ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፡ ‘ከሕግ ውጪ’ የተዋሃዱት አምስቱ ክልሎች

ወታደራዊው መንግሥት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ መዋቅር መሰረታዊ ለውጥ ተደርጎበት በዋናነት ቋንቋን መሰረት ባደረገ ሁኔታ የአስተዳደር ክልሎች ተመስርተዋል።

ከሰማኒያ በላይ የተለያየ ሐይማኖት፣ ቋንቋና ባሕል ያላቸው ሕዝቦችን መብትና ጥቅም ያስከብራል በሚል ዋና ዋና በሚባሉትና በርካታ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው ብሔሮች ዙሪያ ውስጣዊ የአስተዳደር ሥርዓቱን ማዋቀር በወቅቱ የሃገሪቱን የመሪነት ሚና የተረከቡት ኃይሎች ዋነኛ ሥራ ነበር።

በዚህም ለዘመናት ኤርትራን ጨምሮ በ14 ክፍላተ ሃገራት የተዋቀረው የአስተዳደር ሥርዓት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በአዲሱ ቋንቋን መሰረት ባደረገ የፌደራል አስተዳደራዊ አወቃቀር አንዲተካ ተደርጓል።

ይህም የሆነው ሃገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ መንግሥት ከመጽደቁ በፊት በተቋቋመው ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት አማካይነት ነበር። የወቅቱ አከላለል 14 ክልሎች እንዲፈጠሩ ያደረገ ሲሆን አዲስ አበባም በክልል ደረጃ የተዋቀረች ከተማ ነበረች።

በሽግግሩ ወቅት በአዋጅ ቁጥር 7/1984 መሰረት አዲስ የክልል አወቃቀር ሲታወጅ በሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ የሚናገሩትና በወቅቱ የምክር ቤት አባል የነበሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከሁለት ዓመታት በኋላ አሁን በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ አምስት አካባቢዎች በሕገ ወጥ መንገድ ተዋህደው አንድ ክልል እንዲመሰርቱ መደረጉን ያስታውሳሉ።

በሽግግሩ ጊዜ የተዋቀረው አዲሱ የአስተዳደር ሥርዓት በዋናነት በቁጥርና በአሰፋፈር ተለቅ ተለቅ የሚሉትን ማዕከል አድርጎ የተካለለ ቢሆንም የደቡብ ክልል ግን 56 የሚደርሱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችን በመያዝ ከሌሎቹ ክልሎች በተለየ የተዋቀረ ነው።

በወቅቱ አዲስ አበባም ራሷን የቻለች ክልል በመሆን የፌደራል መንግሥቱ አካል የነበረች ሲሆን በኋላ ላይ ይህ ተቀይሮ በቻርተር የምትተዳደር የከተማ አስተዳደር እንድትሆን ተደርጓል፤ ድሬዳዋም በተመሳሳይ የአስተዳደር ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች።

በወቅቱ ክልሎቹ ሲዋቀሩ ቋንቋንና ማንነትን መሰረት አድርገው ሲሆን አሁን ከያዙት ስያሜ በተለየ በቁጥር ነበር የሚታወቁት። ቁጥሩ ከትግራይ ክልል አንድ ብሎ ይጀምርና ደቡብ ተብሎ በአንድ እንዲጠቃለል የሆነው ክልል ከሰባት እስከ 11 የሚደርሱትን ክልሎች በውስጡ እንዲይዝ ተደርጎ አምስት ክልሎችን ነበሩት ይላሉ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ።

እንደእርሳቸው አባባል በአከላሉ ሂደት ወቅት አሁን የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ተብሎ ወደ አንድ የተጠቃለለው በአምስት ዋና ዋና ክልሎች ተዋቅሮ የተለያዩ ሕዝቦች የሚኖሩባቸው ክልሎች እንዲሆኑ ተደርገው ነበር የተደራጁት።

በዚህም መሰረት በጊዜያዊው የሽግግሩ መንግሥቱ ዘመን እነዚህ አምስት ክልሎች እንደ ክልል ለሁለት ዓመት ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች በመሆን ሲተዳደሩ ቆይተዋል።

Presentational grey line
  • ክልል 7፡ ይባል የነበረው ክልል ጉራጌ፣ ከምባታ፣ ሃዲያ፣ የም፣ ሐላባና ስልጤን ጨምሮ በመያዝ ዋና ከተማውን ሆሣዕና ላይ ነበር።
  • ክልል 8፡ ይባል የነበረው ክልል ዋና ከተማውን ሐዋሳ ላይ በማድረግ ሲዳማን፣ ጌዲኦን፣ አማሮንና ቡርጂን በመያዝ የተዋቀረ ነበር።
  • ክልል 9፡ ይባል የነበረው ክልል ማዕከሉን አርባ ምንጭ ላይ አድርጎ ወላይታ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ዳውሮና ሌሎችንም አካቶ የተመሰረተ ነበር።
  • ክልል 10፡ ይባል የነበረው ክልል ደግሞ መቀመጫውን ጂንካ ላይ በማድረግ ደቡብ ኦሞ ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን አቅፎ የተካለለ ነበር።
  • ክልል 11፡ ተብሎ ተሰይሞ የነበረው ክልልም ሚዛን ተፈሪን ዋና ከተማው በማድረግ ከኦሞ ወንዝ ባሻገር ያሉትን ህዝቦች አካቶ የተመሰረተ ክልል ነበር።
Presentational grey line

ብዙም ያልዘለቀው የእነዚህ ክልሎች እድሜ ማዕከላዊው የሽግግር መንግሥት ክልሎቹ የተዋቀሩበትን አዋጅ 7/1984ን በመጣስ አምስቱን ክልሎች በአንድ ላይ እንዲዋሃዱ የሚያደርግ ትዕዛዝ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እንደወጣና በዚህ መሰረትም ክልሎቹ ከሁለት ዓመት በላይ ህልውና እንዳይኖራቸው ተደርጎ በአንድ ክልል እንዲጠቃለሉ መደረጉን ፕሮፌሰር በየነ ይገልጻሉ።

“ለዚህ ምክንያቱ እነዚህ ክልሎችን በአንድ ክልል ስር የማካተቱ እርምጃ ለማዕከላዊው መንግሥት ጥቅምና ቁጥጥር አመቺነት ነው” ይላሉ ፕሮፌሰሩ፤ አክለውም ድርጊቱን ተቃውመው ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውንና ከሽግግሩ ምክር ቤት እስከመባረር እንደደረሱ ይናገራሉ።

ያስከተለው ጽዕኖ

አምስቱን ክልሎች በአንድ ያማከለው የመንግሥት እርምጃ የተለያዩ ቦታዎች የየራሳቸው የሆነ የልማት ማዕከላት እንዳይኖራቸው እንደደረገ ይገላጻሉ ፕሮፌሰር በየነ። ይህም በተለያዩ ስፍራዎች ለሚኖር የሥራ ፈጠራና ለኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ ይኖረው እንደነበር ያምናሉ።

“ክልሎቹ በነበሩበት መተዳደር ቢችሉ ኖሮ አሁን ሐዋሳ ላይ የተከማቸው ሐብት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቅም ይሰጥ ነበር። በዚህም ደቡብ ውስጥ በእድገት ጎላ ብላ የምትታየው የሐዋሳ ከተማ ብቻ ሆናለች” የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ ነገር ግን አምስቱ ክልሎች በነበሩበት ቢቀጥሉ ኖሮ በርካታ ሊያድጉ የሚችሉ አካባቢዎችን መፍጠር ይቻል እንደነበር ያምናሉ።

ነገር ግን ኢህአዴግ ክልሎቹን ወደ አንድ ለማምጣት በወሰደው የዘፈቀደ እርምጃ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የልማት ማዕከሎች እንዳይፈጠሩ እንቅፋት በመሆን ክልሉም ሕዝቡም ተጎድቷል።

ከሃብት አንጻር ለተቀሩት የክልሉ አካባቢዎች በፍትሐዊነት ሊከፋፈልና ሊዳረስ የሚገባው ሐብት በሐዋሳ ላይ ብቻ እንዲፈስና እንዲከማች በማድረግ ሌሎቹ አካባቢዎች በተመጣጣኝ ሁኔታ እንዳያድጉ እንቅፋት መሆኑን ይናገራሉ።

በደቡብ ክልል ውስጥ የቦታ ይገባኛል እንዲሁም ክልል እና ዞን ለመሆን በርካታ ጥያቄዎች በተለያዩ የክልሉ ማኅበረሰብ አባላት ሲቀርቡና በዚህም ሽኩቻና ውዝግብ የነበረ መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰር በየነ፤ የእነዚህ ምክንያቶች ደግሞ የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት መጥፋት ያመጣው እንደሆነ ያምናሉ።

ነገር ግን ይህ “ሁሉም ጋር ያለ መናቆር ነው” ደቡብ ውስጥ እነዚህ አምስት ክልሎች በአንድ በመዋቀራቸው ከሌሎች ክልሎች ከታዩት ችግሮች የተለየ ነገር ገጥሞታል ብለው የሚጠቅሱት እንደሌለ ይናገራሉ።

ለፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የቀረቡት ክልል የመሆን ጥያቄዎች ምላሽ ቢያገኙ በሃገሪቱ አንድነት ላይ የሚፈጥሩት ውጤት የለም። እንደ እርሳቸው አተያይ ዋነኛው ተግዳሮት የሚሆነው “በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከሚያጋጥመው ኢኮኖሚያዊ ውስንነት ውጪ ክልልም ሆኑ ዞን፣ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ እስካሉ ድረስ ከስም ለውጥ ባሻገር የሚኖር ጉልህ ለውጥ የለም።”

ከአሉታዊው ውጤት ባሻገር ከተጠቀሱት ክልሉ ውስጥ የሚታዩ ውስጣዊ መሻኮቶችና መገፋፋቶች ባሻገር ከኢትዮጵያዊነትና ከኢትዮጵያ ህልውና አንጻር ሲታይ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች በአንድ ክልል ውስጥ መተዳደር እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ ሊሆን ይችላል ይላሉ ደቡብ ክልልን። “ለዚህም ነው ደቡብ ሲነሳ ዘወትር ትንሿ ኢትዮጵያ እስከመባል የተደረሰው” ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።

የክልሎቹ መዋሃድና ውጤቱ

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የተወሰነው ክልሎቹን ያለሕዝቡ ፈቃድ የመቀላቀል ውሳኔ በየጊዜው በተለያዩ ደረጃዎች ራስን የማስተዳደር ጥያቄዎች ደጋግመው እንዲከሰቱ አድርጓል። አሁንም አስር የሚደርሱ የክልሉ አካባቢዎች ክልል እንሁን የሚል ጥያቄን ይዘው ምላሽ እየጠበቁ ነው።

ፕሮፌሰር በየነም “ሕግን በመጣስ አምሰቱን ክልሎች ወደ አንድ ሲያጠቃልሏቸው ፖለቲካዊ ውሳኔ ነበር ። ይህም ለዛሬው ጥያቄና ችግር ዋነኛ ምክንያት ነው” በማለት ያምናሉ።

ሌሎችም አካባቢዎች ክልል የመሆን ጥያቄ አንስተዋል፤ ይህ ተግባራዊ ቢሆን ትናንሽ ክልሎች ከመመስረት ባሻገር በኢትዮጵያ ሃገራዊ ህልውና ላይ ተጽእኖ ይኖራቸዋል ብለው አያስቡም።

በርካቶች ክልል የመሆን ጥያቄን ያቀረቡት አካባቢዎች ሁሉም አወንታዊ ምላሽ ቢያገኙ በሚጠበቅባቸው ደረጃ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይችላሉ ወይ የሚል ጥያቄ ይነሳል።

ፕሮፌሰር በየነም “እነዚህ አዲስ ክልል የሚሆኑት አካባቢዎች ከውስጣቸው በቂ ሐብትና ገቢ ማመንጨት ይችላሉ ወይ? በራሳቸውስ በቂ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማድረግና መተዳደር ይችላሉ ወይ? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች በቅድሚያ መመለስ አለባቸው።” ባይ ናቸው።

ከሌሎች የሃገሪቱ ክልሎች በተለየ በርካታ የክልል እንሁን ጥያቄዎች የቀረቡለት የደቡብ ክልል ምላሽ ለመስጠት የተቸገረ ይመስላል። የክልሉ ገዢ ፓርቲም ከመቀመጫው ሐዋሳ ርቆ አዲስ አበባ ውስጥ በጥያቄዎቹ ዙሪያ ለቀናት ተወያይቶ ያወጣው መግለጫ ተጨባጭ ነገርን አላቀረበም።

ጥያቄዎቹ አዎንታዊ ምላሽን አግኝተው ቢያንስ አንድ ክልል መመስረቱ እንደማይቀር የበርካቶች እምነት ሲሆን ይህ ውጤትም በደቡብ ክልል ላይ በተለይ በዋና ከተማዋ ሐዋሳ ላይ የራሱ የሆነ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ይሰጋሉ።

ከዚህ አንጻርም አዳዲስ የሚከሰቱ የቦታ ይገባኛልና የድንበር ጥያቄዎች በሚፈጠሩትና በነባር ክልሎች መካከል ሊከሰቱ እንደሚችሉ አንዳንዶች ቢሰጉም ፕሮፌሰር በየነ ግን “የሚባሉት ውዝግቦችና ግጭቶች አሁንም ያሉ ናቸው ነገር ግን በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ በሕግ አግባብ መፍታት ብቻ ነው የሚያስፈልገው” በማለት ከአዳዲስ ጥያቄዎች ባሻገርም የነበሩ ጥያቄዎች ወደ ፊት መምጣታቸው አይቀርም ይላሉ።

source: BBC Amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe