የፈርኒቸር ቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች ላይ ያተኮረ ዓውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

የፈርኒቸር ቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች ላይ ያተኮረ ዓውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

ናርዶስ ፍቃዱ | 14 April 2019

የፈርኒቸር፣ ቤተ ውበትና ግንባታ አጨራረስ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ያተኮረና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰናዳ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው፡፡ የእነዚህ ምርቶችና አገልግሎቶች ዓውደ ርዕይና ጉባዔ በፕራና ኤቨንትስ ኩባንያና በሻክረክስ ንግድና ኤቨንት ማኔጅመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አዘጋጅነት ከሚያዝያ 24 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ለማካሄድ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ተብሏል፡፡ ይህ ከ50 በላይ አምራቾች የሚሳተፉበት ዓውደ ርዕይ ኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ግብፅ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኬንያና ፓኪስታንን አሳትፏል፡፡ ትኩረቱን በቤት፣ በቢሮ፣ በኢንዱስትሪ ፈርኒቸሮች፣ የማስዋቢያ ምርቶች፣ መብራቶች፣ መጋረጃዎችና ልዩ ልዩ ግብዓቶች ላይ ያደረገው ዓውደ ርዕይ ከ5,000 በላይ ጎብኚዎች እንደሚታደሙበትና ከ500 በላይ የንግድ ልውውጥ እንደሚካሄድበት ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ. 2018 የአሥር ቢሊዮን ብር የፈርኒቸር ግዥ የፈጸመ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ አምራቾች የገዛው 20 በመቶ ያህሉን ነው፡፡ ‹‹ይኼንን ከግንዛቤ በማስገባት አቅም ያላቸው አገር በቀል ድርጅቶችን ከመንግሥት አካላት ጋር አንድ መድረክ ላይ የሚያስቀምጥ ጉባዔ አዘጋጅተናል፤›› የሚሉት ደግሞ አቶ ነብዩ ለማ የፕራና ኤቨስንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ‹‹ይህ መድረክ በውጭ ምንዛሪም ማስገኘትም ይሁን፣ በንግድ ትስስር ደረጃ ለአገራችን ትልቅ ጥቅም አለው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ አቶ አክሊለ በለጠ የሻክረክስ ንግድና ኤቨንት ማኔጀመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ ‹‹በአገራችን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ያለውን ይህንን ዘርፍ ይበልጥ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉትንና የቆዩትን ኩባንያዎች በአንድ ጣራ ሥር በማሰባሰብ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲወያዩ ማድረግ፤ እንዲሁም አማራጮችን ለመንግሥትም ሆነ ለኅብረተሰቡ ማሳየት በዋነኛነት ይዘን የተነሳነው ሐሳብ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የዚህ ዓውደ ርዕይ ዋና ዓላማ በኢንዱስትሪ መሪዎቹ መካከል አቻ ለአቻ ግንኙነት በመፍጠር ቴክኖሎጂያቸውን የሚያሳድጉበትን ዕድል መፍጠር ነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ሁለተኛዋ ግዙፍ የፈርኒቸር ገበያ መዳረሻ ስትሆን የፈርኒቸር ምርቶችን ከውጭ አገር በማስገባት በአፍሪካ አምስተኛ ደረጃን ስለመያዟም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe