም አሉ። የሆነ ሆኖ ብላክቦክስ በማንኛውም ቦታ ላይ እንዲታይ የተሻለው ቀለም ብርቱካናማ ነው ተብሎ ስለተመረጠ ብርቱካናማ ቀለም እንዲኖረው ተመርጧል።

ጥቁር ሳጥን የአውሮፕላን ማንኛውንም እንቅስቃሴ የሚመዘግብ መሳሪያ ነው። መሳሪያው የትኛውንም አደጋ መቋቋም ይችላል። ብላክ ቦክስ ከፍተኛ ቃጠሎ ውስጥ ቢሆን በ2 ሺህ ፋራናይት ልክ ሙቀት ለ1 ሰዓት ያክል ሳይቃጥል ወይም እሳቱ ሳይጎዳው መቆየት ይችላል። የመከስከስ አደጋ እንዳያጋጥመውም የ5 ሺ ፓውንድ ግፊትን እንዲቋቋም ሆኖይሰራል። ብላክ ቦክስ ውሃ ውስጥ ሲገባ ሴንሰሩ ወዲያውኑ መስራት ይጀምራል። በዚህ መንገድም ይገኛል። መሬት ላይ ግን ሴንሰሩ አይሰራም። የሚገኘው ብርቱካናማውን ቀለም በመፈለግ ይሆናል። በቀላሉ የማይጎዳ 3400 Gs የመረጃ ቋትም አለው። ይህ ማለት ከአዲስ አበባ ሳኦ ፓውሎ ብራዚል አውሮፕላኑ ደርሶ እስኪመለስ ያለውን መረጃ(ዳታ) የአብራሪውን እንቅስቃሴ፣ የአውሮፕላኑን ፍጥነት፣ ከፍታውን፣ የነዳጅ ሁኔታ ወ.ዘ.ተ እንቅስቃሴ ይመዘግብለታል ማለት ነው። ከፍተኛ እርጥበት የመቋቋም አቅም ያለው መሳሪያው በውሃ ውስጥ ሆኖ የያዘውን መረጃ ሳያጣ ለ2 ዓመት መቆየት ይችላል። በውሃው ውስጥ 20 ሺህ ጫማ ሰጥሞ ለ30 ሰአት ለመረጃ ፈላጊወች መረጃ ማቀበል ይችላል። እናም የአውሮፕላን አደጋ ባጋጠመ ጊዜ ፈላጊዎች ይህንን ጥቁር ሳጥን ማግኘት ትልቁ ስራቸው ያደርጋሉ።

የጠቅላ ሚኒስትሩ  ‹ብላክ ቦክስ› የት ገባ?

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ችግር ላይ ናት፡፡ ለውጡ እስካሁን ትክክለኛውን ቅርጽ አልያዘም፡፡ አልለየለትም፡፡ ዜጎች በለውጡ አልተማመኑም፡፡ እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥርጣሬው በርክቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን በይፋ እስከመቃወም የዘለቀ ስሜትን እያስተዋልን ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የዛሬ ዓመት ስልጣን እንደተረከቡ ያደረጉት ንግግር የብዙዎችን ስሜት የያዘ ነበር፤ በተለይም በአንድነት ወደ ተሻለ የስልጣኔ ጎዳና ልንሄድ ነው ብለው ተስፋ ያደረጉ ዜጎች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና ወር ሳይሞላቸው አስገራሚና አስደማሚ እርምጃዎቻቸውን በመውሰድ የታሰሩ የፖለቲካ እስርኞችን እየፈቱ ማስወጣት ጀመሩ፤ በውጭ ሀገር በስደት ላይ የነበሩና ወደ ሀገራቸው የመግባት ዕድል ያልነበራቸውን የፖለቲካ ፖርተዎች ‹ ኑ!› አሉ፡፡ ምንም እንኳ አንዳንዶቹ በዚያው ባህሪያቸው ቢቀጥሉም ፖርላማ ሳይቀር በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩትን ድርጅቶች ‹አሻባሪነታቸውን› በዚያው ፖርላማ አስነሱላቸው፡፡

ሃያ ዓመታን ያስቆጠረውን የኢትዮ ኤርትራ የፀብ ግድግዳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረመሱት፡፡ አስመራ ድረስ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ተቃቀፉ፡፡ የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋትና የተለያዩ እርምጃዎችን ወሰዱ፡፡በውጭ ሀገር ከሚኖሩ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተፈጥሮ የቆየውን ፀብ ‹ግንቡን እናፍረስ፤ ድልድዩን ንገንባ› በሚል መርህ በአሜሪካና በአውሮፖ ከተሞች የደመቀ አቀባበል ተደርጎላቸው የዲያስፖራውን ልብ አሸፈቱ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃዎች የተመለከቱ የውጭ ሀገር መንግስታትና ዲፕሎማቶች ሳይቀሩ ሀገሪቱ ወደ ቀደመ ዝናዋና የስልጣኔ ማማዋ ላይ ልትመለስ ነው በሚል ጉዳዩን በአድናቆት መመልከት ጀመሩ፡፡አንዳንዶች እንደውም ገና ስልጣን ላይ ከወጡ ዓመት ያልሞላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለኖቤል የሰላም ተሸላሚነት በእጩነት መቅረብ አለባቸው በማለት ‹የይረጧቸው› ዘመቻ በአደባባይ ጀመረው ነበር፤

ቅናት ቀናትን እየወለዱ ሲመጡ ወደ ሀገር ቤት ከገቡ የፖለቲካ ድርጅቲች ጋር በተያያዘ ግጭቶች እዚህም እዚያም መታየት ጀመረ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ቀለል አድርገው በትእግስት ለመፍታት እንደሚጥሩ ቢናገሩም የተደበቁ የፖለቲካ ፍላጎቶችና የአክቲቪስቶች ሚና የለውጥ ሀይሉን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚጥሉ ተግባራት መከናወን ጀመሩ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ቲም ለማ የሚባለውን የለውጥ ሀይል በይፋ ሲደግፉ የነበሩ ወገኖች በአብዛኛውም የአንድነት ሀይሎችን የሚያስቀይሙ ተስፋዎቻቸውንም የሚያጨልሙ ትርክቶች በኦሮሞ የፖለቲካ ሀይሎች መሰንዘር ሲጀምር ዜጎች ቆም ብለው ለውጡን በጥርጣሬ አይን ማየት ጀመሩ፡፡

ስልጣን ከያዙ 3 ወር ሳይሆናቸው ነበር የአዲስ አበባ ህዝብ የእሳቸውን ፎቶግራፍ የታተመበት ቲሸርት ለብሰው ለድጋፍ ሰልፍ ወደ መስቀል አደባባይ የተመመው፡፡ በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይም ቦንብ ተወርውሮ የአዲስ አባባ ወጣቶች የሞትና የመቁሰል አደጋ አጋጥሟቸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሀገሪቱ መዲና በሆነችው በአዲስ አባባ ዙሪያ ይቀርብ የነበረው የይገባኛል ጥያቄ ከአክቲቪስቶችና ከፖለቲከኞች አልፎ በኦሮሞው ገዢ ፖርቲ ኦዲፒና በክልሉ መንግስትም የ‹የእኛ ነው› ትርክት በመግለጫ ስም መውጣቱ  አነጋጋሪ ሆነ፡፡

በተለይም  የለውጥ ሀይሉ ዋና ሞተር ስለመሆናቸው የሚነገረው የአቶ ለማ መገርሳ ‹ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው › ከሚለው ታሪካዊ ንግግራቸው  የሚስተካከል የ‹ፊንፊኔ  ኬኛ › የተሰኘ ንግግራቸው የአዲስ አበባ ከተማን የባለቤትነት ጥያቄ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል፡፡ አቶ ለማ በንግግራቸው የተመለከተና ስውር የህዝብ ሰፈራ የሚገልፅ የቪዲዮ ንግግር  የለውጥ ሀይሉን ስውር ደባ ያሳየ ተደርጎ ተውሰዷል፡፡ ይህንን ተከትሎም በለገዳዲና በለገጣፎ  ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቤት በሰባት ቀን ማስጠንቀቂያ እንዲፈርስ ሲደረግና ህጻናትና እናቶች ሲያነቡ ጠቅላይ  ሚኒስትሩ ‹ይሄ የእኔ ስራ አይደለም› ብለው ነገሩን ማጣጣላቸው ከጀርባ የለውጥ ሀይሉ ይዞት የመጣው እቅድ ምንድነው? የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ  ስልጣን እንደያዙ እዚህም እዚያም ህዝቡ ሊያያቸውና ሊያዳምጣቸው ይፈለጉ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር የተቃውሞና የትችት ናዳ እያስተናገዱ ነው፡፡ አንዳንዶች ‹የለውጥ ሀይሉ ድብቅ አጀንዳ አለው› በሚል እየዘረዘሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹ብላክ ቦክስ› በአስቸኳይ ሊፈለግና በውስጥ ያለው መረጃም ይፋ ሊሆን ይገባል እያሉ ነው፡፡ ‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን› የሚለው ንግግራቸውም ‹ኦሮሚያ በፊንፌኔ ላይ ያላትን የባለቤትነት መብት ለማስከበር እንሰራለን› በሚለው የኦህዴድ መግለጫ መተካቱም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ብላክ ቦክስ ለማፈላለግ እንደመነሻ እየተጠቀሰ ነው፡፡

ለውጡ በእርግጥ ተቀልብሷል?

 

ጦማሪው በፍቃዱ ኃይሉ  ‹ለውጡ ተቀልብሷልን?› ሲል በአንድ ጽሑፍ ይጠይቃል፡፡ ‹ትላንት መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ‘9 ሚሊዮን ከሚጠጉ ኢትዮጵያውያን መካከል፥ 3.8 ስምንት ሚሊዮኖቹ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ናቸው’ የሚለውን በመግለጫ እያሳወቀ ባለበት ሰዓት በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሔዱ ነበር። የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ይህንን ያህል ከፍ ማለት ያልቀሰቀሰውን ተቃውሞ፥ ኦሮሚያ የአስተዳደር ክልል ውስጥ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሰጠታቸው ግን አስነስቶታል› ይላል በፍቃዱ፡፡

የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲከኞችን በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚወሰዱ እርምጃዎች አንድ የሚያደርጋቸውን ያህል ሌላ የሚያሥማማቸው ነገር ያለ አይመስልም። ከአዲሱ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) አመራሮች መምጣት በፊት የነበሩትን ተቃውሞዎች ከጫፍ እስከ ጫፍ በአመፅ ያንቀሳቀሰው “የአዲስ አበባ መስፋፋት” ጉዳይ ነበር፤ አሁንም የትላንት እና ከትላንት ወዲያ ተቃውሞዎች እና ማጉረምረሞችን የወለዳቸው ይኸው የአዲስ አበባ በሌላ መልኩ መሥፋፋት ጉዳይ ነው።

የተቃውሞዎቹን መጋጋል ተከትሎ ኦዴፓ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት መግለጫ አውጥቷል። ኦዴፓ በመግለጫው “የኦሮሚያ ወሰንን ተሻግረው የተሠሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከክልሉ ዕውቅና ውጪ ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸው ትክክለኛ አለመሆኑን” አስታውቋል።

መግለጫው ተቃውሞዎቹን ለማስታገስ የወጣ ነው ወይስ እውነትም ኦዴፓ ስለጉዳዩ ምንም ዕውቀት አልነበረውም? እውነት የኦዴፓ አባል የሆኑት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የመኖሪያ ቤቶቹን ዕጣ አወጣጥ ፓርቲያቸው ሳያውቅ ነው ያከናወኑት? የዕጣ አወጣጡ መርሐ ግብር ላለፉት ወራቶች ሲራዘም ቆይቶ በዚህ ሳምንት ከትላንት በስቲያ እንደሚወጣ ሲነገር ኦዴፓ የት ነበር? ከሁሉም በላይ ደግሞ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር ክልል ውስጥ ሲገነቡ የክልሉ መንግሥት እንዴት ዝም አለ? የአዲስ አበባ መስተዳድርስ ከአስተዳደር ወሰኑ ተሻግሮ ግንባታውን ለማካሔድ እንዴት ደፈረ? በፍቃዱ እንደሚለው እነዚህን ጥያቄዎች አንስቶ ለሚመለከት ሰው አብዛኛው ድርጊት የቲአትር ገጽታ ያለው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም ለማምጣት ደፋ ቀና እያሉ የጎረቤት አገራትን መሪዎች በማሥማማት በተጠመዱበት ወቅት ኢትዮጵያ በውስጣዊ ቀዝቃዛ ጦርነት እየታመሰች ነው። የጎረቤት አገራት ኩርፊያ ያስጨነቃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገር ውስጥ የዘውግ ብሔርተኞችን (ethnonationalists) ፍጥጫ እና ቀዝቃዛ ጦርነት ለማስታገስ ያላቸው ቁርጠኝነት፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቀዛቀዘ ይመስላል።

በዘውግ ተኮር ግጭቶች ምክንያት ብቻ ተፈናቅለው እርዳታ የሚጠብቁ ዜጎች ቁጥር 3.1 ሚሊዮን መሆኑን መንግሥት አምኗል። የአማራ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በትግራይ እና አማራ ሕዝብ መካከል “ወደ ጦርነት ሊያመሩ የሚችሉ ፀብ አጫሪነቶቸን” እንደማይቀበል የካቲት 26 ቀን 2011 መግለጫ አውጥቷል። መንግሥታዊ ያልሆኑ በኅቡዕ የተደራጁ አካላት ከመፈርጠማቸው የተነሳ፥ ዜጎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የደኅንነታቸው ጉዳይ ያሳስባቸው ይዟል።

ይህ ሥጋት ገበያውን እያቀዛቀዘው መሠረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ላይ ተፅዕኖው እንዳይበረታ ተፈርቷል። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ ውጥረት መካከል የፌዴራል መንግሥቱ የትኩረት አቅጣጫ ምን እንደሆነ ግራ እስከሚያጋባ ድረስ ዝምታን መርጧል። ፍጥነቱ አስደናቂ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራርም እጅግ በጣም መንቀራፈፍ አምጥቷል። ሌላው ቀርቶ ቢሳካ የለውጡ ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚቆጠረው የአፋኝ አዋጆች ክለሳ ሒደቱ ከአጀማመሩ አንፃር እጅግ ዘግይቷል።

ይህ በእንዲህ እያለ የዘውግ ብሔርተኞች ግን ሁሉንም ነገር “የኔ ነው”፣ “የኔ ነው” በሚል ሽሚያ የየክልል መንግሥቶቻቸውን እየጠመዘዙ ነው። በትግራይ እና አማራ ክልሎች መካከል የሚታየው ውጥረት እንዲሁም አዲስ አበባን በተመለከተ የሚነሳው ውዝግብ የዚሁ አልጠግብ ባይ ብሔርተኞች ጥያቄ የወለደው ነው። የክልል መንግሥታቱም ሕዝባዊ ቅቡልነት ለማግኘት ወይም ያገኙትን ላለማጣት ሲሉ የየብሔርተኞቹን ጥያቄ በማስታመም፣ ውሳኔያቸውን ከብሔርተኞቹ ጋር ለማሥማማት በመሞከር እና ወጥ አቋም ይዞ የለውጡን ፍላጎት በሚመጥን መልኩ በፍጥነት በመገስገስ ፈንታ፣ ወትሮም ፍኖተ ካርታ ያልነበረውን የለውጥ እና የመሻሻል ሒደት በብሔርተኞቹ ጮርቃ ሕልም እንዲመራ ወደማድረጉ አዝምመዋል። በዚህ ከቀጠሉ በኦዴፓ እና አዴፓ መካከል የተመሠረተው እና ለለውጡ አንድ አስተዋፅዖ አበርካች የተባለለት ጥምረትም እንዳይላላ ያሰጋል። እናም በችግር ውስጥ ላለችው ሀገር የችግሯን መንስኤ ለመመርመርና በቀጣይ ሌላ ችግር ላይ እንዳትዳትወድቅ መፍትሔ ለማምጣት የጠፋውን ብላክ ቦክስ ፈልጎ ማግኘት ግድ ይላል፡፡

የችግር አዙሪት

አወዛጋቢ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ፌስ ቡክ እና ትዊተርን በመሰሉ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በሚዘወተሩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሳምንት ከሳምንት አይጠፉም። አንዱ ሲሄድ ሌላ ይመጣል። አንዱ ገና በቅጡ ሳይረግብ ሌላው በእግሩ ተተክቶ ያከራክራል፣ ያፋጫል፣ ያነታርካል ባስ ሲልም ያሰዳድባል። ባለፈው ወር ከፍተኛ ትኩረት የሳበው የለገጣፎ ቤቶች መፍረስ ጉዳይ እምብዛም ሳይደበዝዝ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ንግግር ከፍ ያለ ውዝግብን ወልዶ ለውጡ ወዴት እየወሰደን ነው የሚል ጥያቄንም ፈጥሯል።

አቶ ለማ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በሌሎች ቦታዎች ላይ ስለሰፈሩ የኦሮሞ ተወላጆች ለታዳሚያኑ በኦሮምኛ ያቀረቡት ማብራሪያ ነበር የውዝግቡ መነሻ። “ርዕዮት” በተሰኘ የብዙሃን መገናኛ ወደ አማርኛ የተመለሰው ይሄው የፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ “ቲም ለማ” ተብለው የሚታወቁትን የኢህአዴግ አመራሮች “ድብቅ አጀንዳ ያጋለጠ ነው” በሚል ብዙዎች ተቀባብለውታል። ከአተረጓጎሙ ትክክለኛነት እስከ ከአውድ ውጭ የመወሰድ ጉዳይ አንስተው የተከራከሩም ነበሩ። ከክርክሩም በላይ ግን ኢትዮጵያውያን በለውጡ ላይ ያላቸው እምነት እየተሸረሸረ መምጣቱን ማየት መጥፎ ስሜት ይፈጥራል፡፡ በዚያ ሁሉ ተስፋ ተሞልቶ የነበረ ዜጋ ተስፋ መቁረጥ ሲጀምር ያስፈራል፡፡ እንደሃገር ከችግር አዙሪት ሳንላቀቅ ልንቀጥል ነውን? ብለን ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡

ረሃብ በጌዲኦ

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች እስከ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። ከተፈናቃዮች የተወሰኑት ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንደተመለሱ ቢነገረም በየጊዜው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች መፈናቀሉ ቀጥሏል። አሁንም በመጠለያ ያሉ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቀናትን እየገፉ ይገኛሉ።

በሶማሌ ክልል ፋፋን ዞን ቆሎጂ መንደር ስር ባለ ቦታ በርካታ ሴቶች እና ህጻናት ይታያሉ። የተወሰኑቱ በአካባቢው ካለ ቧንቧ ውሃ ለመቅዳት ይሻማሉ። በስፍራው የሚታዩት ብዙዎቹ ሰዎች የአካባቢው ነዋሪዎች አይደሉም። የሶማሌ ተወላጆች የሆኑት በሺህዎች የሚቆጠሩት እነዚህ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው ወደ ቆሎጂ የመጡ ናቸው። ተፈናቃዮቹ በቆሎጂ ከኮረብታ ስፍራ ስር ባለ የተንጣለለ ሜዳ ላይ መጠለያዎችን ቀልሰዋል። ችምችም ብለው የተደረደሩት አብዛኞቹ ትናንንሽ መጠለያዎች በላስቲክ የተሰሩ ሲሆን የአካባቢውን ባህላዊ የቤት አሰራርም የተከተሉ ናቸው።

በእንደዚህ አይነት መጠለያዎች በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩት ተፈናቃዮች ቁጥር 80 ሺህ እንደሚደርስ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከተፈናቃዮቹ አንዷ ያሉበትን አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ እንዲህ ትገልጻለች። “ጥቃት ሲደርስብን ከብቶቻችን እና ሌሎችንም ነገር ትተን ነው የወጣነው። ባሎቻችን እና ልጆቻችንን አጥተናል። እዚህ ያለው የኑሯችን ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ምንም የለንም” ትላለች።

በኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት የተፈናቃዮች ብሶት እና እሮሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተደጋግሞ የሚደመጥ ሆኗል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እዚህም እዚያም በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት ከተወለዱበት፣ ካደጉበት እና ለዓመታት ከኖሩበት ስፍራ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ኑሯቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። የተፈናቃዮች ቁጥር ከሺህዎች ተሻግሮ እንደ ዋዛ ወደ ሚሊዮኖች አሻቅቧል።

ከዓመት በፊት በሶማሌ እና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የተፈናቃዮቹ ቁጥር አንድ ሚሊዮን ገደማ መሆኑ ሲገለጽ ብዙዎችን አስደንግጧል። ለተፈናቃዮቹ እርዳታ ለማሰባሰብ እና በተለያዩ አካባቢዎች ለማስፈር ሰፊ እንቅስቃሴ ሲካሄድም ቆይቷል። የተወሰኑትንም ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስም ተሞክሮ ነበር። በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ይህ የሰብዓዊ ቀውስ ቁስሉ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠግግ ነበር በስተደቡብ አቅጣጫ በሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ያፈናቀለ ግጭት የፈነዳው።

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል ጌዶ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች በተቀሰቀሰው በዚህ ግጭት ከቀያቸው የሸሹ ሰዎች ብዛት ቀደም ሲል በሌሎች አካባቢዎች ከተከሰቱት ጋር ተዳምሮ የተፈናቃዮችን ቁጥር ወደ ሶስት ሚሊዮን አድርሶታል። ይህም ኢትዮጵያን በተፈናቃይ ብዛት በዓለም የመጀመሪያው ረድፍ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል። ምጸታዊው ጉዳይ ደግሞ በእርስ በእርስ ጦርነት በሚታመሱት ሶሪያ እና የመን ያሉት ተፈናቃዮች እንኳ በኢትዮጵያ ያሉትን ያህል አለመሆኑ ነው።

ከብዙዎቹ መፈናቀሎች ጀርባ ያለው የብሔር ተኮር ግጭት ከመብረድ ይልቅ መልኩን እየቀያየረ በተለያዩ አካባቢዎች መከሰት መቀጠሉም ብዙዎች መጪውን ጊዜ በስጋት እንዲያዩ አድርጓቸዋል። ከኦሮሚያ እስከ ደቡብ፣ ከቤንሻንጉል እስከ ሶማሌ ባለፉት ወራት የተከሰቱ ግጭቶችም ስጋቱ ስጋት ብቻ እንዳልነበር በተጨባጭ አሳይተዋል። ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በኦሮሚያ ክልል እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ አካባቢዎች እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን ሸሽተው በየመጠለያዎቹ የሰፈሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ቁጥር በሶስት እጥፍ መጨመሩን ከአካባቢው ባለስልጣናት የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን እስካሁንም ተጠልለው ያሉ ነዋሪዎች በተለይ ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸው ተነግሯል፡፡ በረሃብ ተጠቅተዋል፡፡ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስቃቂ ምስሎችን እያየን ነው፡፡

ለተፈናቃዮች በየጊዜው እርዳታ ለማድረስ በየአካባቢዎቹ ያለው የጸጥታ ችግር እንቅፋት መሆኑን የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሲገለጽ ቆይቷል።

በመጨረሻ

አንድ ዓመቱን ለመያዝ የቀናት እድሜ የቀረው አዲሱ የኢትዮጵያ አስተዳደር (የነዶ/ር አብይ መንግስት) በህዝብ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት ላለማጣት አሁን በየአካባቢው ላሉት ትላልቅ ችግሮች መፍትሔ መፈለግ አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በቅድሚያ የጠፋውን የሃገሪቱን ‹ብላክ ቦክስ› ፈልጎ ማግኘት ግድ ይላል፡፡ የችግራችንን ዋና ዋና መንስኤዎች ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ከሁሉም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት የሚገባን ለዚህ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አፍሪካን በተለይ ምስራቅ አፍሪካን አንድ ለማድረግ የጀመሩትን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መንቀፍ ባይቻልም የሃገር ውስጡን ጉዳይ ችላ ብሎ ውጭ ላይ ትኩረት ማድረግ ግን ተገቢ አይመሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትን ወደአንድ ጎጆ ለመስብሰብ ጥረት ከማድረጓ አስቀድሞ የዜጎቿን  ደህንነት ያረጋገጠች ሀገር መሆን አለባት፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe